ግብጽ 13 ተኛ ስትባል ኢትዮጵያ 46 ተኛ ላይ ተቀምጣለች የፈረንጆቹ 2015 የአለም ሀገራት የጦርና ወታደራዊ አቅም በግሎባል ፋየር ፓወር ተቋም አማካኝነት ማክሰኞ እለት ይፋ ተደርጓል. ተቋሙ በዘንድሮው ሪፖርቱ ከ 50 ባላነሱ የመመዘኛ መስፈርቶች የመዘናቸውን የአለም 106 ሀገራት የወታደራዊ ጡንቻ አቅም በደረጃ ማስቀመጡን አስታውቋል.
የሀገራት የወታደር ቁጥር, ለጦር ሰራዊታቸው የሚመድቡት አጠቃላይ በጀት, የጦር መሳሪያዎቻቸው ብዛት, ጥራትና አይነት … ወዘተ የመሳሰሉ አተቃላይ የሚሊታሪ አቅም መመዘኛ መስፈርቶችን ተጠቅሙ ተቋሙ ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉን ገልጿል. በዚህ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ቁንጮ በመሆን የምትመራዋ ሀገር እንደተለመደው ልእለ ሀያሏ አሜሪካ ስትሆን ራሺያ, ቻይና, ህንድ, እንግሊዝ, ፈረንሳይ, ጀርመን, ቱርክ, ደቡብ ኮሪያና, ጃፓን ተከታዮቹን ዘጠኝ ደረጃዎች በመያዝ የአለም አስር ባለትልቅ የጦር አቅም አገሮች ተሰኝተዋል. አሜሪካ ይህን የቀዳሚነት ደረጃ ስትቀዳጅ 612 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ የጦር ሰራዊት በጀት በመመደብ (ሰባት በመቶ መቀነሷ ቢነገርም) ቀዳሚ ስትሆን; ሁለተኛዋ ራሺያ የምትመድበው 88 ቢሊዮን ዶላር (መጨመሩ ይነገራል); ሶስተኛ ደረጃ ላይ ምትገኘው ቻይና ከምትመድበው 130 ቢሊዮን ዶላር (ይህም መጨመሩ ይነገራል) እንዲሁም ሌሎች ሀገራት ከሚመድቡት ወታደራዊ በጀት በእጅጉ የሚያስከነዳ መጠን ያለው ብር ሀገሪቱ ፈሰስ ታደርጋለች ተብሏል. ብቻዋን ከ 19 የማያንስ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ያላት አሜሪካ ቀሪው አለም በድምሩ ካለው 12 ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ይልቃል. ሀገሪቱ በዚህ ብቻም አይደለም 1.4 ሚሊዮን ቋሚ ወታደር 13 ሺ የጦር አውሮፕላን ስምንት ሺህ ታንክ 7506 ተተኳሽ ኒውክሌር እንዲሁም ከ 75 የማያንስ ባህር ሰርጓጅ መርከብ በመያዝ ጭምር ከአቻዎቿ ፍጹም ብልጫ ወስዳ ነው. ከአለም ጠንካራ ጦር ባለቤት ከሆኑ 35 ሀገራት ውስጥ በ 13 ተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ግብጽ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ባለጡንቻ ሀገር ናት ተብሏል. 4.4 ቢሊዮን ዶላር በጀት; 468 ሺህ ወታደር; 4700 ታንክ; 1100 የጦር አውሮፕላንና; አራት ባህር ሰርጓጅ መርከብ ያላትና በአባይ ወንዝ ዙሪያ ሁሌም ከኛ ጋር ፍጥጫ የማያጣት ግብጽ ከአለም አስራ ሶስተኛዋ ባለጠንካራ ጦር ተሰኝታለች. በዚህ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ከአለም በ 46 ተኛ ደረጃ ላይ ምትገኘዋ እናት ኢትዮጵያችን 340 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ በጀት; 2300 ታንክ; 81 የጦር አውሮፕላን; 182 ሺህ ወታደር ይዛ 27 ተኛ ላይ ካለችው አልጄሪያ; 32 ተኛ ላይ ከተቀመጠችው ደቡብ አፍሪካ; እንዲሁም 41 ኛ ላይ ከምትገኘው ናይጄሪያ ለጥቃ ከአፍሪካ የአራተኛ ደረጃነትን (ከአለም 46 ተኛ) ልትይዝ እንደቻለች ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል. ይህን የደረጃ ሰንጠረዝ በሚመለከት ተቋሙ መገምገሚያ መስፈርቱ በአብዛኛው የጦር ሰራዊት ብዛትን ወይ የመሳሪያ ቁጥርን የተመረኮዘ ነው በሚል የተተቸ ሲሆን አንዳንዶች እንዳሉትም የጦር አቅም ዋነኛ መመዘኛው አይምሬውና እጅግ አውዳሚው መሳሪያ ኒውክሌር በመሆኑ እሱን የታጠቁ ሀገራት በሰንጠረዙ ሊቀድሙ ይገባል የሚል አስተያታቸውን ነው የሰጡት
No comments:
Post a Comment