Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, April 29, 2015

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የፕላስቲክ ፋብሪካ በከፊል በእሳት ቃጠሎ ወደመ


-የወደመው ንብረት ግምት ተጣርቶ አላለቀም ተብሏል
በግዙፉ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን ሥር በሚተዳደረው ኢትዮ ፕላስቲክ ፋብሪካ ላይ፣ ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም በማምረቻ ክፍሉ ውስጥ የተቀሰቀሰ እሳት በከፊል ውድመት አደረሰ፡፡
በፋብሪካው ውስጥ ኬሚካሎችና ሌሎች የተቀጣጣይነት ባህሪ ያላቸው ጥሬ ዕቃዎች ተከማችተው የነበሩ ቢሆንም፣ የተነሳው እሳት በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱ ተገልጿል፡፡
ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ 8፡30 ሰዓት ገደማ የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ዋና መሥሪያ ቤት አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕላስቲክ ፋብሪካ ላይ የተነሳው ቃጠሎ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፣ ኬሚካል ነክ የሆኑ ጥሬ ዕቃዎች የተከመሩበት መጋዘን ሙሉ በሙሉ ወድሟል። እሳቱ የተነሳው በፋብሪካው የጥሬ ዕቃዎች ማከማቻ መጋዘን ላይ ቢሆንም፣ ከሁለት ሰዓታት በላይ በተደረገ ርብርብ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡
የአዲስ አበባ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር ኤጀንሲ ከተደወለለት በኋላ ቃጠሎው ቦታ ለመድረስ ከአንድ ሰዓት በላይ መዘግየቱን የፋብሪካው ሠራተኞችና በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የእሳት አደጋ መከላከል ሠራተኞች በበኩላቸው፣ በዕለቱ የነበረው የትራፊክ መጨናነቅ በሚፈለገው ፍጥነት መድረስ እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡
የእሳት አደጋ መከላከል ሠራተኞች ዘግይተው ከደረሱ በኋላም ቃጠሎውን ገብተው ለማጥፋት እንዳይችሉ፣ የፋብሪካው የውስጠኛ ክፍል ለተሽከርካሪዎች አስቸጋሪ በመሆኑ በግምት ተጨማሪ 20 የሚሆኑ ደቂቃዎች ሲባክኑ ታይቷል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎችን ጨምሮ ፖሊስና የእሳት አደጋ መከላከል ሠራተኞች እሳቱን ለመቆጣጠር በሚሞክሩበት ወቅት፣ ከሚቃጠለው ኬሚካል ይወጣ የነበረው ጭስ የሚያቃጥል በመሆኑና በመተንፈሻ አካላት ላይ በደረሰባቸው ተፅዕኖ ሲፈተኑ ተስተውሏል፡፡ የአደጋ ሠራተኞቹ ከኬሚካሉ ጭስ ሊከላከላቸው የሚችል የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አልነበራቸውም፡፡
በዚያው ቅጽበትም አንድ የፌዴራል ፖሊስ አባል በጭሱ ምክንያት ራሱን ስቶ ወድቆ የአደጋ ሠራተኞች በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ወስደውታል፡፡ ነገር ግን ከቆይታ በኋላ ከሆስፒታል ተሽሎት እንደወጣ ከቀጣና ሦስት ፖሊስ ማዘዣ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡
የፖሊስ ማዘዣ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ሳጂን ኪሮስ ፍቃዱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከአንድ አባላቸው ጊዜያዊ ጉዳት ውጪ በሰው ሕይወት ላይ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰና መንስዔው ገና በምርመራ ተጣርቶ አለማለቁን ገልጸዋል፡፡ እሳቱን ለማጥፋትም ሰባት የአደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች ሲሰማሩ፣ በአደጋው የጠፋው የንብረት መጠን ግን ለጊዜው አለመታወቁ ተገልጿል።
በተመሳሳይ ሚያዝያ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ስሙ 7ኛ ሸንኮራ በረንዳ በተባለው ሥፍራ በተነሳ የእሳት አደጋ፣ 800,000 ብር የተገመቱ ሁለት ካፍቴሪያዎችና አንድ የመኖርያ ቤት ተቃጠሉ። በተለይ ዓለም ካፌ በሚል መሠርያ ተመርቆ ሥራ ለመጀመር አንድ ቀን ሲቀረው መቃጠሉ ታውቋል፡፡
በአንድ የእሳት አደጋ አጥፊ ባለሙያ ላይም መጠነኛ ጉዳት መድረሱ ተረጋግጧል። ሦስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረትን ግን እሳቱን በማጥፋት ርብርብ ማትረፍ መቻሉን፣ የሁለቱም አደጋዎች መንስዔ በመጣራት ላይ መሆኑን ሪፖርተር ከእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials