Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, November 13, 2014

ኢህአዴግ በምርጫው ማግስት በዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞ እንዳይነሳ የመከላከያ ሰነድ አወጣ

ኢህአዴግ በምርጫው ማግስት በዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞ እንዳይነሳ የመከላከያ ሰነድ አወጣ
 
“የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኢህአዴግ የምርጫ ድል የልማት ሰራዊት ግንባታ አደረጃጀት ማንዋል ለምርጫ 2007″ በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ሰነድ በጥቅምት ወር በአዋሳ እንዲቀርብ ተብሎ የተዘጋጀ ቢሆንም፣ የሰነዱ ጥራት የወረደና በሰነዱ የተካተቱት ነጥቦች ከልማት ሰራዊቱ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ መጠቀሙን አያረጋግጥም በሚል በኢህአዴግ ጽ/ቤት በመተቸቱ እንዲሻሻል ከተደረገ በሁዋላ እንደገና ህዳር 1 ቀን 2007 ዓ.ም የኢህአዴግ አመራሮች እንዲወያዩበት ተደርጓል።
የተዘጋጀው ሰነድ “የኢህአዴግን ምርጫ ውጤታማነት እንዲያመች ተብሎ ተሻሽሎ መቅረቡን እንዲሁም የብጥብጥ እና የሁከት መንስኤ የሆነውን ተማሪ በኢህአዴግ አመራር አባላት እየታገዘ መያዝ የሚያስችል ” መሆኑ በመግቢያው ላይ ሰፍሯል።
“በምርጫው ሊፈጠር የሚችለውን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁከት እና ብጥብጥ ለማስቆም ተማሪዎችን በማደራጀት መረጃ ለመጥለፍ አመችነቱ የላቀ እንደሚሆን ታምኖበታል” በማለት የሚያትተው ሰነዱ፣ ” የልማት ሰራዊት ግንባታን ወይም የፖለቲካ ሰራዊት ግንባታ በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ በማቀጣጠልና በማስቀጠል ተቋማዊ ለዉጡን እውን በማድረግ የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ፤ ምርጫ 2007 ትንም ውጤታማ ለማድረግ እና የኢህአዴግን አሸናፉነት ለማረጋገጥ ” እንደሚያግዝ ይገልጻል።
“የከፌተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ልማት ሠራዊት ግንባታ ምንነት፤ አስፈላጊነትና ፋይዳ›› በሚለው ርዕስ ስር ደግሞ “ተማሪዎች በኢህአዴግ ላይ ያላቸው አቋም የወረደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በማንኛውም የተቃውሞ ድምፅ ከተጠሩ ሰልፍ የሚያደምቁ ፣ ተቃውሞን ከግብ ለማድረስ ሁነኛ መሳሪያ ናቸው፡፡ ” ሲል ይፈርጃቸዋል።
በማያያዝም ” ተማሪዎች በየትኛውም ሐገር እንደታየው አደባባይን የመያዝ፣ ህዝብን አስተባብረው በተቃውሞ የማሳደም እድላቸው የሰፋ በመሆኑ ፣ ከዚህም ሲያልፍ ፤ የኢህአዴግ ምከታን በመቃወም ለጠላት ጎራ ተሰልፈው የመታጠቅ እድላቸው ከፍተኛ ነው” ሲል ይገልጻቸዋል።
ስለዚህም ይላል ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሰነድ የከፍተኛ ትምህርት የልማት ሰራዊት በማደራጀትና በመገንባት ማሰማራት የግድ ይላል።
ሰነዱ አክሎም “በተለይም በዚህ ስዓት የምርጫ ፈተና ላይ የጣለን የምርጫ ጉዳይ ፣ እንደምናሸነፍ ቃል የተያዘበት ቢሆንም፤ ፈተናዎች የሚፈጠሩት በህዝብ እና በራሱ ታማኝ ባልሆኑ ሃይሎች ማለትም በመንግስት ክንፍ በመሆኑ የኢህአዴግ አይሸነፍም የሚለው ቃል አይቀለበስም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡” ሲል የኢህአዴግን ፍርሃትና ጥርጣሬ ያመላክታል።
የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች “የአመፅ እና የብጥብጥ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ሃይሎች መሆናቸውን በአክራሪዎች ሲጠለፉ፤ ከመንግስት ይልቅ ሃይማኖታቸውን እየመረጡ በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ፤ በጅማ ዩኒቨርስቲ ፤ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ እና በሌሎችም የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ትተው ሲኮበልሉ ተመልክተናል ብሎአል።
“እስካሁን በዩኒቨርስቲዎች ከተተገበሩት የልማት ሰራዊት እንቅስቃሴ የምንረዳው የከፍተኛ የትምህርት ተቋም አንድን ምዕራፍ በአግባቡ ሳያከናውን ወደሚቀጥለው የግንባታ ምዕራፍ ቢሸጋገር የትምህርት ልማት ሠራዊቱ በተሟላ ሁኔታ ወይም የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ሊወጣ የሚችል ሰራዊት ተገንብቷል ማለት አለመቻሉን በመሆኑ ሁሉም የሰራዊቱ ክንፎች በሙሉ በምርጫው ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ፣ ተገቢውን አደረጃጀትና አሰራር ዘርግቶ ለመካከለኛው አመራር፣ ለዝቅተኛ አመራር፣ ለመምህራን፣ ለምርምር አካላት፣ ለድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችና ተማሪዎች ግልጽ ስምሪት መስጠት፣ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እያንዳንዱን የሰራዊት ክንፍ ወደሚፈለግበት የጥንካሬ ደረጃ እየደረሰ መሆኑንና የተቋሙ እቅድ በውጤታማነት መፈጸሙን ማረጋገጥ አለበት” ሲል ሰነዱ መመሪያ ያስተላልፋል።
ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት የሚመሰረተው በኢህዴግ መሪ ድርጅትነት ብቻ ነው የሚለው ሰነዱ ቀጣዩ ስኬት በኢህአዴግ መሪ ድርጅት ቀጣይነት ላይ የተመሰረተ ነው ብሎአል፡፡
በመንግስት እና በከፍተኛ ተቋማት በሚገነቡ የሰራዊት ክንፎች መካከል ስለሚኖረው አሰራርና አደረጃጀት ቀጣይ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ከኢህአዴግ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials