ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የተሰራጨው ሰንደቅ ጋዜጣ “ራሱን የእስላማዊ መንግስት ነኝ እያለ የሚጠራውና በሚፈጽማቸው አሰቃቂና ዘግናኝ ወንጀሎቹ ዓለምን እያሸበረ የሚገኘው ጽንፈኛ ቡድን የአይ ኤስ ኤስ ዋነኛ አራጅ ነው የተባለው ጆን የቅርብ ጓደኛ ትውልደ ኢትዮጵያ ነው መባሉ እያነጋገረ ነው” ሲል ዘገበ::
የነፉሰ ገዳዩን ጆንን ታሪክ ወደኋላ ሄደው ሲመዙ የከረሙት የዓለም መገናኛ ብዙሃን በሳለፉነው ሳምንት ጆን ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚያገናኘው አጋጣሚ እንዳለ ይፋ አድርገዋል። በጆን ታሪክ ላይ ምርመራ ሲያደርግ የቆየው ሜል ኦንላይን እንደዘገበው ከሆነ ጆን፣ ትውልዱ ከኢትዮጵያ ከሚመዘዝና አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ በእስር ላይ ከሚገኝ ሰው ጋር በአንድ ወቅት ጥብቅ ጓደኝነት መስርቶ እንደነበር ይፋ አድርጓል ያለው ጋዜጣው ሙሐመድ ሙአዚ እየተባለ ሲጠራ የቆየው ጂሀዲስቱ ጆን የኋላ የኋላ ግን ትውልዱ ከኩዌት የሚመዘዝ እንግሊዛዊ መሆኑ ባለፈው ሳምንት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ከሰባት ያላነሱ ሰዎችን አንገት በቪዲዮ ሲቀጥፍ የታየው ጆን በብሪታኒያ ለንደን ከተማ ያደገና ኮሌጅ ገብቶ የተማረ ሲሆን፤ ቤተሰቡ አሁንም በዛው ይኖራል ነው የተባለው። እ.ኤ.አ. በ2012 ወደ ሶርያ ሄዶ አይ ኤስ አይ ኤስን ከተቀላቀለ በኋላ ጂሀዲስቱ ሙአዚ የሚል መጠሪያን ይዞ ጭምብል አጥልቆ የታገቱ ሰዎችን ሲያርድና ሲገድል መክረሙም ተዘግቧል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ነፍስ ገዳዩ ጆን ከኢትዮጵያ ጋር ስሙ መነሳቱን እንዴት ይመለከቱታል ሲል ለኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ለአቶ እውነቱ ብላታ ጥያቄ ያቀረበው ሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት ምላሽም “የአክራሪ የእስልምና እምነት ተከታይ ኃይሎች ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ስጋቶች መሆናቸውን ከለየን እና ተገቢውንም የመከላከል ስራዎች መስራት ከጀመር ቆይተናል። ዛሬ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን የፅንፈኛው ጆን ጓደኛ ትውልደ ኢትዮጵያ ነው የሚል ዜና ይዘው ብቅ ቢሉም እኛ አደጋውን ከተረዳን የቆየን በመሆኑ ብዙም አያደናግጠንም። እንደአንድ ግብአት ግን ልጠቀምበት እንችላለን” ብለዋል ሲል ዘግቧል:: ሚኒስትር ደኤታው ስለዚህ ሰው ኢትዮጵያ መታሰር ማረጋገጫ የሰጡት ነገር የለም::
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/39634#sthash.PQ9VwKDe.dpuf
No comments:
Post a Comment