Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, June 8, 2016

ከአስመራ አገዛዝ ጋር በሽርክና ለሚሰሩ ኩባንያዎች፣ የታንታለም ልማትን ለማቀራመት ሩጫው ለምን አስፈለገ?

በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የትውውቅ ትስስር ከጠለፋቸው መስሪያቤቶች በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ማዕድን አክሲዮን ማሕበር ነው። ይህን “ተቋም” በ1982 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ የማምረት አቅምን ለመጨመር የተቻለውን ከነውስንነቱ አበርክቷል።
መንግስት ከረጅም ጊዜ አንስቶ ማዕድኖችን በጥሬው ለዓለም ገበያ ከማዋል ዕሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ግልፅ ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ ከጀመረ ቆየት ብሏል። ከኢኮኖሚና ከደህንነት አንፃር ስትራቴጂክ ማዕድኖች ተብለው ከሚቀመጡት መካከል አንዱ የታንታለም ማዕድን ነው። ይህንን ማዕድን ዕሴት ጨምሮ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በኩል ከፍተኛ ጥረት መደረጉ አይዘነጋም። ተወዳዳሪ ኩባንያዎች ላለመቅረባቸው ኤጀንሲው ብዙ ምክንያቶች ሊያቀርብ ቢችልም ዋናው ምክንያቱ ግን፣ ከመንግስት ፍላጎት በላይ የአንዳንድ ግለሰቦች ፍላጎት ገዝፎ መውጣት መሆኑን ከዚህ በፊት ባሰፈርናቸው ጽሁፎች ማሳየት ችለናል። እነዚህ ግለሰቦች የመንግስት የቢሮክራሲ አሰራርን የሚጠቀሙ በመሆናቸው በቀላሉ ሊደርስባቸው አልተቻለም።
ከዚህ በፊት በታንታለም ልማት ላይ በተደጋጋሚ በሚወጡ ጨረታዎች ላይ የሚፈጸሙ የቢሮክራሲ ሙስናዎችን ያስታወሰን ተመሳሳይ ድርጊት ለዚህ ጽሑፍ መነሻችን ነው። ወደኋላ መለስ ብለንም የኢትዮጵያ ማዕድን አክሲዮን ማሕበር ከአንድ ኩባንያ ጋር የተቀናጀ የሙስና አሰራር መፈጸሙን የሚያሳይ ማሳያ አቅርበን ወደዋናው ፍሬ ነገር እንገባለን።
የኤሌኒቶ ቅሌት እና የ15 ሚሊዮን ብር ጥናት
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አስቴር ማሞ የሚመራው የፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ታንታለምን ለማልማት ከእስራኤሉ ኤሌኒቶ ኩባንያ ጋር የቀጥታ ድርድር እንዲደረግ መመሪያ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው። እንደሚታወቀው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የታንታለም ድንጋይ ዕሴት ሳይጨመርበት ወደ ውጪ ገበያ እንዳይቀርብ መመሪያ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ነበር ለውጭ ኩባንያዎች ግልፅ ጨረታ መውጣት የጀመረው። ለውድድር ከቀረቡት ሁለት ኩባንያዎች መካከል ኤሌኒቶ የተሻለ በመሆኑ ለቀጥታ ድርድር የተመረጠው መባሉን ከኤጀንሲው በወቅቱ ሰምተናል።
ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ጋር ለድርድር የቀረበው ኤሌኒቶ ኩባንያ ያልተጠበቀ የድርድር ሰነድ ይዞ መቅረቡ አስደንጋጭ ክስተት ነበር። ይኽውም፣ በኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማሕበር በ15 ሚሊዮን ብር የተጠና ሰነድን፣ በራሱ በኤሌኒቶ ኩባንያ የተጠና ሰነድ አድርጎ ከመንግስት አካሎች ጋር ለመደራደር ቀርቦ ነበር። የአክሲዮኑን ማሕበር የቅድመ አዋጪ ጥናት ሰነድ በቀጥታ ከመውሰድም በላይ በአዋጭነት ጥናት ሰነዱ ላይ ስህተት መሆናቸውን አረጋግጦ አክሲዮኑ የለወጣቸውን የቴክኖሎጂ አማራጮችን ሳይቀር ገልብጦ ለድርድር መቅረቡ በወቅቱ ከፍተኛ አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር።
ይህንን 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመንግስትን የአዋጪነት ጥናት ሰነድ ለኤሌኒቶ አሳልፎ የሰጠ አካል እስካሁን በኃላፊነት የተጠየቀ የለም። በኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማሕበር ዋና ሥራአስኪያጅ ዶክተር ዘሪሁን ደስታ ለሰንደቅ ጋዜጣ በፃፉት ደብዳቤ “ከአክሲዮን ማሕበሩ ባልታወቀ መንገድ ካለፈቃድ ተወስዶ እንደራሱ አድርጎ ቀርቦ ነበር” ከማለታቸው ውጪ ተጠያቂ ያደረጉት አካል የለም። “ባልታወቀ መንገድ” በሚል አባባል ብቻ የሚታለፍም አይደለም። በጉዳዩ ላይ እጃቸው ያለበት የአክስዮን ማኅበሩ የሥራ ኃላፊዎች ጉዳያቸው ተጣርቶ ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል።
ይህንን የምንለው ከኤሌኒቶ ጋር የተቀናጀ የሙስና አሰራር የስራው አካል ተጠያቂ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የታንታለም ልማት የድርድር ሒደት ለማስተጓጎል የአክሲዮኑ አባላት አይራወጡም ነበር ከሚል ቀና መነሻ ነው።
በወቅቱ ለድርድር የቀረበው ኩባንያ በምዕራብ አፍሪካ ላይቤሪያ የነበረው የኢንቨስትመንት ታሪክን የተበላሸ መሆኑን ዘግበናል፣ ሰሚ ግን አላገኘንም ነበር። ኤሊኒቶ በአፍሪካ ውስጥ በማንኛውም መንገድ በማዕድን ቁፋሮ ስራ ላይ የተሰማራ ኩባንያ አለመሆኑን፤ በሽርክና አብሮት የሚሰራውም ኤች ሲ ስትራክ የተባለው ኩባንያ ታንታለምን በዓለም ገበያ ውስጥ በመግዛት የሚታወቅ እንጂ ማዕድን በማንጠር የሚያመርት ኩባንያ አለመሆኑን፤ እንዲሁም ኤሌኒቶ በሀገረ ላይቤሪያ የብረት ማዕድን ቆፍሮ በማውጣትና ከሌሎች ውህዶች በመለየት ብረት ለማምረት ከላይቤሪያ መንግስት ጋር ውል የፈጸመ ተቋም ነበር። ሆኖም ግን ከላይቤሪያ መንግስት ፈቃድ ተሰጥቶት ወደ ምርት ይገባል ተብሎ ሲጠበቅ በአስራ ሁለት ወር ውስጥ የተሰጠውን ፈቃድ እና የብረት ማዕድን የሚገኝበትን ቦታ ለሕንድ ኩባንያ ሸጦ መውጣቱን መዘገባችን የሚታወስ ነው።
በመጨረሻም ኤሌኒቶ ወደ ድርድር ውስጥ እንዲገባ ቢደረግም፤ መንግስት ከኤሌኒቶ ጋር የሚደረገው ድርድር እንዲቋረጥ መመሪያ አስተላልፏል። በድጋሚም ለኤሌኒቶ እድል ለመስጠት የተንቀሳቀሱ ባለስልጣናት መኖራቸውንም ማስታወሱ ተገቢ ነው።
አዲስ አልሚ ፍለጋ
መንግስት አዲስ ኩባንያ ፍለጋውን አላቋረጠም። ጥረቱን ገፍቶበት ከአንድ ከአውስትራሊያ ኩባንያ ለረጅም ጊዜ ውይይት አድርጎ ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛል። ይህንን ኩባንያ ከፋይናንስ፣ ከቴክኖሎጂ እና ከልምድ አንፃር እንዲያጠኑት ኃላፊነት ወስደው የነበሩት በማዕድን ሚኒስትሩ በአቶ ቶሎሳ ሻጊ የሚመሩ የመንግስት የተለያዩ መስሪያቤቶች ተወካዮች እና ባለሙያዎች የተካተቱበት አጥኝ ቡድን ነበር።
