Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, March 22, 2015

ጋዜጠኛ ተመስገን በማረሚያ ቤት ህክምና መከልከሉ ተነገረ


ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ: በእስር በሚገኝበት የዝዋይ ማረሚያ ቤት: በጤና አገልግሎት እጦት እንደተቸገረ ሲፒጄ አስታወቀ. የጋዜጠኞች የመብት ተቆርቋሪው ቡድን ሲፒጄ : ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ከሆነ: ጋዜጠኛ ተመስገን በማረሚያ ቤት የጤና አገልግሎት እንዳያገኝ ስለተከለከለ: በሆድና በወገብ ህመም እየተሰቃየ እንደሆነ አመልክቷል.
ጥቅምት ላይ የሶስት አመታት እስር ተፈርዶበት: በዝዋይ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ተመስገን ደሳለኝ :ከመታሰሩ ቀደም ብሎ በየሳምንቱ የህክምና ክትትል ያደርግ እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን: አሁን ግን በእስር ቤቱ ባለስልጣናት: የህክምና አገልግሎት በመከልከሉ የተነሳ :በተለይ የጀርባ ህመሙ በመባባሱ: መሄድ እስከሚያቅተው እንደተቸገረ የሲፒጄ መግለጫ ይዘረዝራል.
የቀድሞው የፍትህ ጋዜጣ ባለቤት የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ: አመጽን የሚያነሳሱ የሀሰት ወሬዎችን በመጻፍ: እንዲሁም የሰዎችን መልካም ስም በማጉደፍ በሚሉ ወንጀሎች ተከሶ :የሶስት አመታት እስራት እንደተፈረደበት ይታወቃል.
ይሁን እንጂ የክሱን መዝገብ በሚገባ መገምገሙንና :ማጥናቱን የሚናገረው ሲፒጄ :ተመስገን ለእስር የተዳረገው :የተባሉትን ወንጀሎች ሰርቶ ሳይሆን :በሚያወጣቸው ጽሁፎች መንግስትን ደጋግሞ በመተቸቱ ነው ሲል: መንግስትን ይከሳል. እስር ቤት ከገባም በኋላ: የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ: አንድ ጽሁፍ ከዛው ሆኖ በመጻፉና በተለያዩ ሚዲያዎች በመታተሙ የተነሳ :በማረሚያው ባለስልጣናት ማንም ዘመድ ወዳጅና ቤተሰብ እንዳይጎበኘው ለወራት ተከልክሎ መቆየቱን ሲፒጄ :ይናገራል.
ድርጅቱ ማረሚያ ቤቱ በተመስገን ላይ የሚፈጽመውን የመብት ጥሰት ለማስቆም: ለኢፌድሪ ፍትህ ሚኒስቴር እንዲሁም አሜሪካ ላለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ :በተደጋጋሚ ጊዜ በስልክና በኢሜል ጥያቄ ማቅረቡን ጠቅሶ :ይሁን እንጂ ከመንግስት በኩል ምንም አይነት ምላሽ እንዳልተሰጠው ተናግሯል.
በሀገሪቱ የጋዜጠኞች ይዞታ ላይ የራሱን ጥናት እንዳደረገ የሚገልጸው ሲፒጄ :መንግስት 17 ጋዜጠኞችን ማሰሩንና: ከ 30 የማያንሱ ደግሞ መሰደዳቸውን ይናገራል. የኢትዮጵያ መንግስት: ተቋሙ የሚያወጣቸውን ሪፖርቶችና ማሳሰቢያዎች ወደጎን በማለት: ይህን ጋዜጠኞችን የማፈን ተግባሩን እንደገፋበት የሚገልጸው ድርጅቱ :በተለይ ከመጪው የግንቦት ምርጫ በፊት : ብዙሀኑን ነጻ ሚዲያና ጋዜጠኞች የማፈን ተግባሩን ቀጥሎበታል ሲል መንግስትን ከሷል.

No comments:

Post a Comment

wanted officials