Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, March 9, 2015

ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹ኢህአዴግ›› በሚል ስም የተመዘገቡ ሁሉም ዕጩዎች እንዲሰረዙ ጠየቀ

ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹ኢህአዴግ›› በሚል ስም የተመዘገቡ ሁሉም ዕጩዎች እንዲሰረዙ ጠየቀ


በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹ኢህአዴግ›› የሚል ውህድ ፓርቲ እንዳለ ተደርጎ በህግ ጥሰት በስሙ የተመዘገቡ ሁሉም ዕጩዎች እንዲሰረዙ ምርጫ ቦርድን ጠየቀ፡፡ ፓርቲው ዛሬ የካቲት 30/2007 ዓ.ም ለምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምግዝባ አዋጅ ‹‹'ግንባር' ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናጠል ህጋዊ ህልውናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ የሆነ ስያሜ፣ የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ኖሯቸው ለመንቀሳቀስ ሲወስኑ የሚደራጅ አካል ነው፡፡›› እንደሚል ገልፆ፣ ግንባር የሆነው ኢህአዴግ እንደ ውህድ ፓርቲ ተቆጥሮ በስሙ ዕጩዎች መመዝገባቸው ህገ ወጥ ነው ብሏል፡፡


ፓርቲው በላከው ደብዳቤ ‹‹በአዋጁ እንደተደነገገውም ኢህአዴግ አራት ህልውና ያላቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የመሰረቱት ግንባር እንጂ ፓርቲ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ አባል የለውም፡፡ በእርሱ ስም ግለሰብ ዕጩዎች ሊወዳደሩም ሆነ ሊመረጡም አይችሉም፡፡›› ሲል በኢህአዴግ ስም ዕጩዎች መመዝገባቸውን ህገ ወጥ ነው ብሏል፡፡

ፓርቲው አክሎም ‹‹የግንባሩ ዕጩዎች በሁሉም የአዲስ አበባ ምርጫ ክልሎች የየትኛው አባል ፓርቲን መወከላቸው ሳይገለፅ ‹ኢህአዴግ› ብቻ እየተባሉ ተመዝግበዋል፡፡ እነዚህ ዕጩዎች ‹የህወሓት፣ ብአዴን፣ ደኢህዴን እና ኦህዴድ› አባላትና በተጨባጭም የእነዚህ አራት ፓርቲዎች አባላትና አመራሮች መሆናቸው እየታወቀ በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ በአሳሳች ሁኔታ ‹ኢህአዴግ› በሚባል የአንድ ውህድ ፓርቲ ዕጩ መስለው ቀርበዋል›› ብሏል፡፡ ይህም ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ህግን ያልተከተለ፣ ወጥነት የሚጎድለውና ህብረተሰቡንም ግራ የሚያጋባ እንዲሁም ለኢህአዴግ ያደላ አሰራርን እየተገበረ እንደሚገኝ እንደሚያመለክት ገልጾአል፡፡

‹‹ምርጫውን ያስፈፅማል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ ቦርድ ይህን የመሰለ ጉልህ ስህተት ሲፈፀም በቸልታ እያለፈ ህገ ወጥነትን እየተባበረ እና እያበረታታ ነው›› ያለው ሰማያዊ ፓርቲ ኢህአዴግ የሚባል ግለሰብ አባላት ያሉት ፓርቲ ሳይኖር በስሙ የተመዘገቡት ዕጩዎች በአስቸኳይ ከዕጩነታቸው እንዲሰረዙና ጉዳዩም ለህዝብ ይፋ እንዲሆን ሲል ምርጫ ቦርድን አሳስቧል፡፡

የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች እንወክላቸዋለን በሚሉት አራቱም ክልሎች ዕጩዎችን በኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ስም ‹‹ህወሓት-ኢህአዴግ››፣ ‹‹ብአዴን-ኢህአዴግ››፣ ‹‹ኦህዴድ-ኢህአዴግ›› እና ‹‹ደኢህዴን-ኢህአዴግ›› በሚል ያስመዘገቡ ሲሆን አዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች ‹‹ኢህአዴግ›› በሚል እንዲመዘገቡ ተደርጓል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials