በየመን እየተንቀሳቀሱ ያሉ አማፅያን በቅርቡ ዋና ከተማዋን ሰነዓን በመቆጣጠር ፕሬዝዳንቱን ለስደት መዳረጋቸውን ተከትሎ የአረብ ሀገራት በሳዑዲ የሚመራ ወታደራዊ ጥቃትን በአማፅያኑ ላይ እያደረሱ ነው። ኤርትራም በወታደራዊ ጥቃቱ ላይ ተሳትፎ እንድታደርግ በአረብ ሊግ ጥያቄ ቢቀርብላትም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርገውታል።
ዜናውን ያሰራጨው ገሲካ አፍሪካ ኦንላይን ፕሬዝዳንቱ የአረብ ሊግን ጥያቄ ለምን ውድቅ እንዳደረጉ የገለፀው ነገር የለም። በጥቃቱ ላይ ሰፊ ተሳትፎ ያላት ሳዑዲ አረብያ የተለያዩ ሀገራት በሎጀስቲክና በቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት እንዲሳተፉ ጥያቄ እያቀረበች ሲሆን ሱዳን በበኩሏ ጥያቄውን በመቀበል እግረኛ ጦሯን ብሎም የውጊያ አውሮፕላንን የምታሳትፍ መሆኗን ገልፃለች።
ሱዳን ትሪብዩን ባሰራጨው ዘገባ ሱዳን ስድስት ሺህ የእግረኛ ጦርን ለማሳተፍ ቃል ገብታለች። የሳዑዲን ጥሪ በመቀበል በየመን አመፅያን ላይ ለሚደርሰው ወታደራዊ ጥቃት ትብብራቸውን የገለፁት ሀገራት ዮርዳኖስ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ፓኪስታንና ሱዳን ናቸው። አማፅያኑን በገንዘብና በሎጂስቲክ ትደግፋለች በሚል ኢራን ክስ እየቀረበባት ነው።
ኤርትራ በዓረብ ሊግ በኩል የቀረበላትን ጥሪ ውድቅ የማድረጓ ምክንያት ተደርጐ በፖለቲካ ተንታኞች እየተገለፀ ያለው ሀገሪቱ ከኢራን ጋር ያላትን የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላለማሻከር ነው።