Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, April 13, 2015

ኢትዮጵያዊያኑ የኬንያን ፍርድ ቤቶች እያጣበቡ ነው


ዳዊት ሰለሞን ከኬንያ እንደዘገበው:-
ከኢትዮጵያ በቀጥታ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚደረግ በረራ ቪዛ ማግኘት ካለፉት አስር ዓመታት ጀምሮ ለኢትዮጵያዊያን ፈጽ ሞ የማይታሰብ ሆኗል፡፡በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ከተሞች ኢትዮጵያዊያን በከፍተኛ ደረጃ ቁጥራቸው እየተበራከተ በመምጣቱ አዲስ አበባ የሚገኘው የኔልሰን ማንዴላ አገር ኢምባሲ ቪዛ መስጠት ዳገት ሆኖበታል፡፡
ethiopia1
ethiopia2
ethiopia3
ህጋዊው መንገድ እየጠበበ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ የሚያስፈልገውን ፈቃድ ማግኘትም 100.000 ብሮችን መስዋዕት ማድረግን ሲጠይቅ የተሻለ ህይወት በደቡብ አፍሪካ እንደሚገኝ የሚሰሙት ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ወደ ኬንያ በማቅናት በህገ ወጥ አስተላላፊዎች አማካኝነት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ናይሮቢን እንደመተላለፊያ መጠቀም ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል፡፡
ከኬንያ ምድረ ርስት ተደርጋ ወደ ተሳለችው ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ጉዞ ብዙ እንቅፋት የሞላበት ቢሆንም ወጣቶቹ ገንዘባቸውን ከስክሰው ሞትን ፊት ለፊት ለመጋፈጥ በመምረጣቸው ለአስተላላፊዎቻቸው ጥሩ እንጀራ ፈጥረውላቸዋል፡፡
‹‹አስጨዳጅ››የሚል መጠሪያ የተሰጣቸው አስተላላፊዎች ከአገር ቤት እስከ ደቡብ አፍሪካ መድረሻ ሰንሰለት የሰራ ግኑኝነት በመፍጠር የተደራጁ መሆናቸውም የሰው ንግዱን ውጣ ውረድ የማይጠይቅ ቀላል ቢዝነስ አድርጎላቸዋል፡፡
‹‹አስጨዳጆቹ››በየድንበሩ ከሚገኙ የፊናንስ አባላት፣ከፖሊሶች፣ከኢምባሲ ሰራተኞችና ከመኖሪያ ቤት አከራዮች ጋር ቁርኝት መፍጠራቸውም የሰው ንግዱን ሰንሰለት መበጠስ ለየትኛውም ወገን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
ኢትዮጵያና ኬንያ ካላቸው ስምምነት የተነሳ ከአንዱ አገር ወደ ሌላኛው ለመተላለፍ ቪዛ የማይጠየቅ መሆኑም በዛ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን አስተላላፊዎቹ ወደ ናይሮቢ ለማዘዋወር ተመችቷቸዋል፡፡የአልሻባብ ዱላ በተደጋጋሚ ጊዜያት ያረፈባት ኬንያ በበኩሏ ድንበሯንና ከተሞቿን በጸጥታ ሰራተኞቿ በስፋት ማስጠበቅ መጀመሯም ለአስጨዳጆቹ ያልተጠበቀ እንቅፋት እየፈጠረባቸው ይገኛል፡፡ኢትዮጵያዊያንን የኬንያ ፖሊሶች በድንበርና በከተሞች አካባቢ ሲያገኙም በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገራችን ገብታችኋል በሚል ሰበብ አፋፍሰው እስር ቤት በመወርወር ፍርድ ቤት መገተርን የቀን ተቀን ተግባራቸው አድርገዋል፡፡ባለፈው አንድ ወር ብቻ ከ485 የሚልቁ ደቡብ አፍሪካ ለመድረስ ናፍቀው ከቤታቸው የወጡ ወጣቶች በፖሊሶች ተይዘው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
አስጨዳጆቹ ለደምበኞቻቸው የሚያደርጉት አቀባበል
ከኬንያ ጉዳያቸውን ጨርሰው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያሻግሯቸው ደላሎች ከመኪና እንደወረዱ እንደሚጠብቃቸው ተነግሯቸው በሞያሌ አቋርጠው ናይሮቢ የሚገቡት መንገደኞች የሚደረግላቸው አቀባበል አስከፊ የሚለው ቃል ከመጠነው የምንጠቀምበት አይነት ብቻ ነው፡፡ፖሊሶች አይደርሱበትም በሚባለውና በአለማችን በድሆች መኖሪያነቱ ተለይቶ በሚታወቀው የናይሮቢ ኪቢራ ሰፈር በሚገኝ መጠለያ በመውሰድ በአንድ ክፍል ውስጥ ከ50 -125 የሚደርሱ የደቡብ አፍሪካ ተስፈኞችን ያሳድሩበታል፡፡
