ለአቶ ዛይድ መነሳት ምክንያት የሆነው ጉዳይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ላይ ባይተነተንም፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባቀረበው ጥያቄ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔውን እንዳሳለፈ ደብዳቤው አትቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ሪፖርት ያቀርባል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየው የመንገድ ባለሥልጣን ቦርድም ሰብሳቢ ናቸው፡፡
ሰሞኑን አቶ ዛይድና አቶ ወርቅነህን የማያግቧቧቸው ነገሮች እየተካረሩ መምጣታቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ አቶ ወርቅነህ የደረሱበት ድምዳሜ ለረዥም ጊዜ የሠሩትን አቶ ዛይድ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በላይ በጥልቀት በመሄድ ሁለቱን ባለሥልጣናት ያላግባባው፣ በቅርቡ ለቻይና ኩባንያዎች የተሰጡ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንደሆኑ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ኩባንያዎቹ ከዚህ ቀደም የወሰዱትን የመንገድ ፕሮጀክት ሳያጠናቅቁ ተጨማሪ ሥራ ሊሰጣቸው አይገባም በሚሉ ሐሳቦች ላይ አቶ ወርቅነህና አቶ ዛይድ መግባባት አለመቻላቸው ተጠቅሷል፡፡
አቶ ዛይድ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንን በዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡ ከአቶ ዛይድ በትምህርታቸው ትራንስፖርት ኢኮኖሚስት ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ መንገድ ልማት ዘርፍ ብዙ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይነገርላቸዋል፡፡ አቶ ዛይድ ባለሥልጣኑን በተለያዩ ደረጃዎች በኃላፊነት ማገልገላቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡
ከባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ትልቁ የበጀት ተጠቃሚ የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የተለያዩ የመንገድ፣ የድልድይ ግንባታዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ አቶ ዛይድ ከተነሱ በኋላ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጊዜ ቦታቸው ላይ ሰው አልተሾመም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ዛይድ አስተያየት እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2007 በጀት ዓመት ግንባታቸውን ለማስጀመር በዕቅድ ከያዛቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ሰባቱን ከሳምንታት በፊት ለአገር ውስጥና ለውጭ ኮንትራክተሮች መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ሰባት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አምስቱ ለውጭ ተቋራጮች ሲሰጡ፣ አራቱን የቻይና ኩባንያዎች መውሰዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ምንጭ:- ሪፖርተር
No comments:
Post a Comment