Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, November 16, 2014

ከኢንጂነር ኃይሉ ሻወል ተጽዕኖ ያልወጣው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (በጌታቸው ባያፈርስ)

ከኢንጂነር ኃይሉ ሻወል ተጽዕኖ ያልወጣው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት
/መኢአድ/ ጠቅላላ ጉባኤ እና አሳፋሪው ድራማ
የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት /መአሕድ/ በ1984 ዓ.ም ተመስርቶ ገዢው ፖርቲ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላና በደቡብ ክልሎች በሚኖሩ በአማራ ብሔረሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን የግፍ ጭፍጨፋና የመብት ረገጣ ለመታገል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕግ የበላይነትን እንዲሁም የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ዕውን ለማድረግ ሰንቆ በተነሳው አላማ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ እንቅስቃሴ በማድረጉ የፖርቲው መስራችና እውቁ የሕክምና ምሁር ኘሮፌሰር አስራት ወልደየስ ደ/ብርሃን ከተማ በጠሩት ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ወደ ውህኒ ወርደው በግፍ ሕይወታቸው ያለፈ ቢሆንም የፖርቲውን ተቀባይነትና እንቅ ቃሴ ገዥው ፖርቲ ኢህአዴግ የሚገደብበት አቅም አላገኘም ነበር፡፡
መአህድ ይዞት በተነሳው አገራዊ አላማ ከብሔር ድርጅትነት ራሱን በማሳደግ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ የሚለውን ስያሜ በመያዝ በ1995 ዓ.ም ሕብረ ብሔራዊነቱን አውጆ እስከ 1996 ዓ.ም ባለው ጊዜ ከ1.2ሚ በላይ አባላት ያፈራና በርካታ ጽ/ቤቶችን በሀገሪቱ ክፍሎች በመክፈት ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ ነበር፡፡
መኢአድ በ1997 ዓ.ም ከሌሎች 3 /ሶስት/ ፖርቲዎች ጋር በመሆን ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ /ቅንጅት/ ፖርቲን በመመስረት ለምርጫ 97 የመኢአድ መሰረቱን ተጠቅሞ ቅንጅት ባደረገው እንቅስቄሴ ለተገኘው የፖለቲካ ተሳትፎና የምርጫ ውጤት መኢአድ የአንበሳውን ድርሻ መያዙ የትናንቱ የታሪክ እውነታ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የ97 ምርጫ ውጤትን ተከትሎ ገዥው ፖርቲ በወሰደው ኢዲሞክራሲያዊ የምርጫ ውጤት ቅልበሳ የተቆጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ “ድምጻችን ይከበር” በማለት በየአደባባዩ ለወጣው ሰላማዊ ሰልፈኛ በታጣቂ ኃይሎች የተወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ ብልጭ ብሎ የነበረውን የዲሞክራሲ ጭላንጭል ወደነበረበት ጨለማ በመቀልበስ የቅንጅት አመራሮችን ወደ ወህኒ ቤት በመወርወር ካሰረና ካስፈረደ በኋላ በተለመደ ድራማው ይቅርታ እንዲጠይቁ በማድረግ ከእስር እንዲለቀቁ የተደረጉት የቅንጅት አመራሮች በእስር ቤት እያሉ በተፈጠረ አለመግባባት ከወህኒ ቤት ከወጡ በኋላም በመቀጠሉ ጉዳዩን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት አንድም ሙከራ ሳይደረግ ወደ አሜሪካና አውሮፖ በቡድን በመንቀሳቀስ ሁሉም የራሳቸውን ቡድን በማጠናከር አለመግባባቱን እንዲባባስ አድርገው በዚህ ምክንያት አብዛኛው የቅንጅት አመራር አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ /አንድነት/ የሚል ፖርቲ መስርተው ለመንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን ጥቂት የመአአድ አመራሮች ወደቀድሞው ፖርቲያቸው መኢአድ በመመለስ ከሰኔ 14-15 2000 ዓ.ም የፖርቲውን የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ ኢንጅነሩን ኘሬዝዳንት በማድረግ የተናጠል ጉዞውን ሲጀምሩ የፖርቲውን የውድቀት ቁልቁለት “ሀ” ብለው የጀመሩ ሲሆን ለዚህ ውሣኔና አካሄድ ዋና ምክንያታቸው ደግሞ ምንም እንኳ ቅንጅት የሚለውን ስም ለማግኘት ለሌላ አካል የተሰጠ በመሆኑና ባያገኙትም ከቀስተ ደመና ፖርቲና ከአድሊ ፖርቲ ጋር አዲስ ፖርቲ መስርተው ለመቀጠል በአዲሱ ፖርቲ ውስጥ ቦታ አናገኝም ከሚለው ስጋታቸው በተጨማሪ በመኢአድ ፖርቲ ውስጥ በተለያዩ ደረጃ ተቀምጠው የሚያገኙት ጥቅማጥቅም ይቀርብናል የሚለው ትልቁ ምክንያታቸው እንደነበር በቀላሉ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የመኢአድ አመራሮች በተናጠል የመስራትና የመጓዝ ልምዳቸው ከራስ ጥቅም ጋር የሚያያዝ ሲሆን ለ2002 ምርጫ ከመድረክ ጋር አብሮ ለመስራትም ሆነ የመድረኩ አባል ለመሆን አልመፈለግና የፖለቲካ ፖርቲዎችን የምርጫ ስነ ምግባር ለመፈረም ኢህአዲግ ከአጋሮቹ ጋር በመራው ውይይት ላይ የመኢአድ ተሳትፎና የፖርቲው ኘሬዝዳንት ኢንጅነር ኃይሉሻወል ከኢህአዲግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር እጅ ለእጅ መጨባበጥ የፖርቲውን ትልቁን የውድቀት ርምጃ ያበሰሩ ሲሆን በአንዳንድ ግለሰብ አስተያየትም ኢንጅነሩ ካላቸው የንግድ ተቋምና ባለሀብትነት አኪያ “ልማታዊ ባለሀብት” አስብሎ ያስጠረጠራቸው እና በምርጫውም ላይ በገጠርም ሆነ በከተማ መኢአድ ላስመዘገበው ዝቅተኛ የድምፅ ቁጥር ዋንኛ ምክንያቱ ይሄው ሀቅ መሆኑ አጠያያቂ አልነበረም፡፡
የፖርቲው ጠቅላላ የውጤት መቀነስም ሆነ ኘሬዝዳንቱ በተወዳደሩበት የምርጫ ክልል እንኳ በግላቸው ያገኙት ዝቅተኛ የድምፅ መጠን የፖርቲውን እድገት እንደ ካሮት ወደታች መሔድ ከማሳየቱም በተጨማሪ የፖርቲው ኘሬዝዳንት ግንቦት 19/2002 ዓ.ም ከፖርቲ ኘሬዝዳንትነት ለቅቄያለሁ የሚለው የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባት የዚሁ የምርጫ ውጤት ዝቅተኛነት መሆኑን ከመልቀቂያ ደብዳቤው ላይ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በኋላ ፖርቲው ያለቅደመ ሁኔታ ከአንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ እንዲሁም ከብርሃን ፖርቲ ጋር ለመዋሀድ የሶስትእዮሽ ድርድር በመፍጠር በአብዛኛው ውይይት የተስማሙ ቢሆንም ከታህሳስ 16-18 ለሚደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ኘሬዝዳንቱ ወደ ፖርቲው በፍቃዳቸው በመመለስ ጉባኤውን አድርገን በጉባኤው እስከምናስወስን ድረስ የ3 /ሶስትዮሽ/ ድርድሩ ይቋረጥ የሚል ትዕዛዝ በመስጠታቸውና የሳቸውን ትዕዛዝ የሚቃወም አመራር ባለመኖሩ የውህደት ድርድሩ ተቋረጠ፡፡
