Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, April 17, 2015

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ ነበር የተባሉ 11 ግለሰቦች ተፈረደባቸው

ራሱን የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ (ጋሕነን) እያለ በሚጠራው ቡድን ውስጥ አመራር፣ ታጣቂና አባል በመሆን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉና በቁጥጥር ሥር ውለው ክስ የተመሠረተባቸው 11 ግለሰቦች፣ በ12 እና በ13 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፡፡
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ ነበር የተባሉ 11 ግለሰቦች ተፈረደባቸው
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፍርድ ውሳኔ ያስተላለፈባቸው ኡቺሚ አፐይ ኡቻላ፣ የጋሕነን ታጣቂዎች ሻምበል መሪ የነበሩት ኡማን ኡጁሉ ቻም፣ ኡቻን ኡጁሉ ኡፐይ፣ ኡመድ ኡጁሉ ኡማን፣ ኝበዱ ቦባንግ ኡጀቶ፣ ኦፒዬ ቹር፣ ኡመድ ኡቶ፣ ኡፑዶክ ኡቲን፣ ታደሰ ኡድጊ፣ ኡማን ኡካይና ኡኬሎ ኡቡር ናቸው፡፡
ፍርደኞቹ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደርና የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን ለማናጋት፣ መሠረተ ልማቶችን የሽብር ታክቲኮችን በመጠቀም ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስና ለማስወገድ በሽብር ድርጅቱ ውስጥ አመራር፣ ታጣቂና አባል ሆነው ሲሠሩ እንደነበርም ይጠቁማል፡፡
በመንግሥታዊ አሸባሪነት ተሰማርቶ በሚገኘው የኤርትራ መንግሥት አጋዥነት ሐሬና ወታደራዊ ማሠልጠኛ በመግባት በሽብር ቡድኑ አመራሮችና የኤርትራ የጦር አመራሮች የተለያዩ ከባድ የጦር መሣርያዎችን አፈታት፣ አገጣጠም፣ ተኩስና ዒላማ፣ የውጊያ ቦታ አያያዝ፣ ቦምብ አወራወር፣ ወታደራዊ ሠልፍ፣ የአካል ብቃት ሥልጠናና ሌሎች ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውንም ክሱ ይዘረዝራል፡፡
ፍርደኞቹ በህዳሴው ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ በጋምቤላ ክልል በሚገኙ የአኝዋ ብሔረሰብ ተወላጆችን ለሽብር ቡድኑ አባልነት በመመልመልና ሥልጠና በመስጠት፣ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና ልማቶች ላይ ጉዳት ለማድረስ ከባድና ቀላል የጦር መሣርያዎችን በነፍስ ወከፍ ታጥቀው እንደነበርም ክሱ ያብራራል፡፡
ከኅዳር 7 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመግባት፣ ከትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን ልዩ ቦታው በረከት ከተማ በተባለ ሥፍራ በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ስምንት አርሶ አደሮችን ሌሊት በር ገንጥለው አፍነው በመውሰድ፣ ውኃ በማስቀዳት ዕገታ ፈጽመውባቸው እንደነበርም በክሱ ተካቷል፡፡ ኅዳር 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ አራት ሰዓት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ በትግራይ ክልል በነበረው ሚሊሻ ሠራዊት ላይ ተኩስ በመክፈትም ሁለት ንጹኃን ዜጎችን በመግደል ፍርደኞቹ መሳተፋቸውን ክሱ በዝርዝር ያብራራል፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ መጋቢት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. በአሥራ አንዱም ተከሳሾች ላይ የመሠረተውን ክስ ሲመረምር የከረመው ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች ከሰማ በኋላ፣ ተከሳሾቹ መከላከያ ምስክሮች እንዲያቀርቡ ብይን ሰጥቷል፡፡ መንግሥት ባቆመላቸው ተከላካይ ጠበቃ አማካይነት ሲከራከሩ ኡማን ኡጁሉና ኡፑዶክ ኢቲን ድርጊቱን ያመኑ ሲሆን፣ ሌሎቹ ግን ክደው ተከራክረዋል፡፡
ፍርደኞቹ ባደረጉት ክርክር ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ እንዳላቸው ፍርዱ ይገልጻል፡፡ የቅጣት ማቅለያ ያላቀረቡ ቢሆንም ቀደም ባሉት ጊዜያት ምንም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ፈጽመው የማያውቁ በመሆናቸው፣ ፍርድ ቤቱ እንደ ማቅለያ እንደያዘላቸው ጠቁሟል፡፡ ሁለቱ ድርጊቱን በማመናቸው አራት አራት የቅጣት ማቅለያ ይዞላቸው፣ እያንዳንዳቸው በ12 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፍርድ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ቀሪዎቹ እያንዳንዳቸው በ13 ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials