Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, April 9, 2015

ድምጽ ከመስጠት ደም መስጠት (አብርሃም Hታዬ)

በቅድሚያ ይሄን አስተማሪ ቀልድ ጀባ ልበላችሁ
electionአንድ ግለሰብ ይሞትና ነፍሱ ዳኞች ፊት ቀረበ።እንደ አጋጣሚ ለወደፊት የሚኖርበትን ገነትን ወይም ሲኦልን ገብኝቶ የመምረጥ እድል ተሰጠው።በመርሐ-ግብሩ መሰረትም በመጀመሪያ ሲኦልን እንዲጎበኝ ይጋበዝና ገና ከበሩ ላይ በመልካም አለባበስ የተሸቆጠቆጠው ሳጥናኤል በሞቀ ሰላምታ ተቀብሎት ወደ ውስጥ ይዞት ይገባል።ገሃነም ውስጥ የሟች የድሮ ወዳጆች ሁሉ ተሰብስበው እየጠጡ፣ ከረንቦላ እየተጫወቱ፣ ዲኤስ ቲቪ እያዩ እና በሙዚቃ እየጨፈሩ አስደሳች ጊዜ ሲያሳልፉ ተመለከተ።
ከዚያም ወደ ገነት ተወሰደ። ገነት እንደ ገባ አንድም የድሮ ጓደኛውን ሊያገኝ አልቻለም። ከዚያም በላይ ሲያስበው ያስመረረው ግን በገነት ያሉ ሰዎች ነጫጭ ለብሰው ስራቸው  ማሸብሸብ፣መጸለይና መስገድ ብቻ መሆኑ ነው ።
ሟች ሁለቱንም ሁኔታዎች አመዛዝኖ ሲያበቃ ገሃነም ከወዳጆቹ ጋር ለመቀላቀል ወስኖ ፊርማውን አኖረ። በማግስቱ ወደ ገሃነም ሲወሰድ ግን የጠበቀው ነገር ሌላ ነበር። ሳጥናኤል በአስፈሪ ዕርቃኑ ቆሞ እህል-ውሃ የማያሰኝ ጅራፍ ይዞ እየዠለጠ ወደ ውስጥ አስገባው። ውስጥ የነበሩት ጓደኞቹም ግማሽ ሰውነታቸው በእሳት ተዘፍቆ ሲሰቃዩ ተመለከተ።  ወደ አንድ ጓደኛው ጠጋ አለና ‹‹ትላንትና ያየሁት ደስታ የት ሄደ?›› ብሎ  ቢጠይቀው። ‹‹አይ እሱማ የምርጫ ቅስቀሳ ነው›› ብሎት እርፍ!
በሃገራችንም ምርጫ ሲደርስ ገዢው ፓርቲ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ደርሷችኋል ይለናል ቤቱ ግን ኣልተሰራም ወይ አላለቀም።የገባንባቸው ቤቶችም ፍሳሽ ከላይ ወደታች ሰው ላይ ይንጠባጠባል:: ምርጫ ሲደርስ ሰላማዊ ሰልፍ ይፈቅድልናል ስንወጣ ግን መንገድ ይዘጋብናል፥ የምርጫ ቅስቀሳ ፖስተሮች ይቀዱብናል፤ያስሩናል፤ ይደበድቡናል። እስከምርጫው ዋዜማ በየቀበሌው በየሰፈሩ እየዞሩ ድጎማ ይሰጡናል ይደልሉናል በምርጫው ማግስት አይናችንንም ማየት ይቀፋቸዋል።
ባለፉት አመታት ሊሰሩ ታቅደው የመሰረት ድንጋይ የተጣለባቸውን ቦታዎች እስካሁንም ሳይሰራ ተጎልቶ ምርጫ ሲደርስ ተጠቅላይ ምኒስተር ሃይለ ማርያም ደሳለኝ በወሎ መሰረት ድንጋይ ጣሉ ወይም ባላፈው የተመረቀ የዉሃ ማቆሪያ መረቁ ይሉናል በድጋሚ።ሃገር አቀፍ ምርጫ በደረሰ ቁጥር ወተት እንደ ዉሃ በቧንቧ አስገባለው እያለ የሚለፈልፈው መንግስታችን የተዋጣለት ፎጋሪ መሆኑን የሚያንጸባርቀውን የቀላል ባቡር ምርቃ እንመልከት።  