ከታህሳስ 16-17/2003 በተደረገው የጠቅላላ ጉባኤ ላይም የፖርቲው ኘሬዝዳንት ስልጣን ይለቃሉ ተብሎ በመጠበቁ የኘሬዝዳንቱን ስልጣን የሚፈልጉ ሁለት ቡድኖች የራሳቸውን ቅስቀሳ /Lobbing/ በማጠናከራቸው ጉባኤው ጤናማ ሆኖ መቀጠል ባለመቻሉ የጉባኤው አባላት ኢንጅነር ኃይሉ ለ2/ሁለት/ ዓመት በኘሬዝዳንትነት እንዲቀጥሉ ሲያደርጋቸው እኔን በኘሬዝዳንትነት ከመረጣችሁ ተቀዳሚ ኘሬዝዳንት ሆኖ የሚያግዘኝ አቶ ያዕቆብ ልኬ በመሆኑ የእኔንም ጥቆማ አፅድቁልኝ በማለት ለጠቅላላ ጉባኤው ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጣቸውና የኢንጅነሩን ቃል በጉባኤ ተቃውሞ ማቅረብ የተለመደ ባለመሆኑ ጉባኤተኛው አፀደቀላቸው፡፡
ይሁን እንጂ በተቃራኒው የኘሬዝዳንቱ ቦታ ይፈልጉ የነበሩ ቡድኖች የአቶ ያዕቆብ ልኬ ተቀዳሚ ኘሬዝዳንት ሆኖ መመረጥ ተቃውሞ ባያቀርቡም ውስጣቸው ደስተኛ አለመሆናቸው በግልጽ ይንፀባረቅ ነበር፡፡
ታህሳስ 20/2003 ዓ.ም የስራ አስፈፃሚውን የስራ ድርሻ ኘሬዝዳንቱ በራሳቸው ፍላጎት ደልድለው ሲያበቁ ቀደም ሲል በአቶ ማሙሸት አማረ ተይዞ የነበረው የፖርቲው ዋና ፀሐፊ ለአቶ ተስፋዬ ታሪኩ መሰጠቱን ተከትሎ በእነ አቶ ማሙሸት አማረ እና በኢንጅነር ኃይሉ ሻወል መካከል የነበረው የአባትና ልጅ እንዲሁም የአካባቢዋ ገመድ ትስስር ተበጥሶ ወደለየለት አጋች ታጋች ድራማ በመሸጋገሩ የፖርቲው ሌላው ዙር የውድቀት ምዕራፍ ተከፈተ፡፡
ሐምሌ 30/2003 ዓ.ም መኢአድ በእየሩሳሌም ሆቴል በጠራው የማዕከላዊ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የእነ አቶ ማሙሸት አማረ ቡድን ከፖርቲው እንዲባረሩ የተወሰነ ሲሆን ይህ ምክር ቤት ሌላ ታሪካዊ ውሣኔ ወሰነ፡፡ ይኸውም ከዚህ በፊት የነበረው የፖርቲው መተዳደሪያ ደንብ ለኘሬዝዳንቱ ሰፊ መብት ሰጥቶ የነበረ ሲሆን ከታህሳስ 14-15 በተጠራው የጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ደንቡን እንዲሻሻል የማዕከላዊ ምክር ቤቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የኘሬዝዳንቱን ስልጣን በመቀነስ ለፖርቲው ማዕከላዊ ምክር ቤትና ለስራ አስፈፃሚው ቀንሶ በመሰጠቱ በኘሬዝዳንቱ እና በአብላጫው 10 /አስሩ/ ስራ አስፈፃሚ መካከል ሌላ ዙር አለመግባባት ተፈጥሮ 10 /አስር/ ስራ አስፈፃሚ በማገድ ወደ ጽ/ቤት እንዳይገቡ በመደረጉ የአባላት መከፋፈል ፖርቲውን በውድቀት ቁልቁለት እያንደረደረው በመሔዱ እና የእነ አቶ ማሙሸት አማረ ቡድንም ሆነ የእነ አቶ አሰፋ ሀብተወልድ ቡድን በየራሳቸው የያዙት አባላትና ደጋፊ ኢንጅነሩ ጽ/ቤቱን ይዘው ከቀሩት አባላት በእጅጉ የገዘፈ በመሆኑ እና የመጨረሻ እልባት ለማግኘት የጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ለምርጫ ቦርድ ከሁለቱም ቡድኖች በቀረበው ጥያቄ መሠረት ፖርቲው የጠቅላላ ጉባኤውን በመጥራት ሁሉም ቡድኖች በተገኙበት ጉባኤው የሚሰጠውን ውሣኔ እንዲያሳውቅ ቦርዱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የፖርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ሐምሌ 14 ቀን 2005 ዓ.ም የተጠራ ቢሆንም የእነ አቶ ማሙሸት አማረ ቡድንም ሆነ የእነ አቶ አሰፋ ሐብተወልድ/አብላጫው/ ስራ አስፈፃሚ በጉባኤ ተገኝቶ የታገደበትን እና የተከሰሰበትን ጉዳይ ለማስረዳት እና የመከላከል ሕገ መንግስታዊ መብቱ ሳይከበር ወደ ጉባኤው እንዳይገባ ተከልክሎ በጠቅላላ ጉባኤው እንድባረሩ ሲወሰን ጉባኤው የሁለቱም ቡድኖች ሐሳብ ለመስማት በጉባኤው ላይ እንድገኙ አለማድረጉ የመኢአድ ጠቅላላ ጉባኤ በኘሬዝዳንቱ ጫና ስር የወደቀ ለመሆኑ ሌላ ማስረጃ የሚያስፈልገው አይሆንም፡፡
በዚህ ጉባኤም የፖርቲው ኘሬዝዳንት ከኘሬዝዳንትነት ለቀው የፖርቲውን መተዳደሪያ ደንብ በማሻሻል የሌለ እና ያልተለመደ የፖርቲው የበላይ ጠበቂ የሚል አንቀጽ በመጨመር አቶ አበባው መሐሪ ኘሬዝዳንት በማድረግ ርሳቸው የበላይ ጠባቂ በመሆን ፖርቲውን ቤታቸው ሆነው ለመቆጣጠር ሪሞቱን አዘጋጁ፡፡
የዚህን ጠቅላላ ጉባኤ ውጤት እና አዲሱን የአመራር አመራረጥ ያልተቀበለው መሆኑን ቦርዱ ወዲያው ቢያሳውቅም ለአመት ያህል ይህ አመራር ፖርቲውን እያስተዳደረ ከቦርዱ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች የሚፃፃፋቸው ደብዳቤዎች እና የነበሩ የስራ ግንኙነቶች ሲታዩ ፖርቲው ሕጋዊ ሆኖ ቆይቷል ያሰኛል፡፡
ቀድሞ የተጀመረው የመኢአድ እና የአንድነት የውህደት ድርድር በእነ አቶ አበባው መሀሪ ስምምነት ላይ ሲደርስ እና ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ሲዘጋጁ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የቆየ ገመዱን ለመምዘዝ ሲቻኮል እና የሁለቱን ፖርቲዎች የውህደት ሂደት ለማደናቀፈ የተደረገውን ሴራ ሲታይ የገዢው ፖርቲ ቀጭን ትዕዛዝ የለም ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡
ይህን ተከትሎ ውህደቱን በመቃወም “መኢአድ ተሸጠ” በማለት በእነ አቶ ማሙሸት አማረ የተሰጠው መግለጫ ሲታይና የመኢአድ ከጥቅምት 28-29 የጠቅላላ ጉባኤ መጠራትና ወደ ፖርቲው ጽ/ቤት ኢንጅነር ኃይሉሻወል ሲገቡ በእነ አቶ ማሙሸት አማረ ታጅበውና ተደግፈው ወደ መድረኩ ሲወጡ ላየ ፖለቲከኛ የትናንቱ የጋዜጣ መዝለፍለፍና እስከ ፍ/ቤት የደረሰ መካሰስ በምን አይነት ሽማግሌ እርቅ እንደወረደ ግልጽ ባይሆንም ቀድሞ መኢአድ ተሸጠ ብለው በጋዜጣ መግለጫ ያወጡትን የእነ ማሙሸትን ቡድን ያስማማ የጋራ ፍላጎት አጀንዳ ሆኖ ከመታየቱም ሌላ የ3/ሶስተኛ/ እጅ ስላለመናሩስ በምን እንዳንጠራጠር ያደርጋል፡፡ የፖለቲካ መሄጃና መምጫው የማይታወቅ በመሆኑ የመኢአድን ከአንድነት ጋር መዋሀድ ከማይፈልጉት ኃይሎች ውስጥ ኢንጅነር ኃይሉና እነ ማመሸት ብሎም ኢህአዲግ በመሆናቸው ሶስቱን አካሎች ያስተሳሰራቸውን ድራማ እና ታሪክ ወደፊት እስከሚያመጣው ድረስ ለጊዜው መተው የተሻለ ይሆንና የጥቅምት 28-29 ጠቅላላ ጉባኤ ሂደትና ውጤት ላይ ማተኮርን እመርጣለሁ፡፡
