Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, March 4, 2015

ለቅስቀሳ የተሰማሩ የሰማያዊ አባላቶቹ እየታሰሩ ነው።ግርማ ካሳ








የአንድነት አባላትን ያካተተው የሰማያዊ ፓርቲ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ትራክቶችን በማሰራጨት ቅስቀሳ ዛሬ ጀምሯል። ለቅስቀሳ የተሰማሩ አባላቶቹ እየታሰሩ ነው። ያ ብቻ አይደለም። በቴሌቭዥን ክርክር እነ ዶር በየነና ሌሎች ሲቀርቡ፣ የሰማያዊ ፓርቲ እንዲቀርብ አልተደረገም።

በራዲዮ የቅስቀሳ መልእክቶቻቸዉን ተወዳዳሪ ፓርቲዎች እንዲያቀርቡ በተጠየቀው መሰረት፣ የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ ኦዲዮ አዘጋጅቶ ቢልክም ፣ «ይሄ ካልተስተካከለ፣ ይሄን ካላወጣችሁ፣ ሙዚቃ ማድረግ አትችሉም ..» እያሉ አንቀበልም ብለዋቸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ በአቶ አበባው የሚመራው መኢአድም ያቀረበው ቅስቀሳ ዉድቅ ተደርጎበታል። ሕወሃቶች አንደኛዉኑ ለምን ኦዲዮ ለድርጅቶች አዘጋጅተው በነርሱ ስም ቢያወጡላቸው ሳይሻል አይቀርም። ፡)፡)


ያም ሆነ ይህ፣ ሰማያዊዎች እያደረጉት ላለው አኩሩ ሥራ አድናቆቴን እገልጻለሁ። ያልተሸራረፈ ድጋፌ ለነርሱ ነው። አሁን ትልቅ ዱላ እየቀመሱ ነው። ግን ዱላ በቀመሱ ቁጥር አገዛዙ መክሰረኡን፣ በሐሳብ መሸነፉን እግልጽ የሚያሳይ ነው። እያሸነፉ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው። በትራክቱ ላይ ያሉቱን መልእክቶች ራሱ ማንበቡ የሚያረካ ነው።
አንዳንዶች ከምርጫው ዉጡ እያሏቸው ነው። ይገባኛል ለምን እንደዚያ እንደሚሉ። ግን ለምንድን ነው የሚወጡት ? እስከ መጨረሻዉ መቀጠል አለባቸው ባይ ነኝ። ከምርጫ በመውጣት የሚገኝ ጥቅም የለም። እነርሱ ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው። ይኸው በየቦታው የመብት ጥያቄን ያነሱ ወረቀቶችን እያደሉ ነው። ያ ራሱ ትልቅ የፖለቲክ ሥራ ነው። ምርጫ ላይ አንድ የፓርላማ መቀመጫ 5፣ 10 መቀመጫ ካገኙም፣ 5፣ 10 ግርማ ሰይፉዎች ተገኙ ማለት ነው። ቢያንስ ቢያንስ ሌላው ቢቀር በፓርላማ ትንሽም ብትሆን የሕዝብን ስሜት ማንጸባረቅ ይቻላል።
ለአገዛዙ ሌጂቲማሲ መስጠት ነው የሚል መከራከሪያ ነው አንዳንዶች የሚያቀርቡት። ወገኖቼ አንደኛ አገዛዙ ሌጂቲማሲ ካጣ ቆይቷል። አንድነትን አግዶ፣ የፖለቲካ መሪዎችን አስሮ፣ ጋዜጦችን ዘግቶ ምርጫ አድርጌ አሸነፍኩ በማለቱ ነው ሌጂቲማሲ የሚያገኘው ? ሌጂቲማሲ ብሎ ነገር የለም። ቅንጣት ሊጂቲማሲ የለውም። አገዛዙ እየገዛ ያለው በኋይል ነው። አራት ነጥብ።

