Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, June 8, 2016

ጉዞ ወደ ‘ሲቪክ’ ብሔርተኝነት by ሔኖክ አክሊሉ

የአፍሪካ ቀንድ በየጊዜው እያስተናገደ ካለው እጅግ ተለዋዋጭ እና የአገሮች መበታተን/መፍረስ አደጋን በማጤን፣ ሕመማቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት፣ ከተቻለም መድኃኒቱን ለማግኘት ውስጣዊ የፖለቲካ ማንነታቸውን በተለይም ከአገራዊ ብሔርተኝነት (Nationalism) አንጻር መመልከቱ ጠቃሚ ነው። በዚች አጭር ጽሑፍ የአገራችንን መፃኢ ዕድል (የነብይነት ፀጋ ባይኖረኝም) ምን ሊሆን ይችላል? በተለይም ዋነኛ ከሆኑት ሁለት የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ትርክት መውደቅ እና በመነሳት አንፃር ለመዳሰስ እሞክራለሁ። ጽሑፉ የትናንት ወይም የዛሬ ትክክል/ስህተት ነው ከሚል ድምዳሜ የሚነሳ ሳይሆን ከሁለት አንዱ ላይ የምር መርገጥ አለመቻላችን የሚደቅነውን የመበታተን አደጋ በመመርመር “የአዲስ” ብሔርተኝነት አስፈላጊነትን ለማሳየት ትሞክራለች።
አገራዊ ብሔርተኝነት ሲፈተሽ
አሳ ተፈጥሮ የሚኖረው በውኃ ውስጥ እንደሆነ ሁሉ አገሮች ተፈጥረው የሚኖሩት ብሔርተኝነት ተብሎ በሚጠራ ውኃ ውስጥ ነው፤ ከዚህ መኖሪያቸው ከወጡ ወይም መኖሪያቸው ከፈረሰ ሕልውናቸው በጥያቄ ውስጥ ይገባል። የዘርፉ አጥኚ የሆኑት “ሱዩን ማ” አገራዊ ብሔርተኝነት በቀዘቀዘ መጠን የመበታተን አደጋ የሚፈጥረውን ያህል፣ በጋለ መጠን ደግሞ ሌሎች አገሮች ሕልውና ላይ የሚደቅነው ፈተና ከባድ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።
በብሔርተኝነት ሥም ያልተከፈተ ጦርነት፣ ያልተፈፀመ ግፍ፣ ያልፈሰሰ ደም በተለይም ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ማግኘት ትልቅ ምርምር የሚጠይቅ ነው። የጀርመን ብሔርተኝነት፣ የጣሊያን ፋሺዝም፣ የባልካን አካባቢ ብሔርተኝነት፣ ወጣት ቱርኮች በአታቱርክ እየተመሩ ዘመናዊ አገራቸውን የፈጠሩበት... ሁኔታ የሰውን ልጅ ሕልውና የተፈታተኑ የጭንቅ አጋጣሚዎች ነበሩ። ስለሆነም ብሔርተኝነት በጥንቃቄ ካልተያዘ አገራትን የማፍረስ ማጥ ውስጥ የመክተት ወይም እንዳዲስ የመፍጠር ታላቅ አቅም ያለው ኃይል ነው።
ብዙ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ኤሪክ ሀብስባውን “Nations and Nationalism since 1780” በሚለው ጽሑፋቸው ብሔርተኝነት አገሮች አሁን በምናውቃቸው ባሕሪ እንዲፈጠሩ ማድረጉን እና ተራማጅ የሆነው ቡርጅዋ ክፍል ዕድገት ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ይነግሩናል። በተለይም በዘመናችን አገነዛዘብ እንግሊዝ የመጀመሪያ አገራዊ ብሔርተኝነትን ያስተናገደች እንደሆነች ጥናቶች ያመላክታሉ።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ብሔርተኝነት ምንድን ነው በሚለው ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም ጠቅለል ተደርጎ ግን ጂዎርጅ ሶሬንሰን “ብሔርተኝነት እውነት ወይም በተስፋ ነጻነት፣ አንድነት እና ማንነት የተረጋገጠበት አንድ አገር ለመመሥረት በሕዝብ ሥም የሚደረግ ትግል እና አይዲዎሎጂ ነው” በማለት ያስቀመጡትን ብየና ለዚህ ጽሑፍ ግንዛቤ ልንወስደው እንችላለን። ብሔርተኝነት ሕዝባዊ ትግልን እና አንድ ዓይነት የሆነ አመለካከትን በዋነኝነት ያቀፈ ከሆነ ዓይነቱን ደግሞ በሦስት ከፍለን ልናየው እንችላለን።

የአገራዊ ብሔርተኝነት ዓይነቶች
አገራዊ ብሔርተኝነት ብዙ ዓይነት ሊሆኑ ቢችሉም ብዙ ተቀባይነትን ካገኘው ኬላስ ጄ “The Politics of Nationalism and Ethnicity’’ ከሚለው ሥራቸው ወስደን እንየው። የመጀመሪያው “ባሕላዊ ብሔርተኝነት” እየተባለ በዘርፉ የሚታወቅ ሲሆን መገለጫውም የአንድ አገር አመጣጥ በረጅም የታሪክ ፍሰት አንድ ብሔር ወይም የተለያዩ ሕዝቦች ተሳስረው በሒደት ወደ አንድ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብነት እንደመጡ የሚቆጥር ነው። ሕዝቦቹ በዚህ ረጅም የታሪክ ዕድሜ የሚጋሩት የጋራ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ጠላት፣ ጀግንነት፣ ባንዲራ፣ ድል፣ ምልክት... ያፈሩ በመሆናቸው ጊዜያቸውን ጠብቀው ወደ አንድ አገርነት የሚደርሱ አድርጎ ይረዳቸዋል። ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው የጋራ ታሪካቸው አንዱ አንዱን የመጨቆን ገጽታ ብቻ ሳይሆን ያለው ባጠቃላይ በተለያየ መልኩ እና ጊዜ ጭቆናው እና ትግሉ ከሁሉም መልክ እና ቀዳሚ ሆኖ ይታያል። እነዚህን ዓይነት ሕዝቦች ጠንካራ የትናንት የታሪክ ሰንሰለት የሚያስተሳስራቸው ስለሆነ ዛሬ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንደ አላፊ ነገር እንጂ ሁል ጊዜ በአብሮነታቸው ውስጥ የሚኖር ማንነት አድርገው አይቆጥሩትም። የዚህ ብሔርተኝነት አባልነት ሙሉ በሙሉ ደም ላይ ያላተኮረ፣ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ፈቃደኝነትም ላይ ያልተመረኮዘ ባሕል፣ ደም እና ታሪክ በተወሰነም ደረጃ ከፈቃደኝነት ጋር ተጋብተው የሚወልዱት ልጅ ነው። እንደዚህ ዓይነት ብሔርተኝነት አልፈው አገራዊ ሕልውናቸውን ካገኙ አገሮች ውስጥ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ግብጽ፣ ቱርክ፣ ቻይና እና ሌሎችንም ኃያላን አገሮች ልንጠቅስ እንችላለን።
ሁለተኛው ዓይነት ደግሞ “ዘውጋዊ ብሔርተኝነት” ተብሎ የሚታወቀው ነው። ይሄን ብሔርተኝነት አንዳንዶች “የጎሳ ብሔርተኝነት” ሲሉ የሚጠሩት ሲሆን አገራዊ ብሔርተኝነቱ ከዘውግ አንፃር የተቃኘ ነው። አገርን የሚመሠርቱት አንድ ዘውግ ወይም ብዙዎች ሆነው ነው። ብሔርተኝነት መሠረቱ ዘውግ ስለሆነ ደም፣ ቋንቋ እና ባሕል ትልቅ ትኩረት አላቸው። የብሔርተኝነቱ መሠረት ዘውግ ስለሆነ አባልነት በዋነኝነት በደም እና ቋንቋ ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ ዓይነት አገራዊ ብሔርተኝነት የተደራጁ አገሮችን ስናይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የቀድሞ የሶቭየት ኅብረት አባል አገራት የነበሩትን እንደ ታጃኪስታን፣ ኡዝቤኪስታን፣ ቱርክሜኒስታን... የመሳሰሉትን እናገኛለን። ነገር ግን እነዚህ አገሮች የመሠረቱት የዘውግ ብሔርተኝነት ሁሉንም ለምሳሌ ሕዳጣን ሩሲያውያንን ወይም የእስልምና ማንነትን ስለማያካትት አገር ግንባታቸውን ፈታኝ አድርጎባቸዋል።
የመጨረሻው ደግሞ “(ሲቪክ/የዜግነት) ፖለቲካዊ ብሔርተኝነት” የሚባለው ሲሆን ትላንትም ሆነ ደም ላይ ያልተኛ ብሔርተኝነት ነው። ሕዝቦች ረጅም የጋራ ትስስር ኖራቸውም አልኖራቸውም አገራዊ መሠረታቸው ዕኩልነት፣ ነጻነት፣ ወንድማማችነት ላይ ተመሥርቶ አብሮነትን ይፈጥራል። ይህ ዓይነቱ ብሔርተኝነት በተለይ የፈረንሳይ አብዮትን እና የዴሞክራሲን ፀሐይ መውጣት ተከትሎ የመጣ ነው። ሕዝቦች ሁሉንም በሚያስማማ ሕገ መንግሥት እና እርሱን ተግባራዊ በሚያደርጉ አገራዊ ተቋማት ጥላ ሥር የጋራ ጎጇቸውን ይቀልሳሉ። በዚህ ሥር ለምሳሌነት ከሚጠቀሱት አገሮች ውስጥ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና አብዛኛው የቅኝ ግዛት ልጆች የሆኑትን አፍሪካ አገሮችን ይጨምራል። ነገር ግን ይህ ዓይነት ብሔርተኝነት ሁሉንም ዜጎች ሊያስተናግድ የሚችል የመጫወቻ ሜዳ እስከሌለው ድረስ የጋራ ሕንፃቸው በቀላሉ አደጋ ሊገጥመው ይችላል። ለማሳየት ያክል ብዙ የአረብ አገሮች ዘንድ ይሄ መሠረታዊ የአገር እና የዜግነት ማንነት ስለሌለ ማባሪያ በሌለው ግጭት ውስጥ ሲሽከረከሩ ይታያሉ።

ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት፤ ትናንት እና ዛሬ
ወደ አገራችን መጥተን በየትኛው የብሔርተኝነት ጥላ ሥር እንደተሰባሰብን ስንቃኝ እስከዛሬ የነበሩትን በሁለት ከፍለን ልናይ እንችላለን። ቀደም ሲል የነበሩት መንግሥታት በባሕላዊ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጥላ ሥር አገራዊ ማንነትን ለማሰባሰብ ትልቅ ተጋድሎ አድርገዋል። ዐፄ ኃይለሥላሴ የአገር ግንባታ ዕቅዳቸውን በተለይም ከጣሊያን ወረራ በኋላ በሰለሞን ዘውድ ስርዓት እና በእሳቸው መሪነት፣ በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት፣ የአማርኛ ቋንቋ፣ የጋራ የውጭ ጠላት ላይ የተቀናጀነው ድል... በማሳየት የአገሪቱን ማንነት ከእነዚህ ነገሮች አንፃር ለማስቀጠል ትልቅ ሙከራ አድርገዋል።
ነገር ግን ይሄ ብሔርተኝነት የግራ አመለካከት ማቆጥቆጥን እና አፍሪካ አገሮች ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ በትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቷል። በተለይም አብሮ የመኖር ታሪካችን የመቻቻል ሳይሆን አብዛኛውን ሕዝብ ጥቂቶች በአንድ ሃይማኖት፣ ቋንቋ ሥም ሲገዙት የነበረ መሆኑን በአሁኑ አጠራር “አማራ” የነበረው ዋለልኝ መኮንን “የብሔረሰብ ጥያቄ በኢትዮጵያ” ሲል በሰየመው ጽሑፍ የዘመኑን መንፈስ ገልጿል።