በተሰየመው አጥኝ ቡድን ውጤት መሰረት ኩባንያዉ በኢትዮጵያ ውስጥ ታንታለምን ማልማት የሚችል ሙሉ አቅም ያለው መሆኑን አረጋግጠው ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ሪፖርት አድርገዋል። ከዚህ ሪፖርት በኋላ አዲስ የመንግስት የመዋቅር አደረጃጀት በመፈጠሩ የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማሕበር አዲስ በተዋቀረው በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ስር እንዲሆን ተደርጓል።
ይህም በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ደሚቱ ሃምቢሳ ቦንሳ በሰጡት መመሪያ ከአውስትራሊያው ኩባንያ ጋር ታንታለምን ለማልማት መስሪያቤታቸው ድርድር ለማድረግ እየሰራ ነው። ሚኒስትሯም በቀጥታ ወደ ድርድር ከመግባታቸው በፊት በአዲስ መልክ የአውስትራሊያውን ኩባንያ እንዲጠና መመሪያ ወደታች አውርደው ነበር። እሳቸው ባዋቀሩት የጥናት ቡድንም ኩባንያው ታንታለም ለማልማት የሚችል ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ ተረጋግጧል።
ለአብነት ይረዳን ዘንዳ በመካከላቸው የተደረጉትን የደብዳቤ ልውጦች መንፈስ በወፍ በረር እንመልከታቸው። የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ለኩባንያው በታንታለም ልማት ላይ ዕሴት የሚጨምሩበትን እቅዳቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ጥሪ አድርጓላቸዋል። አጠቃላይ ይዘቱን በተመለከተ፣ ኩባንያው ዕሴት የሚጨምርበትን እና ወደተግባር የሚገባበትን የጊዜ እቅዶቹን፣ ያለውን የማምረት ልምድ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፋይናንስና የገበያ ጥናት፣ በምን መልኩ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ቢዝነስ ለመስራት እንዳሰበ (በሽርክና ወይም በሌላ መልኩ) ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው። እንዲሁም ከአካባቢና ከማሕበራዊ ተፅዕኖ አንፃር፣ በማዕድን ፍለጋና ማውጣት እና ኩባንያው በታንታለም እና በተያያዥ ማዕድኖችን ለማልማት ያለውን ዕቅድና ቁርጠኝነት የሚያሳይ ዕቅድ ይዘው እንዲያቀርብ ተጠይቋል።
የሚኒስቴሩን ጥሪ ኩባንያው ተቀብሎ ለሚኒስቴሩ በቀንጢቻ ታንታለምን ለማልማት ያለውን ዕቅድ በዝርዝር ጽፎ አስረክቧል። ከአዋጭነት ጥናት እስከ አምርቶ ወደ ውጪ ለመላክ የሚያስችሉ የሥራ ሒደቶች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንደሚያከናውን ማረጋገጫ ሰጥቷል። ከ100 ዓመታት በላይ በዘርፉ ልምድ ያለው ይህ ኩባንያ፣ በኦፕሬሽን ሥራዎቹ Tin, Tantalum ,kaolin, Lithium, and Niobium የተባሉ ማዕድናትን ከረጅም ጊዜ አንስቶ እየሰራ ነው የሚገኘው። ከኮርፖሬት ፋይናንስ በቂ ገንዘብ ማቅረብ እንደሚችል አስታውቆ፣ ለከርሰምድር ጥናት 20 ሚሊዮን ዶላር እና ለኢንጅነሪንግና ለእሴት መጨመሪያ ፕላንቶች ለመትከል 200 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጿል። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ ቴክኖሎጂውም እንዳለው አስታውቋል። የቢዝነስ ሞዳሊቲውም በሽርክና ከኢትዮጵያ ማዕድን ፔትሮሊየም እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን ጋር መስራት መሆኑን አስፍሯል።