ከጉራፈርዳ የተፈናቀሉ አብዛኞቹ አርሶ አደሮች ወደ ቀያቸው ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆኑም
ኀዳር ፭(አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጋምቤላና በደቡብ ክልል አዋሳኝ በሆነው በጉራ ፈርዳ ወረዳ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ከፍተኛ የሰው ህይወትና ንብረት ከወደመ በሁዋላ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣኖች ባለፉት ሁለት ቀናት የአካባቢውን አመራሮች በመሻርና በመሾም መረጋጋት እንደተፈጠረ በመግለጽ
ተፈናቃይ አርሶደሮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማግባባት ቢሞክሩም፣ አብዛኞቹ አርሶአደሮች ግን ለህይወታችን ዋስትና የሚሰጠን ስለማይኖር ወደ አካባቢው ለመመለስ ፈቃደኞች አይደለንም ብለዋል። በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በየጫካው ባሉበት ሁኔታ የእኛ መመለስ ለህይወታችን
ዋስትና የሚሰጥ ባለመሆኑ አንመለስም በማለት እየተቃወሙ ነው። 12 የፌደራል ፖሊሶችን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ በመምራት አስገድሏል የተባለ የወረዳው የጸጥታ ሹም ተይዞ ወደ አዲስ አበባ ተወስዷል። ሌሎች ሁለት ባለስልጣናትም ወደ ማእከላዊ ተወስደዋል። እጃቸው አለበት የተባሉት ባለስልጣናት ሁሉም
የኢህአዴግ አባሎች ናቸው። በአካባቢው የሚታየው አለመረጋጋት እንደቀጠለ ሲሆን፣ መጠናኛ ቁጥር ያላቸው የሰራዊት አባላትም በአካባቢው ሰፍረው ይገኛሉ። በጉራፈርዳ ወረዳ በተነሳው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት ማለፉ መዘገቡ ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment