Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, April 22, 2015

የጎንደር ከተማ መንፈሳውያን ወጣቶች የአሸባሪው የአይሲስን ኢሰብአዊ ድርጊት አወገዙ፡፡







በጎንደር ከተማ የሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የመንፈሳውያን ወጣቶች ማኅበራትና የማኅበረ ቅዱሳን የጎንደር ማዕከል አባላት በላኩት መግለጫ በአሸባሪውና አረመኔው አይሲስ በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመውን ጭካኔ አውግዘዋል፡፡ በመግለጫው ላይ እንደተገለጠው ‹‹‹‹ISIS›› የሽብር ቡድን 30 ኢትዮጵያውያንን ክርስቲያን በመሆናቸውና ሃይማኖታችንን አንቀይርም በማለታቸው ርህራሄ በጎደለው ሁኔታ አንገታቸውን በሰይፍ በመቅላትና በጥይት በመደብደብ የፈጸመው ዘግናኝ ተግባር ኢትዮጵያዊነትን የሚፈታተን፣ ታላቅ ኀዘንን በክርስቲያኖች ላይ ፈጥሯል፡፡›› ብሏል፡፡
በማያያዝም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው ሊደረጉ ይገባል ያሏቸውን አራት ሐሳቦች ለሀገረ ስብከቱ አቅርበዋል፡፡
የመግለጫውን ሙሉ ቃል ቀጥሎ መመልከት ይቻላል፡፡ 





የጎንደር ከተማ የሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የጎንደር ከተማ ማኅበረ ቅዱሳን ማዕከልና የጎንደር ከተማ ወጣት ማኅበራት መግለጫ 

