የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እስር ያሳስበኛል ብሏል
በኢትዮጵያ ሃሳባቸውን በነፃ የመግለፅ መብታቸውን በመጠቀማቸው ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞች ከእስር እንዲፈቱ ሰሞኑን የአሜሪካ መንግስት ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የተፈረደበት የሶስት ዓመት እስር በእጅጉ ያሳስበኛል አለ። የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ሃሳብን በነፃ የመግለፅና የፕሬስ ነፃነት የዲሞክራሲ አንኳር እሴቶች መሆናቸውን በመጠቆም፤ ዲሞክራሲያዊ ነኝ የሚል መንግስት ይህን መብት የማስከበር ኃላፊነት አለበት ብሏል።
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገትና አፍሪካ ውስጥ ግጭቶችን ለመፍታት የምታካሂደው ጥረት በአርአያነት እንደሚጠቀስ መግለጫው አውስቶ፤ ይህንንም በመስከረም ወር ፕሬዚዳንት ኦባማ ከጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በተወያዩበት ወቅት በይፋ መናገራቸውን አስታውሷል። በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የታሰሩ ጋዜጠኞችን በመፍታት፣ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብትንና የፕሬስ ነፃነትን የሚያስከብር አርአያነት እንዲያሳይ የአሜሪካ መንግስት ጠይቋል።
የ «ፋክት» መፅሄት አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ የ«ፍትህ» ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረ ጊዜ በተለያዩ ህትመቶችና ባወጣቸው ፅሁፎች «ህዝብን ለአመፅ አነሳስተሃል፤ ሃሰተኛ ወሬዎችን አሰራጭተሃል» በሚል በርካታ ክሶች እንደቀረቡበት የሚታወስ ሲሆን፤ ሰሞኑን የ3 ዓመት እስር የ10ሺህ ብር ቅጣት ተወስኖበታል። ጋዜጠኛው በጠበቃው አማካይነት ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።
ከስድስት ወር በፊት አንድ ላይ የታሰሩ ዘጠኝ ጋዜጠኞችና የኢንተርኔት ፀሐፊዎችን ጨምሮ፤ ኢትዮጵያ በአለም ደረጃ በርካታ ጋዜጠኞችን ለእስርና ለስደት በመዳረግ ተጠቃሽ ሆናለች በማለት አለማቀፍ የሰብአዊ መብትና የፕሬስ ነፃነት ተቋማት በተደጋጋሚ መንግስትን ይኮንናሉ። በጋዜጠኛነት ሙያው የታሰረና የተሰደደ ጋዜጠኛ እንደሌለ የሚናገረው መንግስት በበኩሉ፤ ጋዜጠኞች የታሰሩት የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል በሚል እንደሆነና ጉዳያቸው በፍ/ቤት ውሳኔ እንደሚያገኝ ይገልፃል።
No comments:
Post a Comment