ጥቅምት 28/2007 የፖርቲው ማዕከላዊ ም/ቤት ስብሰባ ስለነበር የጉባኤው አባላት /የም/ቤቱ ምዕለተ ጉባኤ በመሟላቱ ስብሰባውን ኢንጅነሩ እንዲመሩት ተደርጐ፡፡ የእነ አቶ ማሙሸት ቡድንና የእነ አቶ አሰፋ ሀብተወለድ ቡድን ታግዶ የቆየበትን አሰራር ፖርቲው በሪፖርት ከገለፀ በኋላ ም/ቤቱ እንዲወያይበትና የውሣኔ ሀሣብ በማሳለፍ በቀጣዩ ቀን 29/02/07 ለጠቅላላ ጉባኤ እንዲቀርብ በተጀመረው ውይይት መሰረት የም/ቤቱ አካሄድ ኢንጅነሩ የጠበቁት ባለመሆኑ እና እነ አቶ ማሙሸትን ለማባረር የተዘጋጀ በመምሰሉ በዚህ ሁኔታ ውይይቱን ማስቀጠሉ ለቀጣይ ቀን ለጠቅላላ ጉባኤው የሚቀርብ የውሣኔ ሀሳብ ላይ ደስተኛ ያልሆኑት ኢንጅነሩ በለመዱት ተጽኖ ፈጣሪነት ከሰዓቱ መምሸት አኳያ እንደምክናያት ተጠቅመው ይሔ አጀንዳ ለነገ ከጠቅላላ ጉባኤው ጋር ውሣኔ ይሰጥበት በማለት አካሄዱን ቀይረው በይደር አሳለፋት፡፡
አዳሩን የገባው የጠቅላላ ጉባኤ አባላት እነ ማሙሸት እንደመለሱ እንዲወሰን ቅስቀሳ /Lobbing/ ሲደረግ ያደረ ሲሆን በ29/03/07 የጠቅላላ ጉባኤው ምለዕተ ጉባኤ የተሟላ በመሆኑ የእነ አቶ ማሙሸት አጀንዳ ሲከፈት የጉባኤው አባላት 3 /ሶስት/ ሀሣቦችን አቅርቦ ነበር፡፡ እነዚህም
1. እነ አቶ ማሙሸት ከዲሲኘሊን ውጭ የተንቀሳቀሱ ስለሆነ ከፖርቲ አባልነታቸው ይባረሩ፡፡
2. ፖርቲው ካለበት ችግርና እነሱም ለፖርቲው ከሰጡት አገልግሎት አንፃር በይቅርታ ታልፈው በአባልነት ይቀጥሉ፡፡
3. ወደ አመራርነት ሳይመጡ በአባልነት ለ2 /ሁለት/ ዓመት ይቆዩ የሚሉ ሲሆን በአብዛኛው በ3ኛው ውሣኔ ላይ በመስማማት ጉባኤተኛው በጭብጨባ ያፀደቁት ሲሆን ኢንጂነሩ ጉባኤውን በለመዱት አካሄድ ውሳኔውን የሻሩት በተለመደው ተጽኖ ፈጠርነታቸውን በመድገም ወደ ፖርቲው መመላለሳቸውን ምክንያት በማድረግ የማዕከላዊ ም/ቤት አባል እንደሆኑ በማድረግ የተለመደ ጫናቸውን በጉባኤው ላይ ሲያሳርፉ አንዳንድ የጉባኤው አባላትም ሰብስበውን እየረገጡ የሄዱ ቢሆንም አብዛኛው ጉባኤትኛ ከዚህ በላይ መከራከሩና ኢንጅነሩን ማሸነፍ ያልተለመደ በመሆኑ በሳቸው ተጽኖ ስር ጉባኤው ወደቀ፡፡
ጥቅምት 30/2007 የጠቅላላ ጉባኤው አባላት የተበተነና ቀጣዩ ኘሮግራም የማዕከላዊ ም/ቤት አባላት ስብሰባ የስራ አስፈፃሚውን የስራ ምደባ ማድረግ ስለነበር ኢንጂነሩ አቶ ማሙሸት አማረን ኘሬዝዳንት አድርገው ስልጣናቸውን አውርሰዋል፡፡
እነ ማሙሸትም በአካባቢያቸው ተወላጆች ታጅበው አመራሩን ይዘው እንዲቀጥሉ ሊያስማማቸው የሚችለው አካል ማን ሲሆን ይችላል የሚለውን ጥያቄ በሂደት የምንመለሰው ቢሆንም የጉባኤው ውሳኔ በኢንጅነሩ ተሽሮ ፖርቲው በእነ ማሙሸት አማረ እጅ መግባቱ በርካታ አባላቱንና አመራሩን ከማስቆጣት አልፎ በዚህ አመራር ስር ላለመቀጠል እና ሌሎች አማራጮችን ለመውለድ የተዘጋጀውን ኃይል ስናየው የፖርቲውን የመጨረሻ የውድቀት ምዕራፍ ያስተናጋደ ታሪካዊ ሂደት ሆኖ መኢአድን እስካሁን ከገጠመው የመከፋፈልና የአባላት ድርቀት የዚህ ጉባኤ ውጤት ያመጣው ጣጣ የሶስተኛውን አካል ተሳትፎ ያጐላ በመሆኑ እስካሁን ለፖርቲው የተከፈለውን ዋጋ የሸጠ የኢንጁነር ኃይሉ አሳዛኙ ድራማ ሆኖ በታሪክ ይመዘገባል፡፡
(በጌታቸው ባያፈርስ)

No comments:

Post a Comment

wanted officials