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር መስራያቤት በበኩሉ ኩባንያው ላሳየው ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ማዕድን ፔትሮሊየም እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን ጋር በሽርክና ለመስራት ባሳየው ፍላጎት መደሰቱን ጠቅሶ፣ በሽርክና ለመስራት የሚያስችላቸውን ነጥቦች ለማስቀመጥ ፍላጎት እንዳለው ገልፆ ጽፏል። አያይዘውም፣ ዕሴት በመጨመር ላይ አትኩሮት እንደሚያደርግ ጠቁመው ወደስራ የሚገቡበት የሥራ ድርጊት መርሃ ግብርም እንዲገለጽላቸውም ጠይቀዋል። ኩባንያውም ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ለተደረገለት ጥሪ የማረጋገጫ ምላሽ አቅርቧል። እንዲሁም በማንኛው ጊዜ አዲስ አበባ በመገኘት ለውይይት ወይም ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልፆ ጽፏል።
በመጨረሻም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ኩባንያው ዕሴት ለመጨመር ያለውን ዕቅድ እና አምርቶም ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ያላውን ቁርጠኝነት እንደሚያደንቅ ጠቅሶ ይፋዊ የሆነ ድርድር ከኩባንያው ጋር ማድረግ እንደሚፈልግ አስታውቋል። ለኢትዮጵያ ማዕድን ፔትሮሊየም እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን መስሪያቤት የመደራደሪያ ነጥቦችን በፍጥነት እንዲያዘጋጅ ማሳሳቢ እንደደረሳቸው አረጋግጠናል። ኩባንያው በበኩሉ ለይፋዊ ድርድር መጠራቱ እንዳስደሰተው ገልፆ አዲስ አበባ በመገኘት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
ከኤሌኒቶ ጋር የተራገፈው ቡድን በአዲስ መልክ ሴራ ጀመረ
እንደሚታወቀው ታንታለም ውህድ እና የከበረ የማዕድን ድንጋይ ነው። ይህንን የማዕድን ድንጋይ በፋብሪካ ደረጃ ሲፈነከት Tin, Tantalum ,kaolin, Lithium, and Niobium የተባሉ ማዕድናት ከፍንክት ድንጋዩ ይወጣሉ። ለታንታለም የጨረታ ሰነድ ሲዘጋጅም የጨረታ ሰነዱ ስያሜ “ኮንሰትሬትድ ታንታለም” ተብሎ ነው የሚጠራው።
ይህንን ውህድ የከበረ ድንጋይ ለማልማት የሚፈልግ ኩባንያ የሚጠይቀው፣ ውህዱን ታንታለም በመፈንከት በውስጡ የሚገኙ ማዕድኖችን ለማልማት እና ዕሴት በመጨመር አዋጪ ስራዎችን ለመስራት ነው። በየትኛውም አግባብ ከወሰድነው ለማልማት ፍላጎት ያለው ኩባንያ የሚወዳደረው የማዕድኑን ድንጋይ ለመፈንከት ነው። ከዚህ ውጪ ከተፈነከተው ድንጋይ ሊገኙ ከሚችሉ ማዕድኖች መካከል አንዱን መርጦ አለማለሁ የሚባል አግባብ የለም።
ከአሰራር አንፃር ከተመለከትነው፣ አንዱ ኩባንያ በፈነከተው ድንጋይ ውስጥ የሚገኙ ማዕድኖችን ለሌላ ኩባንያ መስጠት አይቻልም። ለአሰራርም አመቺ አይደለም። ከሳይንሱ አንፃርም ከወሰድነው ከሚፈነከተው ድንጋይ የሚገኘው የማዕድን መጠን ስለማይታወቅ ተረፈ ምርቶቹን በዋና የቢዝነስ አካሎች አድርጎ መውሰድ አዋጪም አይደለም። በዚህም መልኩ የተሰራ ቢዝነስም የለም። ከሁሉም በላይ ባለሙያዎች እንደሚሉት ድንጋዩን በፋብሪካ ደረጃ ለመፈንከት የተስማማ ኩባንያ የሁሉም ማዕድናት አልሚ ነው የሚሆነው። ይህ ጥሬ እውነቱ ነው።፡
