በምእራብ አርማጭሆና በመተማ የአንድነት ፓርቲ አደራጆች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ታፍነው ተወሰዱ
ጥቅምት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአዲስ አበባ የተላኩ የፌደራል ፖሊስ አባላትና ደህንነቶች፣ ወደ ፓርቲው መሪዎች ቤት ከንጋቱ አስራ አንድ ሰአት ላይ በመሄድ፣ መኖሪያ ቤቶቻቸውን ሰብረው በመግባትና አንዳንዶችንም ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በመደብደብ አፍነው ወዳልታወቀ ቦታ ወስደዋቸዋል።
የመተማ ወረዳ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ በላይነህ ሲሳይ፣ የምእራብ አርማጭሆ ወረዳ ሰብሳቢ አቶ አንጋው ተገኝ እንዲሁም የስራ አስፈጻሚ አባላት የሆኑት አባይ ዘውዱና እንግዳው ዋኘው ከተያዙት መካከል ይገኙበታል። የአቶ በላይነህ ቤት ከሌሊቱ 9 ሰአት የተከበበ ሲሆን፣ አቶ በላይ ሳይነጋ ቤቴን አልከፍትም በማለት፣ ከንጋቱ 11 ሰአት ላይ ቤቱን ሰብረው ገብተው ወስደውታል። ቤተሰቡ በፌደራል ወታደሮች ድርጊት በእጅጉ ተዳንገጠዋል።
ከንጋቱ 11 ሰአት ሲሆን በአብራጅራ የአንድነት ፓርቲ አመራር በሀነው በአቶ አንጋው ተገኝ ቤት የተገኙት የፌደራል ፖሊሶች፣ ቤቱን እንዲከፍት ሲጠይቁ፣ እስኪነጋ እንዲታገሱት ቢጠይቅም፣ ወታደሮቹ በሩን ሰብረው በመግባት ክፉኛ ደብድበው ወስደውታል። አቶ አንጋው ክፉኛ በመደብደቡ ወታደሮች አንስተው መኪና ላይ እንደጫኑት የአይን እማኞች ገልጸዋል።
ወጣት አባይ ዘውዱን ሊይዙ የሄዱት ፖሊሶች ከቤተሰቦቻቸው በደረሰባቸው ተቃውሞ ውዝግብ ፈጥረው የቆዩ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ግን በሃይል መውሰዳቸውን ቤተሰቦች ተናግረዋል።
ለቤተሰቡ ብቸኛ የሆነውንና ከዚህ ቀደም ስራ በመከልከልና በእስራት ከፍተኛ እንግልት ሲደርስበት የነበረውን ወጣት አባይን ላለማስወሰድ ሲማጓቱ የነበሩ ሁለት እህቶቹ በሰደፍ በመመታታቸው በአሁኑ ጊዜ ጤና ጣቢያ ውስጥ መተኛታቸውን ቤተሰቦች ገልጸዋል። አንደኛዋ ጡቷ ስር በሰደፍ ስትመታ ሌላኛዋም ተመሳሳይ ጉዳት ደርሶባት ፈሳሽ ምግብ ወይም ግሉኮስ ተተክሎላት ህክምና እየተደረገላት ነው። በአካባቢው ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ሶስቱ የፓርቲው አመራሮች በተያዙበት ወቅት ነዋሪው ተቃውሞ በማሰማት ውሳኔውን ለማስቀልበስ ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል። ይሁን እንጅ ድርጊቱ የህዝብ ቁጣ መቀስቀሱን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
አቶ አንጋው ተገኝ ከዚህ በፊት በከፍተኛ ሁኔታ ተደብድቦ ታስሮ መፈታቱ ይታወቃል። አባይ ዘውዱም ኤርትራ ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር ትገናኛለህ በሚል ከወር በፊት በመከላከያ አባላት ተይዞ በህዝብ ተቃውሞ እንዲፈታ መደረጉ ይታወቃል። ሁለቱም መሪዎች ስለሚደርስባቸው እንግልት በቅርቡ ለኢሳት ቃለምልልስ መስጠታቸው ይታወቃል።
ገዢው ፓርቲ የሃይል አፈናውን አጠናክሮ መቀጠሉን የሰሜን ጎንደር አንድነት ፓርቲ የአመራር አካል የሆኑት አቶ ሙላት ፍሰሃ ተናግረዋል በደቡብ ጎንደር ደግሞ የፎገራ ወረዳ የአንድነት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አለበል ዘለቀ ከሚሰሩበት የእርሻ ቦታቸው ላይ በፌዴራል በፖሊስ ተይዘው ወዳልታወቀ ቦታ ሲወሰዱ፣ በምዕ/ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ የወረዳው ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን አበበና 3 የአንድነት አባላት ከቤታቸው በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደዋል።
ከትናንት በስቲያ ደግሞ የምእራብ ጎጃም የመኢአድ ዋና ጸሃፊ አቶ ጌታቸው መኮንንና የፓርቲው ዋና ጸሃፊ የነበሩት አቶ ተስፋየ ታሪኩ ተይዘው መታሰራቸው መዘገቡ ይታወቃል። የወላይታ ዞን የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ማሞ ገሞ እና የዞኑ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ወኖ በዳሳ ጥቅምት 22 ቀን 2007 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ከተማ በአንድ ሆቴል ውስጥ እያሉ በከተማው የፖሊስ አዛዥ መመሪያ በመንግስት ሀይሎች ከባድ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ለፍኖተ ነፃነት መናገራቸው መዘገቡ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment