ሚያዝያ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መንግስት ባለፉት አምስት አመታት ተግባራዊ ባደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረት ምርቶችን ውደ ውጭ በመላክ በያመቱ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በአምስቱ አመታት ውስጥ ያሳካው ሩቡን ያክል መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።
መንግስት በያመቱ ከኤክስፖርት ከ2 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን እስከ 3 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ሲንቀሳቀስ ቢቆይም፣ በአምስት አምት ውስጥ ያገኘው አጠቃላይ ገቢ ከ3 ቢሊዮን ዶላር ያልበለጠ ነው። በተቃራኒው መንግስት በአምስት አመቱ ውስጥ ወደ አገር ውስጥ ያስገባው ገቢ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን፣ በአምስት አመቱ መጨረሻ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ ከ8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከፍ ብሎአል።
የወጪ ንግድ ገቢው ዝቅተኛ መሆን በአንድ በኩል የ5 አመቱ የልማት እቅድ ህዝቡን ሆን ብሎ ለማደናገር በምኞት ላይ ተመስርቶ የታቀደ መሆኑን ሲያመላክት፣ በሌላ በኩል ደግሞ እቅዱን ያወጡ ሰዎች ችሎታውና ብቃቱ የሌላቸው መሆኑን ኢኮኖሚስቶች ይናገራሉ።
የንግድ ሚዛን ጉድለቱ መስፋት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ማባባሱንም ኢኮኖሚስቶች ይናገራሉ። ለጊዜው መንግስት እዳዎቹን ለመክፈል ከአይ ኤም ኤፍና ከሌሎች አበዳሪ ድርጅቶች ለመበደር ቢችልም፣ እዳው እየሰፋ ሲሄድ ለመከፍል የሚቸገርበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ኢኮኖሚስቶች ይገልጻሉ።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የንግድ ድርጅቶች በውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚቸገሩትም በዚሁ የተነሳ መሆኑን ኢኮኖሚስቶች ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት 5 አመታት አገሪቱ ወደ ውጭ ልካ ካገኘቸው አጠቃላይ ገቢ ይልቅ፣ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአንድ አመት ብቻ ወደ አገራቸው ከሚልኩት ጋር እኩል መሆኑ ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሰረት መሆናቸውን ያሳያል። ባለፉት 5 አመታት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ12 -15 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገራቸው ልከዋል።
No comments:
Post a Comment