የዉጭ አገር መንግስታት ካሰብን ደግሞ፣ አንሳሳት፣ ሕወሃቶች 99.6% አሸነፍን ሲሏቸው ፊት አልነፈጓቸውም። እነርሱ ጥቅማቸዉን የሚያስከብር እንጂ የለየለት ወትያደራኢ ጁንታ ቢመራ ግድ አይሰጣቸውም።የፒኖቼ፣ የሞቡቱ፣ የሙባረክ፣ የሳዳም ሁሴን ሁሉ ሳይቀር ወዳጆች እንደነበረ አንርሳ።
በመሆኑም ሰማያዊም ሆነ ሌሎች ሂሳባቸዉን ማስላት ያለባቸው የድርጅታቸውን ጥቅምና ጉልበት ከማሳደግ አንጻር እንጂ በሌላ መሆን የለበትም። ምርጫ አለመግባቱ ይጠቅመናል ካሉ አይግቡ። ግን በኔ ግምት መግባቱ ካለመግባቱ የበለጠ ይጠቅማል።

ሕጋዊ ያልሆነ የእምቢተኝነት ትግል መደረግ አለበት የሚል አቋም አንዳንዶች ይኖረቸዋል። እኔም ይሄ አቋም አለኝ። ሌሎች ደግሞ የትጥቅ ትግል ይላሉ። መረሳት የሌለበት ግን አገር ቤት የሚደረገዉ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈታኝና ትዕግስት አስጨራሽ ቢሆንም፣ ሌሎች ትግሎችን እንዳይደረጉ መሰናክል የሆነበት ሁኔታ የለም። የሚዋጋ ይዋጋ፣ በስዉር ሰላማዊ የእምብተኝነት ዘመቻ የሚያደርጉ በዚያ ላይ ይበርቱ። በሮቹ ቢዘጋጉም፣ ቁጭ ከማለት ትግሉን እንቀጥላለን የሚሉ ደግሞ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ይቀጥሉ። እኔ ሰላማዊና ሕጋዊው ትግል ጣራ ላይ ደርሷል ወደ ምእራፍ ሁለት መሄድ ያስፈልጋል የሚል ሐሳብ ቢኖረኝም፣ በቦታዉና በአገር ቤት ያሉ ታጋዮች፣ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ገና የሚሰራ አሉ ካሉ፣ የምደሰትበት ነው።

እግዲህ የምለው፣ ሁሉም በሚያምንበት ይሰማራ። ሁሉም እርሱ ማድረግ ያለበት ላይ ያተኩር። ይሄ አይሰራም፣ ይሄ ይሰራል መባባሉ ጥሩ አይመስለኝም። “ከነርሱ የኛ ይሻላል” ፖለቲካ ከፋፋይ ፖለቲካ ነው። ወደ አላስፈላጊ ዉዝግብ ውስጥ ይከተናል። በተቻለ መጠን የትጥቅ ትግል እንመራለን የሚሉ ቡድኖች፣ በምርጫዉ ረገድ ሆነ በሌሎች ጉዳዮች የሰላማዊ ታጋዮች በሚያደርጉት ላይ “እኛም ሞክረነው ነበር፡ አይሰራም ወዘተረፈ ..” የሚል አሉታዊ አስተያየት ባይሰጡ ጥሩ ነው። ለምን የነርሱንም የትግል ዉጤት መመርመር ከተጀመረ ስለ እነርሱም ብዙ መናገር ስለሚቻል።
ለሰማያዊዎች በድጋሚ ድጋፌን እየገለጽኩ፣ ኢትዮጵያዉይን በዚህ ወሳኝ ወቅት ከሁሉም አቅጣቸው አጋርነታችንን ከመቼዉም ጊዜ በበለጠ እንድናሳይ እጠይቃለሁ።ግርማ ካሳ
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

No comments:

Post a Comment

wanted officials