ሚያዝያ 12 ቀን 2007 ዓም ሰዓት11፡00 
ቦታ፤ መ/ነ/ግ/ቤ/ት ማርያም ሰንበት ት/ቤት አዳራሽ 
በቀን 12/08/2007 ዓ/ም
 በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ቤተክርስቲያን የጎንደር ሰንበት ት/ቤት፣ የማኅበረ ቅዱሳንና የወጣት ማኅበራት ተወካዮች በተገኙበት ስብሰባው በጸሎት ተጀምሮ ቀጥሏል፡፡ የእለቱ አጀንዳ ሚያዝያ 11/2007ዓ/ም ዓለም አቀፍ እስላማዊ አሻባሪ የሆነው ‹‹ISIS›› በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ ርህራሄ በጎደለው መንገድ ሊቢያ ላይ አንገታቸውን ቆርጦ በመጣልና በጥይት በመግደል በሰማዕትነት እንዲያልፉ አድርጓል፡፡ ይህንንም ድርጊት ተከትሎ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃንና የተለያዩ ሀገር መንግስታት መቃዎማቸውንና ማውገዛቸውን ቀጥለዋል፡፡ እኛ በጎንደር የምንገኝ ሰንበት ት/ቤቶች፣ ማኅበረ ቅዱሳንና ወጣት ጥምር ማህበራት ይህንን ዘግናኝ ድርጊት በመቃወም መግለጫ አውጥተናል፡፡ መግለጫ ‹‹ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ስለእግዚአብሔርም ደማቸውን አፈሰሱ ስለ መንግስተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ›› ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ክርስቲያን መሆን እንደ ወንጀል እየታየ ባለበት በአሁኑ ወቅት የቀደሞ ሰማዕታትን ታሪክ በመለሰ ሁኔታ በአሁኑ ሰዓት በርካታ ክርስቲያኖች በአክራሪ እስላሞች አሸባሪ ቡድን እየደረሰባቸው ያለው ግፍ፣ እንግልትና ስቃይ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ደርሷል፡፡ ለዚህም ማሳያው በቅርቡ ‹‹ISIS›› እየተባለ የሚጠራው አለምዓቀፍ የሽብርተኛ ቡድን ሲሆን የግብጽ ክርስቲያኖችን በግፍ በመግደል ለክርስቲያኖች ያለውን ንቀትና ጥላቻ ያሳየበት መንገድ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከዚህ ከግብጽ ክርስቲያኖች ሀዘን ሳንወጣ ሚያዝያ11 ቀን 2007ዓ/ም በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ‹‹ISIS›› የሽብር ቡድን 30 ኢትዮጵያውያንን ክርስቲያን በመሆናቸውና ሃይማኖታችንን አንቀይርም በማለታቸው ርህራሄ በጎደለው ሁኔታ አንገታቸውን በሰይፍ በመቅላትና በጥይት በመደብደብ ዘግናኝ ተግባር መፈጸሙ ተገለጸ፡፡ ድርጊቱም ኢትዮጵያዊነትን የሚፈታተን፣ ታላቅ ሀዘንን በክርስቲኖች ላይ ፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጅ ድርጊቱ አሰቃቂ ቢሆንም ክርስቲያን ወንድሞቻቻን ባሳዩን የተግባር ክርስትና ኮርተናል፡፡ ‹‹ስጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ ይልቅስ ነፍስንም ስጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፡፡›› ሜቴ10፤28 የሚለውን አምላካዊ ቃል በማሰብ ቤተ ክርስቲያንን ጌታችን በደሙ እንደ መሰረታት ሰማዕታት በደማቸው እንዳጸኗት ሁሉ የአባቶቻቸው ልጆች መሆናቸውን በደማቸው መስክረዋልና ስለ ሃይማኖታቸው ሲሉ ባሳዩት ምስክርነት እጅግ እናደንቃቸዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ሰማዕት ለሆኑ ክርስቲያን ወገኖቻችን በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል የሚደረጉ ክርስቲያናዊ ሥርዓቶችን የምንጠብቅ ሲሆን እንደ ጎንደር ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ ማኅበረ ቅዱሳንና የወጣት ማኅበራት ድርጊቱ ሊወገዝ የሚገባው አረማዊ ተግባር ነው እንላለን፡፡ በመሆኑም በሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ በማኅበረ ቅዱሳን፣በወጣት ማኅበራት በኩል የሚከተለውን መግለጫ አውጥተናል፡፡ 1. ለሠላሳው ሰማዕታት በቤተ ክርስቲያን በኩል አስፈላጊውና ተገቢው ስርዓት እንዲከናዎንና እንዲፈጸም ለህዝቡም ወቅታዊ መረጃ እንዲደርስ እንጠይቃለን፡፡ 2. በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የምንገኝ ሰንበት ት/ቤት አባላት፣ የማኅበረ ቅዱሳንና የወጣት ማኅበራት አባላት በሙሉ በየአጥቢያችን ቅዱስ ሲኖዶስ በሚወስናቸው ቀናት ከጸሎተ ፍትሃቱ ጋር በየቀኑ የሰማዕትነት ምልክት የሆነውን 30 ሻማ በማብራት በዝማሬና በትምህርት ሰማዕታቱን እንዘክራለን፡፡ 3. በሰንበት ት/ቤቶች፣ማህበረ ቅዱሳንና ወጣት ማኅበራት በጋራ ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመተባባር ለሰማዕታቱ መታሰቢያ ለ2 ቀናት ታላቅ ህዝባዊ ጉባዔ እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡ 4. እንደ ሰ/ጎንደር ሀ/ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች፣ማህበረ ቅዱሳንና ወጣት ማኅበራት በጎንደር ከተማ ያሉ ህዝበ ክርስቲያን በሙሉ ጊዜያዊ ደስታን ከሚያስገኙ ነገሮች ርቀን ፍጹም መንፈሳዊነት በተሞላበት ሁኔታ በጸሎት ሰማዕትነትን የተቀበሉ ወገኖቻችንን ልናስባቸው ይገባል፡፡ በሌላ መልኩ የባህል ምሽት፣ ጭፈራ ቤት ያላችሁ ሁሉ ቢያንስ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚወስናቸው የጸሎት ቀናት ቤቶቻችሁን እንድትዘጉ እንጠይቃለን፡፡ በመሆኑም ይህንን ሰብአዊነት የጎደለው ድርጊት ለፈጸሙ የአይኤስ አበላት ወደ ሰብአዊ አዕምሯቸው እንዲመለሱና እንደ ሰው የሚያስቡበትን ልቡን እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው እንጸልያለን፡፡ በመጨረሻም የጎንደር ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ የጎንደር ማዕከል ማኅበረ ቅዱሳንና ወጣት ጥምር ማኅበራት በጋራ ለምናከናውናቸው መንፈሳዊና ሰላማዊ ተግባራት ቤተ ክህነቱና መንግስት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርግልን በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፡፡ ‹‹ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን በዚሀ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጠለን››ሮሜ8፤36-37


No comments:

Post a Comment

wanted officials