ከሰማያዊና ከአንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማህበራት የተሠጠ መግለጫ
ህውሃት/ኢህአዴግ የሚቆጣጠራት የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ለዜጐቿ ምቹ አልሆነችም፡፡ አገዛዙ በራሱ በሚቆጣጠረው የመገናኛ ብዙሃን እንደሚለፈፈው አገሪቱ በሁለት እጥፍ እያደገች ሣይሆን በተቃራኒው ኢትዮጵያ ለዜጐቿ የማትመች፣ ፍትህ የሌለባት፣ ሰው በነፃነት የማይኖርባት፣ ችግርና መከራ የበዛባት፤ ለአብዛኛው ዜጎቿ የማትመች የመከራ ምድር በመሆኗ የአገዛዙን የጭቆና ቀምበር መሸከም ስላልቻለ፣ ኑሮ ስለከበው እልፍ-አእላፍ ዜጐች በስደት መከራ እንዲሰቃዩ ተደርገዋል፡፡ የአገዛዙ ባለስልጣኖች ሠሞኑን በስደተኛ ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን እጅግ አሠቃቂ ግድያ ማውገዝ እንኳን ሲያቅታቸው ተስተውለዋል፡፡ የኢህአዴግ የዘዉግ መንግሥት ዘመንኛ ገዢዎች የተጐጅ ወገኖቻችንን ኢትዮጵያዊነት እውቅና ላለመስጠት የፈለገበት ምክንያት ለሕዝቧና ለአገሪቱ ካላቸው ስር የሰደደ ጥላቻና ግድየለሽነት የመነጨ ነው፡፡ ገዳዮቹ አሸባሪዎች “የጠላታችን የኢትዮጽያ ቤተክርስቲያን የመስቀል ጦረኞች ልጆች” ብለው ሲነግሩን ከሁሉም በላይ ደግሞ የወገኖቻችን ደምና መልካቸው እየታዬ የኢህአዴግ አምባገነን ገዢዎች ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ለመቀበል ተስኗቸዉ ተስተውሏል፡፡ ይህም ድርጊታቸው ኢትዮጵያውያንን እጅግ አሣዝኗል፤ አበሣጭቷልም፡፡ የአዲስ አበባና የአካባቢው ሕዝብ ሃዘኑን ለመግለፅ ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ወደ ጎዳና በመውጣት ምሬቱን ሲያሠማ ተስተውሏል፡፡ ይሁን እንጂ ትናትናና ዛሬ በአዲስ አበባ ሠልፈኞች ላይ እጅግ ከፍተኛ ድብደባ በፀጥታ አስከባሪ ቅልብ ፖሊሶች ተፈጽሟል፡፡ አገዛዙ እራሱ ሠልፍ ጠርቶ መልሦ ሕዝቡን በዱላና በጥይት እያሠቃየው ይገኛል፡፡ በባዕዳን የፈሰሰው ደም ሣይደርቅ ዓለም እንኳን ይታዘበናል ብለው ሣያፍሩ ሣይሰስቱ በሰልፈኛው ሕዝብ ላይ መሣሪያ በመተኮስ ብዙ ወገኖች ከፍተኛ አደጋ ደርሦባቸዋል፡፡ ብዛት ያላቸዉ ሠልፈኞች ታሥረዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፡-
የዚህ ሁሉ የማያልቅ መከራ የዕለት-ተዕለት ክስተት ዋናው ምክንያት አገሪቱ ውስጥ ያለው የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለጥቂቶች ገነት ለብዙሃኑ ገሃነም የሆነች አገር ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ ጀምሮ ፍትሕ የለም፣ ነፃነት የለም፣ ሰዎች ባገራቸው ከቦታ ቦታ መዘዋወር አይችሉም፣ የአገዛዙ ካድሬዎች ሕዝቡን በዘርና በቋንቋ በመከፋፈል እርስ በርሱ እንዳይተማማንና እንዳይግባባ አድርገውታል፡፡ ኢትዮጵያውያን በነፃነት በእኩልነት መብታቸው ተከብሮ የመኖር ዋስትናቸው እንዲረጋገጥና ስደት እንዲቀር እንዲሁም አገራችን የጥቂቶች ሣይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንድትሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነቂስ አገዛዙን መቃወምና ስርዓቱን ከስር መሠረቱ መቀየር ያስፈልጋል፡፡ስለሆነም ኢትዮጵያውያን በውስጥም በውጭም ያሣለፍነው የመከራ ዘመን ከኋላችን እንዲቀር ከተፈለገ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሌላው ዓለም እንደታየው ሁሉ እኛም ዕጅ ለዕጅ ተያይዘን አገዛዙን በመቃወም በጋራ አሽቀንጥረን መጣል ይገባናል፡፡
ድል ለኢትዬጵያ!
የአንድነትና የሠማያዊ ድጋፍ ማህበሮች በሰሜን አሜሪካ አስተባባሪ ኮሚቴ
No comments:
Post a Comment