አመለካከቱም ከሶሻሊዝም ርዕዮት ዓለም መስፋፋት እና ከፀረ ቀኝ ግዛት ትግል ጋር ሥር በመስደድ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተለያዩ ፖለቲካ ቡድኖች መፈጠር ምክንያት ሆኗል፤ የዚህ ውላጅ የሆኑትንም እንደ ኦ.ነ.ግ.፣ ኢ.ሕ.አ.ፓ.፣ መ.ኢ.ሶ.ን.፣ ሕ.ወ.ሓ.ት. ሻዕቢያ... ድርጅቶች ለመፍጠር በቅቷል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች እና አይዲዎሎጂዎች የኢትዮጵያን የነበረ ባሕላዊ ብሔርተኝነት በመጠየቅ የአዲስ አገራዊ ማንነትን አስፈላጊነት አራምደዋል።
ከ17 ዓመታት መራራ ትግል በኋላ ለሥልጣን የበቃው ሕ.ወ.ሓ.ት./ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. አገሪቱ ለረጅም ዘመን የነበራት ታሪክ በአንድ ብሔር እና ሃይማኖት የበላይነት ላይ የተመረኮዘ የእስር ቤት ታሪክ በመሆኑ አዲስ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የመመሥረት አስፈላጊነትን ላይ በማተኮር ቀድሞ የነበረውን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በመጣል አዲስ አገራዊ ማንነት እና ግንባታ ላይ ተረባርቧል። ይህ አዲስ አገራዊ ማንነት ዘውግ ላይ የተመሠረተ ሲሆን አዲሲቷን ኢትዮጵያን የመሠረቱትም ሆነ አባል የሆኑት የዘውግ ቡድኖች ናቸው። ለዚህ የበለጠ አስረጅ የሚሆነን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት መረቀቅ እና ሥራ ላይ መዋል ሲሆን በመግቢያ ላይ “መጪው የጋራ ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነው የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል” እንደሆነና ይህም የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ዕኩልነት ላይ ተመርኩዞ አዲስ የሕዝቦች ቃል ኪዳን የሆነ ሕገ መንግሥት በማፅደቅ እንደ ተጠናቀቀ ያስቀምጣል።
ይህ ቀድሞ በነበረው ባሕላዊ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት መቃብር ላይ የተመሠረተው ዘውጋዊ ብሔርተኝነት (ገዥዎቻችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እያሏት መጥተዋል)፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ዕኩልነት በማረጋገጥ ዘውጎችን ከአገራዊ እስር ቤት አውጥቶ “ነጻነት” ሰጥቷቸዋል። ለባለፉት 25 ዓመታት የቀን ተቀን እንቅስቃሴው እና ፍሬውን ሲታይ የቆየው የዘውጌ ብሔርተኝነት በወረቀት ላይ የሰፈረውን አዲስ አገራዊ ማንነት ለማሳካት ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ቅርጽ በአገሪቱ ዘርግቷል። ከዛም በተጨማሪ ይሄን የሚጠብቁ ወሳኝ ተቋማትን መሥርቶ ሥራ ላይ ለማዋል ተንቀሳቅሷል። በዚህ ብሔርተኝነት እሳቤ ለምሳሌ የኦሮሞ ኢትዮጵያዊነት መሠረቱ ትናንት አባቶቻችን በጋራ አድዋ ላይ ያደረጉት የጀግንነት ተጋድሎ ሳይሆን አሁን የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብቱ ስለተከበረለት እና የሥልጣን ባለቤት በመሆኑ ነው። ይሄን ማድረግ ካልተቻለ ግን መብቱን እስከ መገንጠል በመራመድ ሊያስከብር ይችላል።

