ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለዋል
በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቄራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አየር ጤና አካባቢ አንዲት የአሥረኛ ክፍል ተማሪ በተሳፈረችበት ታክሲ ታፍና ከተወሰደች በኋላ በደረሰባት አስገድዶ መደፈር ጉዳት ሕይወቷ ማለፉን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
ሟቿ ተማሪ ሃና ላላንጎ ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. አየር ጤና በተለምዶ ሳሚ ካፌ በሚባለው አካባቢ በአንድ ሚኒባስ ውስጥ ተሳፍራ ወደ ጦር ኃይሎች እየመጣች እንደነበር ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ ከትምህርት ቤት ወጥታ ወደ ቤተሰቦቿ በመጓዝ ላይ የነበረችው ሟች ተማሪ የተወሰነ ርቀት ከተጓዘች በኋላ መድረሷን ተናግራ ‹‹ወራጅ አለ›› ስትል፣ በሚኒባሱ ውስጥ የነበሩ አራት ወንዶችና ሾፌሩ ስለት በማውጣት አስፈራርተው እንዳገቷትም ተጠቁሟል፡፡
ሟች እንዳትናገር በማድረግ በሰዋራ ቦታ በታክሲው ውስጥ እንድታመሽ ከተደረገች በኋላ፣ ከተጠርጣሪዎቹ አንደኛው ቤት ወስደው ለአምስት እየተፈራረቁ እንደደፈሯት ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡
አንደኛው ተጠርጣሪ በራሱ ቤት ውስጥ እንድትቆይ በማድረግ ለተከታታይ አምስት ቀናት ሲደፍራት እንደከረመም ምንጮቹ አክለዋል፡፡ ሁለተኛ ተጠርጣሪ ነው የተባለው ግለሰብ ለአምስት ቀናት በተደጋጋሚ ሲደፍራት ከከረመ በኋላ፣ ከቤት አውጥቶ ጭር ባለ ቦታ ጥሏት መገኘቷንም ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ ሟች ከፍተኛ የሆነ የማሕፀንና የፊንጢጣ ጉዳት አጋጥሟት ስለነበር በተለያዩ ሆስፒታሎች ሕክምና ያደረገች ቢሆንም፣ በደረሰባት ከባድ ጉዳት በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል በመታከም ላይ እያለች ሕይወቷ ማለፉን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ሟች በመሀል በአንደኛው ተጠርጣሪ ስልክ ወደ ቅርብ ጓደኛዋ በመደወል ስልኩን በመዝጋቷ ጓደኛዋ የደወለችበትን ስልክ ለቤተሰቦቿ ትሰጣለች፡፡ የሟች ቤተሰቦች የሞባይሉን ቁጥር ለፖሊስ አሳልፈው በመስጠታቸው ፖሊስ ባደረገው ከፍተኛ የክትትል ሥራ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት ቀርበው በወንጀል መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 35 መሠረት የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውንም ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፦ ሪፖርተር
No comments:
Post a Comment