አስጨዳጆቹ ለደምበኞቻቸው ደረቅ ዳቦ ከወረወሩና ጉዳያቸው እስኪያልቅ መንቀሳቀስ ፈጽሞ የማይታሰብ መሆኑን በማስጠንቀቅ ከአካባቢው ይሰወራሉ፡፡ርሃብ፣ተፋፍነው ከመቀመጣቸው ጋር ተደማምሮ በሚፈጠር የአካል መዛል ተስፋ የሚቆርጡ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ወጣቶች ዳቦ ፍለጋ በወጡበት በሌቦች ይዘረፋሉ አልያም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይውላሉ፡፡
የኬንያ ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት በቀላል ማስጠንቀቂያ ታሳሪዎቹን ይለቅ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ‹‹በህገ ወጥ መንገድ በመግባታችሁ ››በሚል ሰበብ እስከ ከ500 -1000 ዶላር ወይም ከ6 ወር – 2 ዓመት የሚደርስ ቅጣት መበየን ጀምሯል፡፡አስጨዳጆቹ ፍርድ ቤት በቀረቡ ደምበኞቻቸው ላይ የሚበየነውን ገንዘብ ለመክፈል ቀርቶ በእስራታቸው ወቅት ስንቅ ለማቀበል እንኳን ድራሻቸው አለመገኘቱም ጭካኔያቸውን ያሳያል፡፡
የተጨዳጆቹ ዕጣ ፈንታ
ዕድል ቀንቷቸው የኬንያ ፖሊስ እጅ ያልወደቁ ተጨዳጆች ወደ ሶስተኛ አገር እንደተዘዋወሩ ተመሳሳይ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡እኛም ኢትዮጵያዊያኑ ድንበር ሊያቋርጡ ሲሉ ተያዙ የሚሉ ዜናዎችን ከደቡብ አፍሪካ ጎረቤት አገራት እንሰማለን፡፡በናይሮቢ ከጠበቁት በላይ ጉዟቸው ተጓትቶ ወይም ፖሊስ ይዟቸው እስር ቤት የተጣሉ ወጣቶች በእስር ቤቶች በሚደርስባቸው ጥቃት የተነሳ ራሳቸውን እስከመጥላት በመድረስ ወደ አገር ቤት እንኳን ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መንገድ ተዳዳሪዎች ሆነው አስቸጋሪውን ህይወት ይገፋሉ፡፡
ትንንሾቹን አሳዎች የሚያጠምደው መንግስት
በቅርቡ ሁለት ሴት አስጨዳጆችን በኢንተርፖል አማካኝነት መንግስት ይዞ ከናይሮቢ መውሰዱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ሰዎቹን በቅርበት የሚያውቁ በናይሮቢ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በበኩላቸው አሳው አንጂ አሳ አንበሪዎቹ አሁንም ባህሩ ውስጥ መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡አሳ አንበሪዎቹ በናይሮቢ ከአስጨዳጅነት ተግባራቸው በተጨማሪ በተለያዩ ታላለቅ የንግድ ኢንቨስትመንቶች የተሰማሩ፣ናይሮቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋር ጥሩ ግኑኝነት በመፍጠር ኢምባሲው በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ዝግጅቶች ቀድመው በመገኘት ሪከርድ የሰበሩ፣ያለ ችግር አገር ቤት ገብተው ተጨዳጆችን መልምለውና ዲያስጶራ በሚል ስያሜ ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው የተንደላቀቀ ህይወት የሚመሩ መሆናቸውን ያወሳሉ፡፡የኬንያን ፖሊሶች በወዳጅነት የቀረቡት አሳ አንበሪዎች እጃቸው ከዚህም በላይ ረዥም መሆኑን የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
መፍትሔው በየት ነው?
በአብዛኛው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር ድንበር የሚሻግሩት ወጣቶች የአንድ አካባቢ ተወላጆች ናቸው ፡፡ከደቡብ ክልል የበቀሉ ተስፈኛ ወጣቶች፡፡እነዚህን ወጣቶችን በመመልመል ስራ የተሰማሩትም የዚያው ክልል ተወላጆች ናቸው፡፡የአስጨዳጆቹ የአገር ቤት ወኪሎችም የደቡብ ልጆች ናቸው፡፡መምህራን፣ፓስተሮች፣ካድሬዎችና በየአካባቢው የሚታወቁ ሽማግሌዎችና ልጆቻቸው ቀደም ብለው በደቡብ አፍሪካ ኑሮ የመሰረቱላቸው ቤተሰቦች ናቸው፡፡መንግስት ለአካባቢው ትኩረት በመስጠትም የስደት ጎርፉን መቀነስ የሚያስችለውን ፖሊሲ ሊቀርጽ ይችላል፡፡
እርግጥ ነው ስደተኞቹ በአገራቸው ሰርተው ለመኖር የሚያስችላቸው ዕድል ቢፈጠርላቸው ይህን ያህል የኬንያን ፍርድ ቤት የሚያጣብቡበት መንገድ ሊፈጠር አይችልም፡፡እናም አስጨዳጆቹን ለቃቅሞ በማሰር ብቻ ነገሩን ማቆም የማይቻል በመሆኑ የስራ ዕድል ለሁሉም እኩል የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ለዜጎቼ አስባለሁ ከሚል ስርዓት ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials