"እነሱ የሚፈልጉትን እኛ አንሆንም!"
"አምባገነኖች ባሉበት የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው" የዞን ዘጠኝ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ግንቦት 27 ቀን 2008 ዓ.ም ሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋጀው ፣በአገዛዙ ስርዓት በሰላማዊ ትግል ሂደት ለተሰው እና ዋጋ ለከፈሉ ፣የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ በመገኘት ለንግግሩ መግቢያ የተጠቀመው አባባል ነው።የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የእለቱ ዝግጅት አስመልክቶ ለተገኙ እንግዶች እና ለፓርቲ አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ ሰላምታ ካደረጉ በኋላ ፣በተለያየ እስር ቤት እንግልትና ስቃይ የደረሰባቸውን በማስታወስ፣እንዲህ አይነቱ ስቃይና በደል ልናስቆም የምንችለው ኃይላችንን አሰባስበን በምናደርገው ትግል ነው፤ በማለት ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ለዝግጅቱ አሰተባባሪ ኮሜቴ ምስጋና አቅርበዋል ።
የቀድሞ አንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊ ዳንኤል ሺበሺ፤ በእስር ቤት የሚደርስብን ስቃይ ብዙ ነው፣ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። ሰማያዊ ፓርቲ ይህን አስታውሶ አጋርነቱን ለመግልጽ እና ለማበረታታት ባዘጋጀችው ዝግጅት ላይ በመገኘቴ ደስ ብሎኛል፣ ፓርቲውም ሊመሰገን ይገባል፣ በማለት ንግግር ያደረገ ሲሆን፣ ሰማያዊ ፓርቲ እንደተቋም ያለበትን ችግሮች በሰለጠነ መንገድ በውይይት እንዲፈታ መልእክቱን በማስተላለፍ ፣ ወደፊት ፓርቲው ሊሚያደርጋቸው ማናቸውም ነገሮች የሚችለዉን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጾአል።
በእስር ቤት በነበረዉ ቆይታ ፣ ለከፍተኛ ህመም የተጋለጠው ፣ የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው "እነሱ የሚፈልጉትን እኛ አንሆንም" በማለት ፣በተለያየ እስር ቤት የአገዛዙ ስርዓት ጠባቂዎች የሚያደርሱብን በደል እና ስቃይ ፣እኛን በማሸማቀቅ ከያዝነው ትግል በማራቅ ፈሪዎች ሊያደጉን ይፈልጋሉ ፣እኛ ግን እነሱ የሚፈልጉትን አንሆንም በማለት ንግግር ያደረገ ሲሆን፣በደረሰኝ ከፍተኛ ህመም በአገር ውስጥ እና በውጪ የምትገኙ ወገኖቼ ላደረጋችሁልኝ ድጋፍ ሁሉ አመሰግናለሁ በማለት መልእክቱን አስተላፏል።
ሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋጀው ፣ በአገዛዙ ስርዓት በሰላማዊ ትግል ሂደት ለተሰው እና ዋጋ ለከፈሉ የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ፤ ከተገኙ እንግዶች መካከል ለ1 ዓመት ከ10 ወር ከእነ ሀብታሙ አያሌው ጋር ታስረው የተፈቱት፣ አቶ አብርሃም ሰለሞን እና አቶ ባህሩ ደጉ ይገኙበታል።በእስር ቤት በነበራቸው ቆይታ ይድርስባቸው የነበረ እንግልት እና ስቃይ የገለጹ ሲሆን፣ያሳለፉት ነገር ሁሉ አሁን ላይ ብርታት እንደሆናቸው ገልጸዋል ። አቶ የሺዋስ አሰፋ ፣የእለቱ ዝግጅት አስመልክቶ ሃሳቡን በጽሑፍ የገለጸ ሲሆን፣የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች በእንዲህ መልኩ ማሰብ እና አጋርነትን መግለጽ የሚበረታታ መሆኑን በማሳሰብ ፣ወደፊት በተሻሻለ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል።
አቶ አብርሃም ሰለሞን፣ አቶ ባህሩ ደጉ ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ ሀብታሙ አያሌው ፤በእስር ቤት በነበራቸው ቆይታ ገጠመኞቻቸውን ያጋሩ ሲሆን፣በእለቱ የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት፣ የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን እንዲሁም የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል ።
(ይድነቃቸው ከበደ)
No comments:
Post a Comment