የኢትዮጵያ ሕልውና በሽታ
ወደ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ዋ ኢትዮጵያ ስንመጣ የዘውግ ብሔርተኝነቱ ሁለት ዋነኛ ፈተናዎች አላሳልፍ ብለውት ጠፍረው ይዘውታል። የመጀመሪያው ፈተና የሚመነጨው መንግሥት ራሱ ተስፋ የገባውን ዘውግ ብሔርተኝነት ማክበር አለመቻሉ ላይ ነው። የዘውግ ብሔርተኝነት መሠረት የሆኑት የራስን ዕድል በራስ መወሰን፣ የፌዴራል ስርዓቱ ከፌዴራል መንግሥቱ እና ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሕ ውጪ ባልተማከለ መንገድ መሥራት እና የዴሞክራሲያዊ እሴቶች አለመከበር ነው። እኝህ የዘውግ ብሔርተኝነት እሴቶች አለመከበር ከሚፈጥሩት የራሳቸው ቅሬታ ባሻገር ከአገራዊ ግንባታ ጋር በእጅጉ እንደተቆራኙ ከፍ ብሎ ያለው ገለጻ አስፍሮታል። ታዲያ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ እሴቶች ካልተከበሩ (EPRDF’s Ethiopian Ethnic Nationalism lacks performance legitimacy) የአገር ማንነት አደጋ ውስጥ ገባ ማለት ነው። ይህ በሕገ መንግሥቱ የታተመው አዲሱ ኢትዮጵያዊ የዘውግ ብሔርተኝነት እነዚህን ጥያቄዎች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መመለስ ሳይችል የሚያፈርስ ከሆነ ቀድሞ ከነበረው “ያረጀ” አቁማዳ የሚሻለው በምንድን እንደሆነ ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የዘውግ ብሔርተኝነት የሚያስነሳው ችግር፣ መሠረቱ የዘውግ ማንነት ላይ በመሆኑ ሁሉም የፌዴራሉ አካል የሆነ ዘውግ፣ ትኩረቱ በራሱ ዛቢያ ላይ ብቻ ስለሚሆን አንድ የጋራ አገር የመመሥረት ጉዳይ ቸል ይባላል፤ እንዲሁም አንዳንዴ አገራዊ አንድነትን ማናናቅ ለፖለቲከኞች ያለበትን የዘውግ ቡድን ጥቅም የበለጠ ያስጠበቀ ስለሚመስል ለተቀባይነት ሲሉ ልኂቃን ይጠቀሙበታል። አንድ ከሚያደርጉ ነገሮች ይልቅ የሚለያዩ ጉዳዮች ቅድሚያ ቦታ ስለሚሰጣቸውም በሒደት የኢትዮጵያ አንድነት እየላላ እና እየፈረሰ ይመጣል።
ስለሆነም አገራችን መንታ መንገድ ላይ ቆማ ትዋልላለች ማለት ነው። በአንድ በኩል ቀድሞ የነበረው ባሕላዊ ብሔርተኝነቱ ተመትቶ አፈር እንዲበላ ተደርጓል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አዲሱ የዘውግ ብሔርተኝነቱ መተግበር አቅቶት ነዳጅ ጨርሶ ቆሟል። አገራችን ታዲያ በአሁኑ ወቅት ወይ የሚያስማማን አንድ አገራዊ ታሪክ የላት፣ ካልሆነም ደግሞ አዲሱ የተመሠረተው ዘውጋዊ ብሔርተኝነቱ የብሔር ብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት ለሁሉም ‹አሰባሳቢ ማንነት› ሆኖ ከወሬ ባለፈ ካልተረጋገጠ የሚቆመው በየትኛው መሠረት ላይ ነው?

መውጪያው መንገድ ምን ይሆን?
ከላይ እንደተቀመጠው ይሄ አሸዋ ላይ የተሠራው ቤት ነፋስ ሲመታው አወዳደቁ ታላቅ ስለሆነ ከዚህ ለመዳን አንድ አማራጭ ሊኖረው ይችላል። በቅድሚያ ግን አማራጭ ሊሆን የማይችለውን እንመልከት፤ ይህም ተለያይቶ የራስን ጎጆ መመሥረት ነው። ካለን ጥልቅ ዘርፈ ብዙ ትስስር አንፃር ይሄን “አማራጭ” ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር ቡናን ከወተት ከተሠራ ማኪያቶ ውስጥ ለመነጠል እንደመሞከር ስለሆነ ያለ ምንም ጥርጥር ወደማያባራ ግጭት ውስጥ መግባታችን አይቀርም። ከዚህም በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድ ተገንጥለው አገር በመመሥረት የተሻለ ነገር ለመፍጠር የተሞከረባቸው እንደ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ያሉ የምድር ሲኦሎች ይሄን አማራጭ የበለጠ እንድንጠይቅ ያደርጉናል። ይህም ቢሆን ቀላል በማይባሉ ኃይሎች መንገዱ እየተሞከረ ይገኛል።
የማይሆነውን ትተን ወደ ተሻለው አማራጭ ስንመጣ መፍትሔ የሚሆነው አገራዊ ግንባታውን እና ማንነቱን ሁሉንም ሊያግባባ በሚችል አዲስ ብሔርተኝነት ላይ መመሥረት ነው። ይህ ብሔርተኝነት ደግሞ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው የዜግነት/ሲቪክ ብሔርተኝነት ነው። ወደ እዚህ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ዜጎች እና ቡድኖች በዕኩልነት የሚያስተናግድ ምዕራፍ እስካልተሸጋገርን ድረስ አገሪቱን ቀደም ሲሉ በነበሩት ብሔርተኝነቶች ለመምራት መሞከር አንዱን ጥሎ ሌላውን ማንሳት ስለሚሆን ልብሱ ለሁሉም ዜጋ አይበቃም።
ነገር ግን  ይህ ብሔርተኝነት ላይ በሁሉም ልሂቃን ዘንድ ስምምነት መፍጠር እና እርሱ ጋር ለመድረስ የሚደረገው ጉዞ አሁን በአገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ደም ተሻግሮ መጓዝን የሚጠይቅ መራራ እና ረጅም ዳገት ነው። ይሄን የአንድ አገር መግባባት ቃል ኪዳን ለመፍጠር ሁሉም ኃይሎች የተወሰነ የሚተውት እና የሚያገኙት ትርፍ የሚፈጥር በመሆኑ ፍትሓዊ ቢሆንም በከባድ ፈተናዎች የታጠረ መሆኑን ልብ ማለት ያሻል።
ሲጠቃለል የእስከዛሬው ኢትዮጵያዊነት መሠረት የሆኑት ሁለቱ ብሔርተኝነቶች አፈር ስለበሉ፣ ማንነታችን መሠረት የሌለው አየር ላይ ያለ ግንባታ ሆኗል። ኢትዮጵያጵያም ባሕላዊ ብሔርተኝነትን ጥላ ወደ ዘውግ ብሔርተኝነት እንደመጣች ሁሉ አሁን ደግሞ ሁላችንንም የሚያሰባስብ እና የማያፈስ የዜግነት ብሔርተኝነት የሚያስፈልጋት የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
ሔኖክ አክሊሉ
ሔኖክ አክሊሉ የሕግ አማካሪና ጠበቃ ነው፡፡ በኢሜይል አድራሻው henoklawyer@gmail.com ሊያገኙት ይችላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials