ያለፉት ሶስት ሳምንታት ለሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን አንገት ያስደፉ ሳምንታት ሆነው አልፈዋል፡፡ በየመንና ደቡብ አፍሪካ በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ሰቆቃና ግፍ ሀዘናችን ሳይበርድ አረመኔው የአይ ኤስ አይ ኤስ (ISIS) ቡድን 30 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያንን በጭካኔ ማረዱንና መግደሉን የተለያዩ የዓለም መገናኛ አውታሮች ዘግበውታል፡፡ ይህ ሀገር ውስጥ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር እና የመልካም አስተዳደር እጦት ለማምለጥ በስደት ላይ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመው አረመኔያዊና የጭካኔ እርምጃ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ልብ ሰብሯል፡፡ ከምንም በላይ አሁንም የእነዚህን ዜጎች ጉዳይ በአግባቡ የሚይዝ መንግስት እንደሌለን መታወቁ የኢትዮጵያውያንን ሀዘን እጥፍ ድርብ አድርጎታል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በዚህ አረመኔ ቡድን በጭካኔ በታረዱና በተገደሉት ኢትዮጵያውያን ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው መግለጽ ይወዳል፡፡ በሀገራቸው ያለውን መከራ ለማምለጥ በስደት እያሉ ይህ በሰው ላይ ሊደርስ የማይታሰብ አረመኔያዊነት የደረሰባቸው ዜጎችን ነፍስ በገነት እንዲያኖራት ምኞቱን ይገልጻል፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና በከፍተኛ ሀዘን ላይ በሚገኙት ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንም መጽናናትን ይመኛል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን ጭካኔ በፅኑ ያወግዛል፡፡
በሌላ በኩል ራሱ ገዳዩ ቡድን ኢትዮጵያውያንን እንደገደለ በገለጸበት፣ በተለያዩ ሚዲያዎችና አይ ኤስ አይ ኤስ በለቀቀው ቪዲዮም የተገደሉት መልክና የፊት ገጽታ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሆኖ፣ የተለያዩ የውጭ መንግስታትም በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ጭካኔ ባወገዙበት፣ ከምንም በላይ ደግሞ ከዚህ ውጭ የሟቾቹን አስከሬንም ሆነ ሌላ ነገር አግኝቶ ማረጋገጥ በማይቻልበት ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ‹‹ የድርጊቱ ሰለባዎች ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ግብፅ የሚገኘው ኢምባሲ አላረጋገጠም፣ በርግጥ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ለማረጋገጥ እየጣርን ነው›› በማለት ለሰለባዎቹ እውቅና ላለመስጠት እና ተገቢዉን እርምጃ ላለመውሰድ በመፈለግ የተሰጠው መግለጫ ሀዘናችንን በእጅጉ አብዝቶታል፡፡ እንደ ሀገር አፍረናል፡፡ በተለመደው መልኩ አንድ መንግስት ነኝ የሚል አካል ሊያደርግ ይገባው የነበረውን ሚና ባለመወጣቱም ብዙዎቹን አስቆጥቷል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በድጋሜ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን አረመኔያዊ ድርጊት እያወገዘ፤ መንግስት በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ዜጎችን ደህንነትን የማስጠበቅ ግዴታውን በጥብቅ እንዲወጣ እያሳሰብን የግፍ ሰለባ ወገኖቻችንን ለማሰብ በአስቸኳይ ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንዲታወጅ እንጠይቃለን፡፡ በመጨረሻም ሰማያዊ ፓርቲ በተፈፀመው አሰቃቂ ድርጊት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸውና በጉዳዩ ልባቸው ለተሰበረ ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ይመኛል፡፡
No comments:
Post a Comment