በፓትርያርኩ እንደራሴ አስፈላጊነት ከስምምነት ተደረሰ፤ “ወቅቱን የጠበቀ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፣ “ቅ/ሲኖዶሱ ተስማምቶ ካልወጣ ለሕዝብም ለሀገርም ጥሩ አይኾንም” ብለዋል
በምልዓተ ጉባኤው ውሎ በተደረሰው መግባባት፤
- የእንደራሴው መመዘኛ፣ ፓትርያርኩን የማገዝ ተግባሩና ሓላፊነት ደንቡ በቀጣዩ ጉባኤ ይታያል
- በልዩ ጽ/ቤቱ፣ ለሥራ ዕንቅፋት የኾኑ ሰዎች ተነሥተው፣ እንዲስተካከልና እንዲረጋጋ ይደረጋል
- የገዘፈ ችግር ያለበት የአ/አበባ ሀ/ስብከት፣ በረዳት ሊቀ ጳጳስ እየተመራ ሕጉ የሚሻሻል ይኾናል
- ፓትርያርኩ፣ ስለወቅታዊ ኹኔታዎች ያላቸው አረዳድ ውስንነት ምደባውን አስፈላጊ አድርጎታል
- ተግባር የሚሻው የልዩ ጸሐፊውና የጨለማ አማካሪዎች ግፍና አውዳሚነት አጽንዖት አግኝቷል፡፡
ሚኒስትሩ ስለአጀንዳዎቹና በውሏቸው እንደታዘቡት፡-
- ከጥቅማጥቅም ጋር ሳይገናኙና ራስን ማዕከል ሳያደርጉ ጤናማ ውይይት ሊካሔድባቸው ይገባል
- ጠንካራ ቅ/ሲኖዶስ፤ ጠንካራ አደረጃጀትና ፖሊሲ፤ አስፈጻሚና ፈጻሚ የሰው ኃይል ያስፈልጋል
- እናንተ ናችሁ እኛን መደገፍ ያለባችሁ፤ ቤቱ ተኣማኒነቱና ተጽዕኖ ፈጣሪነቱን ማጣት የለበትም
- በጨለማ የሚያማክሩት እነማን ናቸው? በእምነት፣ በምግባርና በዕውቀትስ ለቤቱ ይመጥናሉ?
- አለመተማመን ይታያል፤ ይህ ፍጹም ክፍተት አምጥቷል፤ በጋራ መሥራት ይጠበቅባችኋል፡፡
የሚኒስትሩ እንደታዛቢ መጠራት፡-
- ከቅ/ሲኖዶስ ልዕልና፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያንና ከሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች አንፃር መነጋገርያ ኾኗል
- የፓትርያርኩ ግትርነት ዋናው መንሥኤ ቢኾንም፣ ምልዓተ ጉባኤው በጥሪው መስማማቱ አስቆጥቷል
- ጥሪው፥ “ኃይል አለኝ” ሲሉ የዛቱት ፓትርያርኩ፥ ለማስፈራሪያ በሚጠቅሱትና አዘውትረው ለርምጃ በሚማፀኑት አካል ፊት፣ ችግራቸውን የማስረዳትና ምልዓተ ጉባኤው በመጨረሻ የሚወስደውን አቋም ጠብቆ የግንቦት 2001 ዓ.ም. ዓይነቱ ግርግር ለመፍጠር የተዘጋጀውን የጨለማ ቡድን የማጋለጥ ዓላማ እንደነበረው ተጠቁሟል፤
- በጥሪው፥ በእምነቶች የሰላምና የመግባባት ጉዳዮች እንዲሠራ ተልእኮ የተሰጠው ሚኒስቴር ሚኒስትሩ፣በሃይማኖታቸውና ለቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ያላቸው ቅርበት ከግምት መግባቱ የተጠቀሰ ሲኾን፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ፥ የቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣንና ተግባር ከፓትርያርኩ ሥልጣንና ተግባር ጋር እየተነፃፀረ በብፁዕ ዋና ጸሐፊው ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፤
- “ለምን ተጠራን አንልም፤ እምነታችን ነው፤ ቤታችን ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፣ ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ያደረገችውን አስተዋፅኦ በመዘርዘር፤ ተኣማኒነቷንና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን እንዳታጣ፣ “ወቅቱን የጠበቁ ናቸው” ባሏቸው አጀንዳዎች ላይ በመተማመን ጤናማ ውይይት ማካሔድ እንደሚያስፈልግ ሐሳብ ሰጥተዋል፤
- “ቤተ ክርስቲያኒቷ ከላይ እስከ ታች መጠናከር እንዳለባት ይገባኛል፤” ያሉት ሚኒስትሩ፣ አጀንዳዎቹም የተቀረፁት ከዚኽ አንፃር እንደሚመስላቸው ጠቅሰው፣ የእንደራሴ ምደባው ደንብና አፈጻጸሙ አስቀድሞ ተጠንቶና ከዋናው ሕግ ጋር ተጣጥሞ ለቀጣዩ ምልዓተ ጉባኤ ቢቀርብ፤
- የአ/አበባ ሀገረ ስብከት የከበደና የገዘፈ ችግር እንዳለበትና መንግሥትም በቅርበት እንደሚያውቀው፤ ችግሩ፥ ለጊዜው፣ ባለው ሕግ ሰንሰለቱ ተጠብቆ እንዲፈታና በቀጣይም ከተጠሪነት አኳያ[የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የሚለው] በማገናዘብ ቢታይ፤
- በልዩ ጽ/ቤቱ ለሥራ ዕንቅፋት የኾኑ ሰዎች እንዲነሡ ቀድሞም ከፓትርያርኩ ጋር ተነጋግረውበት እንደነበርና በአጀንዳ መካተቱ ትክክል እንደኾነ፤ መወሰንና በጎ ተጽዕኖ መፍጠር በሚችል የአስተዳደር ሰው ቢደራጅና ቢጠናከር የሚሉ ሐሳቦችን ሰጥተዋል፤ ቅዱስ ሲኖዶስ በእነዚኽ ጉዳዮች ላይ ተስማምቶና ወስኖ ካልወጣ፣“ለሕዝቡም ለሀገርም ጥሩ አይኾንም” ሲሉም መክረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment