Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, April 13, 2015

ቤይሩት ለመድረስ አስባ በናይሮቢ የጠፋች ነፍስ

መሰረት ከጎንደር አዘዞ ተነስታ ህይወትን ለማሸነፍ አዲስ አበባ ከተመች፣ሸገር ለ16 ዓመቷ ታዳጊ ያዘጋጀችላት መና ስላልነበርም ወላጅ እናቷን በሞት ተነጥቃ ሰማይ ምድሩ የተደፋባት መሰረት ቡና ቤት ተቀጠረች፡፡‹‹ክበረ ንጽህናዬን ሸጬ ለሶስት ዓመታት ያህል ባጠራቀምኩት ገንዘብ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ዱባይ አመራሁ›› በዱባይ የሶስት ዓመታት ቆይታ መሰረትና እድል አብረው አልነበሩም፡፡
የረባ ገንዘብ ማጠራቀም ሳትችል ኮንትራቷ በመጠናቀቁ በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ግድ ሆነባት፡፡
የአዲስ አበባው መንግስት አገሪቱ በኢኮኖሚ ጫፍ መርገጧን ፣መሰረተ ልማቶች መስፋፋታቸውንና ዜጎች በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው መካከለኛ ነጋዴዎች መፈጠራቸውን ቢሰብክም አዲስን ለሶስት ዓመታት ለተለየቻት መሰረት ከተማይቱ ወለል አድርጋ የከፈተችላት የቡና ቤቶቿን በር ብቻ ነበር፡፡
‹‹ስጋዬን እየሸጥኩና ራሴን እያረከስኩ ለመኖር ህሊናዬ ስላልፈቀደልኝ ወደ ዱባይ ለመመለስ ወሰንኩ››የምትለው መሰረት መንግስት ወደ አረብ አገራት የሚደረጉ ጉዞዎችን ማገዱን ዘግይታ ሰማች፡፡ሰውን በህገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር ደለብ ያለ ገቢ ያካበቱ የሞት ደላሎች እጅ የወደቀችው መሰረት ኬንያ ከሄደች በኋላ በ24 ሰዓት ውስጥ የቪዛዋን ጣጣ ጨርሰው ቤይሩት ሰው ቤት እንደሚያስቀጥሯት ደላሎቹ ማግባባት በመቻላቸውም 14.000 የኢትዮጵያ ብር ክፍያ ፈጽማ ቤይሩት ለመድረስ በሞያሌ አድርጋ ናይሮቢ ትገባለች፡፡
በአንድ ቀን ዕድሜ ቤይሩት ገብታ ስራ እንደምትጀምር የተደሰኮረላት ወጣቷ በናይሮቢ የተቀበላት በ50ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ሰው ጉዳይዋን በመከታተል የሚጨርስላት እርሱ መሆኑን በመግለጽ ለመኝታ ወዳዘጋጀላት ሶስት በሶስት ወደሆነች ግድግዳዋና ጣራዋ ቆርቆሮ ወደሆነች ቤት ያመጣታል፡፡በቤቱ ውስጥ እንደርሷው ተስፋ ተገብቶላቸው በሞያሌ በኩል ናይሮቢ የመጡ አራት ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን ታገኛለች፡፡
አራቱ ሴቶች በግምት 14፣15፣17 እና 19 የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ የምትናገረው መሰረት አማርኛ መናገር የማይችሉ በመሆናቸው ለወራት ለመግባባት ተቸግረው በቆርቆሮዋ ቤት መክረማቸውን ትገልጻለች፡፡የቤይሩት ጉዞዋን እየጠበቀች በቆርቆሮዋ ቤት ሶስት ወራትን ያስቆጠረችው መሰረት እቤቷ እየመጡ እንዲያርፉ ከሚደረጉ የአገሯ ሴቶች ብዙ የስቃይ ዜናዎችን አድምጣለች፡፡
ለደላላዎቹ ገንዘባቸውን ከፍለው በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ የሚገቡት ወጣት ሴቶች በደላሎቹ እንደሚደፈሩ፣ላልተፈለገ እርግዝና በመጋለጣቸውም ራሳቸውን እስከማጥፋት የሚደርሱ አጋጥመዋት ከሚያነቡት አንብታ የራሷ ዕጣ ደግሞ የት እንደሚያደርሳት ነገን እየፈራች አምላኳን ትማጸናለች፡፡
‹‹በናይሮቢ የተቀበለኝ ደላላ ለትንሽ ግዜ ስልክ እየደወለ በሳምንት ውስጥ ለሁለት ቀን የማይበቃ ምግብ እየሰጠኝ ጉዳይሽ ነገ ያልቃል እያለ ሲያታልለኝ ቆይቶ በቅርቡ ደውሎ ‹‹ሁለተኛ እንዳትደውይልኝ ››በማለት እንዳስጠነቀቃት በእንባ ተውጣ ታስረዳለች፡፡
‹‹በምሽት እየደወለ እቤት ልምጣ ሲለኝ እምቢ በማለቴና ፓስፖርቴን እንዲሰጠኝ በመጠየቄ ከአሁን በኋላ እንዳልደውል ከደወልኩ ግን ለፖሊስ ደውሎ እንደሚያሲዘኝ ዛተብኝ››ትላለች፡፡
ጓደኞቿ እርዳታ ሊያደርጉላቸው በሚችሉ ሰዎች መወሰድ
በናይሮቢ የቆርቆሮ ቤት ውስጥ ያገኘቻቸው አራት ሴቶች መወሰድ መሰረትን የበለጠ በአገሯ ልጆች ድርጊት እንድታዝንና መፈጠሯን እንድትጠላ አድርጓታል፡፡‹‹ከልጆቹ ጋር በቋንቋ መግባባት ባንችልም በጊዜ ሂደት በደረሰብን ተመሳሳይ በደል ምክንያት መግባባት ችለን ነበር፡፡የእነርሱ አጠገቤ መኖርም ብዙ እገዛ አድርጎልኛል፡፡በዚህ መሃል ስለ እኛ የሰሙ ሰዎች አምስታችንንም መጥተው አነጋገሩን፣ለፖሊስና ሊረዱን ለሚችሉ ድርጅቶች ስለ እኛ ሁኔታ በማስረዳትም እንደሚተባበሩን ነገሩን፡፡ነገር ግን በመጨረሻ የወሰዷቸው አራቱን ብቻ ነው፡፡››እንባ ተጨማሪ ቃላቶችን ከአንደበቷ እንድታወጣ አልፈቀደላትም፡፡
‹‹የምትበላው ምግብ፣ለምታድርበት የቆርቆሮ ቤት የሚከፈል ገንዘብ የሌላት መሰረት ‹‹ይህንን የሚያነብና ታሪኬን የሚሰማ የአገሪ ህዝብ ፓስፖርቴን የማገኝበትንና በአዲስ አበባ ላፍቶ አካባቢ የምትንቀሳቀስ ሄለን የተባለች ደላላ ጋር በመደወል ጭምር ካለሁበት ሁኔታ እንድወጣ እንዲተባበረኝ መንግስትም ዜጋው በመሆኔ እንዲደርስልኝ እማጸናለሁ››የመጨረሻ መልዕክቷ ነው፡፡
ሄለን የተባለችውን ደላላ በ251 9 13 41 23 45 ማግኘት እንደሚቻልም ህይወቷ አደጋ ውስጥ የሚገኘው መሰረት ትገልጻለች፡፡በተለይ አገር ውስጥ ያላችሁ ዜጎች በዚህ ስልክ በመደወል ጫና እንድታሳድሩ ትለመናላችሁ፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials