Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, April 30, 2015

ፖሊስ በ‹‹በሁከትና ብጥብጥ›› ተጠርጣሪዎች ላይ ሦስት መዝገብ አደራጅቻለሁ አለ •እነ ወይንሸት ለሁለተኛ ጊዜ 6 ቀን ተቀጥሮባቸዋል

ፖሊስ በ‹‹በሁከትና ብጥብጥ›› ተጠርጣሪዎች ላይ ሦስት መዝገብ አደራጅቻለሁ አለ
•እነ ወይንሸት ለሁለተኛ ጊዜ 6 ቀን ተቀጥሮባቸዋል
•‹‹ወይንሸት ከአሁን በፊትም ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ስታሸብር ነበር›› ፖሊስ
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ የሽብር ድርጊት ለማውገዝ ጠርቶት በነበረው ሰልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ አስነስታችኋል፤ ተካፍላችኋልም›› በሚል ፖሊስ ባሰራቸው ሰዎች ላይ ሦስት የተለያዩ መዝገቦች ማደራጀቱን አስታውቋል፡፡
ዛሬ ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረቡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ሌሎች በዕለቱ የተያዙ ሰዎችን በተመለከተ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ እንደገለጸው፣ ፖሊስ የራሱን ቡድን በማዋቀር ተጠርጣሪዎችን በሦስት መዝገቦች ስር እንደየተሳትፏቸው አደራጅቻለሁ ብሏል፡፡ በዚህ መሰረት በሶስተኛው መዝገብ ላይ ያካተታቸውን በርካታ ታሳሪዎች አጣርቶ መልቀቁን የገለጸው ፖሊስ፣ በሁለተኛውና በአንደኛው መዝገብ ላይ ባሉት ተጠርጣሪዎች ግን ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጹዋል፡፡


አንደኛው መዝገብ ላይ በእነ ወይንሸት ሞላ መዝገብ 5 ሰዎች የተካተቱ ሲሆን አራቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፤ አንደኛዋ ተጠርጣሪ ደግሞ ፖሊስ የፓርቲው አባል እንደሆነች የሚገልጸው፣ እሷ ግን አባል አለመሆኗን የገለጸች መሆኗን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለሆነም በዚህ መዝገብ የተካተቱት ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ማስተዋል እና የፓርቲው አባል ያልሆነችው ቤተልሄም ይገኙበታል፡፡ ማስተዋል በዛሬው ዕለት ቀደም ብሎ የተሰጠው የቀጠሮ ቀን ስላልደረሰ ፍርድ ቤት አልቀረበም፡፡ ቤተልሄም ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሳልሆን አባል ነሽ እየተባልኩ ምርመራ ይደረግብኛል፤ ሌሊት እየተጠራሁ እመኝ እየተባልኩ ነው›› ስትል ለፍርድ ቤቱ ገልጻለች፡፡
በሁለተኛው መዝገብ ላይ ደግሞ 15 ተጠርጣሪዎች ተካትተዋል፡፡ ፖሊስ በዚህ መዝገብ በተካተቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ክሱን ሲያሰማ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ተጠርጣሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሲያደርጉ ‹ጠንካራ መሪ እንጂ ጠንጋራ መሪ አንፈልግም›፣ ‹ወያኔ አሳረደን›፣ ‹ፍትህ የለም!››› በማለት ሁከት እንዲነሳ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡››
የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በምርመራ ወቅት የገጠማቸውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ ያሰሙ ሲሆን፣ በተለይ የሚደረግባቸው ምርመራ ከፓርቲው ጋር የተያያዘ እንጂ ከተጠረጠርንበት ጉዳይ ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ምርመራው ከጉዳዩ ጋር የሚገናኝ አይደለም፤ ሌሊት ሌሊት እየተጠራሁ ምርመራ ይደረግብኛል፡፡ የፓርቲ አባል መሆን ወንጀል እስኪመስለኝ በፓርቲ አባልነቴ ጫና ይደረግብኛል፡፡ በዚያ ላይ የጤና እከል ገጥሞኛል፤ ህክምና ያስፈልገኛል›› ስትል ለፍርድ ቤቱ ያስረዳችው ወይንሸት ሞላ፣ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት እንዲሰጣት ጠይቃለች፡፡
በሁለቱም መዝገብ የተካተቱት ሁሉም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ በመጀመሪያው መዝገብ ላይ ያሉት እነ ወይንሸት ላይ የምርመራ ስራውን እንዳልጨረሰ በመግለጽ 14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ በተለይ ወይንሸት ሞላ ላይ ፖሊስ፣ ‹‹ከአሁን በፊትም ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ተመሳስላ በመልበስ ስታሸብር ነበር›› በማለት ዋስትና እንዳይሰጥና የጠየቀው የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ በሁለተኛው መዝገብ ላሉት ደግሞ 7 ቀን ፖሊስ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በሁለቱም መዝገብ ላይ በተመሳሳይ የ6 ቀን ጊዜ በመስጠት ለሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች እስር አሁንም እንደቀጠለ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ በትናንትናው ዕለትም ሦስት የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አባላት (አንደኛው አሁን ላይ የሰማያዊ አባል) መታሰራቸው ይታወሳል

No comments:

Post a Comment

wanted officials