አዲስ አበባን የበርሊን ግንብ ኣስመስሎ ለሁለት የከፈላት  የባቡር መንገድ ግንባታ አንድ ሰው ከሳሎን ቤቱ ወደመኝታ ቤቱ ለመሄድ የአንድ ሰአት ታክሲ መንገድ ርቀት ሆኖበታል። ሃዲዱ  ተመርቋል ተብሎ የካቲት ላይ ተነግሮን አገልግሎት የሚጀምረው ግን  ከሶስት ወር ኋላ ምርጫ ሲቃረብ  ነው ያሉን ያው ለምርጫው ማሟሟቂያ ዘገባ ካንድም ሁለቴ ሲመረቅም ሲጀመርም በመተረክ ህዝቡን በወሬ ለማጥገብ ነው። በተግባር ግን መንገዱ ከመሰራቱ ከ 6 ጊዜ በላይ ከባባድ የመኪና ግጭቶች ደርሰውበታል። አሰራሩ የይድረስ ይድረስ ስለሆነ የብረት አጥሩም የባቡሩ ሃዲድም ገና በድምጽ ይደረመሳል። የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ የሚለው አባባል ለፎጋሪው ወያኔ የተጠቀሰ እስኪመስል ድረስ ቻይና ሰራሽ መንገዶች ድልድዮች ሲልም ህንጻዎች ገና አመት ሳያገለግሉ ይሰነጣጠቃሉ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ።የቀለበት መንገድም ሆነ ቀላል ባቡር  የእግረኛ መንገድ ስለሌለው  በታጠረው የባቡር እና የመኪና   መንገድ እግረኞች  ሲዘሉ ሲሻገሩ ለአደጋ ይጋለጣሉ።
ገና ከመሰራታቸው ከተቆፈሩት መንገዶች አንዱ ዛሬ ባቡር መንገድ ተብሎ የታጠረው ከመስቀል አደባባይ ወደ ሳሪስ የሚወስደው ሰፊ የአስፋልት መንገድ መሆኑ መረሳት የለበትም። ከ2005 አም በፊት ለመኪና ብቻ ተብሎ የመስቀል አደባባይ ሳሪስ መንገድ ሲሰፋ በርካታ ሰዎች ካካባቢው ተነስተዋል ከቁፋሮ ጀምሮ  እስከ  አስፋልት የማልበስ ድረስ ከፍተኛ የዉጪ ብድር ገንዘብ ተከስክሶበታል። ይሁንእና  ስንት ወጪ ፈሶበት በተሰራው ባለሶስት መስመር መንገድ መኪኖች ሸር ማለት እንደጀመሩ ለባቡር መሆን አለበት የሚል ሃስብ በደንገት ብልጭ ባለበት የመለስ  የትራንስፎርሜሽን ቅዠት ምክንያት  ያው አስፋልት በድጋሚ ለባቡር ተብሎ ታጠረ ተቆፈረ አሁን ደሞ ተመረቀ ሲባል  አንድም ባቡር ሳይሄድበት ተሰባበረ።እንግዲህ ወያኔዎች ለ አዲስ አበባ ህዝብ በአምስት አመቱ የ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት ሰራንልህ የሚሉት  ፉከራ ፉገራ ሲሆን እያየነው ነው። እውነታው ግን ድንጋይ መንገድ ላይ ከምሮ ሰውን ሁሉ ቃሊቲ አስሮ ማሰቃየት ነው::
በድፍረት ምርጫ ዲሞክራሲያዊ የሚያሰኘው ሂደቱ ነው እንጂ ውጤቱ አይደለም የሚለን የመንግስት የኮሚኒኬሽን ሃላፊ የእስካሁኑ ሂደት ዲሞክራሲያዊ ነው ብሎ መግለጫ ይሰጣል። ለመሆኑ  ጽሁፍን ሳንሱር ማድረግ ህገመንግስቱን የሚጻረር አይደለምን? ይሄው እስካሁን እንኳ ሰማያዊ ፓርቲ ከ10 ጊዜ በላይ የምረጡኝ ቅስቀሳውን በአንድዬዋ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ እንዳያቀርብ ተከልክሏል። ተለጣፊ የሚባለው መ ኢ ኣ ድ እና የተቃዋሚ ካባ ለብሶ የሚጫወተው ኢህአዴጉ ኢዴፓም የቅስቀሳ መልክቶቼ ሳንሱር እየተደረጉብኝ ነው ሲሉ ስንሰማ ወያኔ የራሱ የሆኑት እንኳ ለዘብተኛ ተቃውሞ ወይ ውዳሴ  ላለማዳመጥ መቁረጡ አምባገነንነቱ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ያረጋግጣል።
ህወሃት ኢህኣዴግ ሙሉ ሃያ አራት አመት ሙሉ ሃያ አራት ሰዓት እየደሰኮረ  በአምስት አመት አንዴ ለዛውም አንዲት ሰዓት  ለማይሞላ የተፎካካሪ ፓርቲ የሚሰጥ የአየር ሰዓት  ከተከለከለ  ህዝቡ ተፎካካሪ ፓርቲን መኖሩን ካልሰማ ቀጣይ አመታትን በድህነት፥ በ ኢ-ፍትሃዊነት፥በዘረኛው  ስርዓት ወስጥ መክረሙ አሌ ኣይባልም።
