Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, April 1, 2015

በሽብርተኝነት የተጠረጠሩት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ተጨማሪ 28 ቀናት ተጠየቀባቸው



‹‹የጦር መሣሪያ በእጃቸው ስላገኘን ተጨማሪ አላቸው ብለን እንጠረጥራለን›› መርማሪ ፖሊስ

‹‹ተጨማሪ ጊዜ የተጠየቀበት ጉዳይ አሳማኝ አይደለም›› የተጠርጣሪዎች ጠበቃ

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ላለፉት 28 ቀናት በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) በእስር ላይ የነበሩት የሰማያዊ ፓርቲ ሦስት አባላት፣ መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው ተጨማሪ 28 ቀናት ተጠየቀባቸው፡፡


በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል ታስረው የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የአደረጃጀት ጉዳይ ምክትል ኃላፊ የነበረው አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ የምክር ቤት አባል የነበረችው ወ/ሪት ኢየሩሳሌም አስፋውና የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴ አባል ነው የተባለው አቶ ፍቅረ ማርያም አስማማው ሲሆኑ፣ መርማሪ ፖሊስ መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት አቅርቧቸዋል፡፡ ባለፉት 28 ቀናት በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሠራውን ለፍርድ ቤቱ በመግለጽ ለተጨማሪ ምርመራ 28 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ የቀረውን ምርመራ በሚመለከት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ የቴክኒክ ምርመራ ማለትም ከኢሜል፣ ከፌስቡክና ከሌሎች በተገኙ ማስረጃዎች ላይ ምርመራዎች እንደሚቀሩት፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮች ስላሉ ተጠርጣሪዎቹ ቢለቀቁ ሊያስጠፏቸው እንደሚችሉ፣ ለሽብር ተግባር የሚውል ገንዘብ በባንኮች የተለዋወጡባቸውን ሰነዶች ከባንኮቹ ተቀብሎ መመርመር፣ የጦር መሣሪያም የተገኘ በመሆኑ ተጨማሪ የጦር መሣሪያ ይኖራቸዋል የሚል ጥርጣሬ ስላለ፣ ተጨማሪ ፍተሻ ስለሚቀር ተጨማሪ 28 ቀናት እንዲሰጠው በድጋሚ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የተቃወሙት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ ዳዊት ነጋሽ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፣ የቴክኒክ ምርመራ ይቀራል በማለት መርማሪ ፖሊስ የጠየቀው የኢሜል፣ የፌስቡክና ሌሎች ማስረጃዎች የሚገኙት በመርማሪ ፖሊስ እጅ ነው፡፡ ግብረ አበሮች አሉ ቢባል እንኳን ተጠርጣሪዎቹ መታሰራቸውን ሲሰሙ አይሸሹም ተብሎ እንደማይገመትም አመልክተዋል፡፡

ለሽብር ዓላማ የሚውል ገንዘብ በባንክ ተለዋውጠዋል የተባለው ሰነድም፣ በሚታወቁ ባንኮችና በኔትወርክ የተያያዙ በመሆናቸው፣ በአንድ ቀን ሊጣራ የሚችል በመሆኑ ደንበኞቻቸውን ለማሰር የሚያበቃ ምክንያት አለመሆኑን በማስረዳት ዋስትና እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡






አንድ የጠብመንጃ ፎቶግራፍና አንድ ማንነቱ የማይታወቅ ግለሰብ ጠብመንጃ ይዞ የሚታይበት ፎቶግራፍ መቅረቡን አስመልክቶ ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜ እንዳይፈቀድ ጠይቀዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ አቶ ብርሃኑና ወ/ሪት ኢየሩሳሌም አንድ ላይ በዳኛ ፊት የቀረቡ ቢሆንም፣ ጠበቃቸው አቶ ዳዊት ካስረዱት በተጨማሪ የገለጹት ነገር የለም፡፡

ተጠርጣሪ ፍቅረ ማርያም ግን ለ24 ሰዓታት መብራት በሚበራበት ክፍል ውስጥ መታሰሩን ገልጾ የዓይን ሕመም እንዳለበት በማስረዳት፣ እንዲስተካከልለት ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡ በቀን ለ15 ደቂቃዎች ብቻ ወደ ውጭ እንደሚወጣ በመግለጽ ሰብዓዊ መብቱን የሚነካ ድርጊት እየተፈጸመበት መሆኑንና ቤተሰቦቹንና የሕግ ባለሙያም እንደማያገኝም አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ሐሳብ ከተቀበለ በኋላ፣ ተጠርጣሪዎቹ የታሰሩበት የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ከቤተሰቦቻቸውና ከሕግ ባለሙያ ጋር እንዲገናኙ እንዲያደርግ መርማሪ ፖሊሱ ለኃላፊዎች እንዲያስረዱና እንዲስተካከልም አዟል፡፡ በመጨረሻም ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርምራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

ሦስቱም የፓርቲው አባላት መቼ፣ የት፣ እንዴትና በማን እንደተያዙና እንደታሰሩ ባይታወቅም፣ በእስር ላይ መሆናቸውንና ፍርድ ቤት ቀርበው 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንደተጠየቀባቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ቁጥር 652/2001 አንድ በሽብርተኝነት በተጠረጠረ ዜጋ ላይ ለአራት ጊዜያት ያህል ለ28 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊፈቅድ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡
Reporter

No comments:

Post a Comment

wanted officials