የሆነው ግን ሌላ ነው። ይኽውም ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ለኢትዮጵያ ማዕድን ፔትሮሊየም እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን መስሪያቤት የመደራደሪያ ነጥቦችን እንዲያዘጋጅ ማሳሳቢያ ቢጽፍለትም ተግባረዊ ከማድረግ ተቆጥቧል። ይህም ሲባል ኮርፖሬሽኑ በአሰራርም ሆነ በሳይንስ ድጋፍ በማይሰጠው ሁኔታ ከሚፈነከተው የታንታለም ድንጋይ ከሚገኙ ማዕድኖች መካከል ሊቲየም የተባለውን ማዕድን የሚያለሙ ኩባንያዎች ስለቀረቡ የድርድሩ ተካፋይ መሆን አለባቸው የሚል አዲስ ሃሳብ ይዞ ብቅ ብሏል። ከላይ እንዳሰፈርነው ከኤሌኒቶ ጋር የተቀናጀ ሙስና በመፈፀም የሚጠረጠሩ የአክሲዮኑ ኃላፊዎች ተገቢውን ቅጣታቸውን ባለማግኘታቸው በአዲስ የቢዝነስ ሴራ ስኳር ለመላስ የጠለፋ መረባቸውን መዘርጋታቸውን ለማወቅ የተለየ እውቀት አያስፈልግም። ወይም እነሱን መሆን ግዴታ አይደለም።
በኮርፖሬሽኑ በኩል የተፈነከተውን የማዕድን ድንጋይ እናለማለን ብለው በጓሮ በር የቀረቡት ኩባንያዎች ከሀገር ደህንነት አንፃር ሊፈተሹ የሚገባቸው ናቸው። ኩባንያዎቹ ላይንታውን እና ዳኮታ ሚኒራልስ ተብለው የሚጠሩ ናቸው። እነዚህ ኩባንያዎች ከኤርትራ አገዛዝ ጋር 60 በ40 የሽርክና ድርሻ በመውሰድ ሥራዎችን ለመስራት የተስማሙ፣ የነበሩ ናቸው። ከኤርትራ አገዛዝ ጋር መስራታቸው በተራ የንግድ ዕይታ ችግር የለውም ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ቁምነገሩ ግን የኤርትራ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አንፃር በተቃርኖ የቆመ በመሆኑ ይህንን አገዛዝ በኢኮኖሚ የሚያበረቱ ኩባንያዎች አቅማችን በፈቀደ መጠን ልንከላከላቸው ይገባል። ይህ አይነት የብሔራዊ ጥቅም ደህንነትን የማስከበር አሰራር ዓለም ዓቀፍ ተቀባይነት ያለው ነው። ቢያንስ ደግሞ ለልማታችን አማራጭ ኩባንያዎች በራችንን እያንኳኩ ሳለ መፍቀድ ተገቢነቱ በጣም ዝቅተኛ ነው።
በዋናነትም ሊታይ የሚገባው ሌላው ነጥብ ኩባንያዎቹ እናለማዋለን የሚሉትን ሊቲየም ከተባለው ማዕድን ጋር ያላቸው ልምድን መመልከት ጠቃሚ ነው። ይኽውም ላይንታውን ኩባንያ ከሊቲየም ማምረት ስራ ጋር በተያያዘ የስድስት ወራት እድሜ ብቻ ነው ያለው። ዳኮታ ሚኒራልስ ኩባንያም ፈጽሞ የሊቲየምን ማዕድን በማምረት ዘርፍ ላይ የተሰማራ አይደለም።
ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ማዕድን ፔትሮሊየም እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን ከሚኒስትር መስሪያቤቱ የተሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ሳያደርግ፣ አዲሶቹን ኩባንያዎች የማዕድኑን ፍንካች እንዲያለሙና የድርድሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለምን ፈለገ? ይህ ፍላጎቱ የተቋሙ ነው? ወይንስ ከኤሌኒቶ ጋር የተቀናጀ ሙስና ሰንሰለት የተራገፉ ግለሰቦች ፍላጎት ነው? ሚኒስቴር መስሪያቤቱ እና ቦርዱ ለምን ፍጥጫ ውስጥ ገቡ? ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ የሰጡትስ የአቅጣጫ መመሪያ የቀለበሰው አካል ማነው?

No comments:

Post a Comment

wanted officials