ምንም የግል ሚዲያ በሌለበት ሁኔታ በብቸኛው የመንግስት ቲቪ እና ራዲዮ ካመት ኣመት የሚሰለቸውን ወሬ መስማት ብዙ ኢትዮጵያውያንን አስመርራል ። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኣላማቸውን ባላስተዋወቁበት ሁኔታ ህዝቡን ንብን ይምረጡ ሲል ግራ ያጋባል። ሌሎቹን ከልክሎ ኣፍኖ እና አስሮ ብቻውን ምረጡኝ እያለ የህዝቡን የመዝናኛ ፕሮግራሞች የማየት ፍላጎቱን ገድቧል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫ ዘጠና ሰባት ተመሳሳይ የኮንዶሚኒየም ቤት ምርጫ ሲደርስ የተሰጠው እና  በገንዘብም የተደለለ ቢመስልም በነበረችው ትንሽ ቅስቀሳ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መርጦ ነበረ።ይሁንእና በማግስቱ ለምን ቅንጅትን መረጣቹ ብሎ ለምርጫ ቅስቀሳ ያሳየንን ፊት ነስቶ በርካታ ኢትዮጵያውያን ታስረዋል ተገድለዋል አሁንም የበቀል ሰለባ ሆነዋል::  ያኔ የተሰለፍነው የሚመረጥ ስለነበረ ሲሆን አሁን ግን ደም መጣጩን ከምንመርጥ ብንታቀብ ይበጃል::ሃሳብን የመግለጽ መብት በይፋ በተዘጋበት በዚህ ወቅት መከራከር ራስ ላይ ሰበብ መጠምጠም ነው::
በ አሁኑ ኣለም ቀፍ ታዛቢዎች በማይገኙበት የኣውሮጳ ህብረት ምርጫውን እንዳይታዘብ በተከለከለበት በዚህ ወቅት ከምንም በላይ ታዛቢው ህዝብ  የወያኔን እንጂ የሌላን ፓርቲ ኣላማ እንዳይሰማ ገድበው፥ የምርጫ ቆጣሪዎች ሳይቀሩ ከወያኔ ሴት ሊግ ወጣት ሊግ ያለህዝብ ይሁንታ ተመርጠው የምርጫ ድምጽ ለመስረቅ ለማዛባት ኣቆብቁበው፥ የሰማያዊን ከሁለት መቶ በላይ ዕጩዎች መወዳደር ኣትችሉም ብለው ያለህግ አግደው፥ በአጠቃላይ በዘንድሮው ምርጫ የመወዳደሪያ ሜዳው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየጠበበ መምጣቱን የሚያሳይ ተግባራት ተከምረውብን የሚቆሰቁሱን ድምጽ ለመስጠት ሳይሆን ደም ለመስጠት  ነው።
ከገባን የምርጫ አጃቢ አድርጎን በሗላ ጅብ ሆኖ ከሚበላን ለወንበዴ ወያኔ ድምጽ ከመስጠት ለነጻነት ደም ብንሰጥይቀላል።
የቀድሞው የ አሜሪካ ፕረዚዳንት እብርሃም ሊንከን Ballot is stronger than bullet የምርጫ ካርድ ከጥይት የጠነከረ ነው ቢልም በሃገራችን የምርጫ ሳጥኖች በጠበንጃ ሲቀየሩ ስላየን  We are forced to use bullet instead of ballot የሃይል አማራጭ እንድንጠቀም እንገደዳለን።
እነ እስክንድር ነጋ ወይ ርእዮት አለሙ ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያን ስለታሰርን በቅድሚያ ልንፈታ ይገባል።
ከአብርሃም ታዬ
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/40287 

No comments:

Post a Comment

wanted officials