ቋንቋችንን እንታዘበው (፫)፤ Nation, Country, State (የትኛው ነው አገር? የትኛው አይደለም?)
በቋንቋችን ውስጥ ያሉ እና (በዋነኝነት) የሌሉ ቃላትን በመመርመር ፅንሰ-ሐሳቦቹን የሚወክሉ ቃላት በማኅበረሰባችን ውስጥ ማስረፅ አስፈላጊ ስለመሆኑ መነጋገራችንን እንቀጥላለን፡፡ ይህንን ማራኪ የማይመስል ርዕሰ-ነገር እያከታተልኩ የማመጣው ተፅዕኖው መፍትሔ መውለድ ላልቻለው ውይይት-ሙግታችን ቀላል እንዳልሆነ በመጠርጠር ነው፡፡ መነሻው ሠለጠኑ ከምንላቸው ዓለማት ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን ሐሳባዊ ሥልጣኔንም መውረስ፤ አለን የምንለውንም ማጎልበት ወይም መስጠት የሚቻልበትን ተዋስኦ (discourse) ለማቀላጠፍ ባለመ የዋህ ምኞት ነው፡፡
እንደመንደርደሪያ ሰሞኑን ‹ፌሚኒዝምን› በተመለከተ በትዊተር ያየኋትን አጭር ውይይት ላስታውስ፡፡ ‹ፌሚኒዝም› በአጭሩ፣ በራሴ አተረጓጎም የሴቶች የዕኩልነት ንቅናቄ ነው፡፡ ንቅናቄው በተለይ በባሕል እና በቅርጽ ‹ወንዳዊ› የሆነውን ዓለም ለሴትም ዕኩል ዕድል (opportunity) እንዲሰጥ (‹ሴታዊ› የማድረግ ሳይሆን ‹ሴታዊ›ም) የማድረግ ዓለምዐቀፍ ንቅናቄ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች “‹ፌሚኒዝም› ከምዕራባውያን የተጫነብን፣ ለአፍሪካውያን እንግዳ አስተሳሰብ ነው፤ ማስረጃውም ቃሉን የሚተካ ለምሳሌ አማርኛ የለም” የሚል ዓይነት “ሙግት” ነው፡፡ ተመሳሳይ ሙግቶች ‹ሊብራሊዝም›ን በተመለከተም ሲሰነዘር ሰምቻለሁ፡፡ ‹ፌሚኒዝም› ለአፍሪካ እንግዳ ሐሳብ ነው በሚለው ላይ አልስማማም፣ ነገር ግን ሐሳቡ እንግዳ ነው ለሚለው ተጨባጭ ማስረጃ ቢኖርም እንኳን ሙግቱ ቂላቂል ነው፤ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎች (ራሱን ይሄን ቃል ጨምሮ) እንደ ዘመን አመጣሽ አስተሳሰቦች ሁሉ የአገር ውስጥ አቻ ቃል የላቸውም፡፡ ነገር ግን ከተቻለ የቴክኖሎጂዎቹን ሥራ የሚገልጽ ቃል ፈልገን እንጠቀማለን፣ ካልሆነ ደግሞ ከቴክኖሎጂዎቹ ጋር ተያይዞ የመጣውን የባዕድ አገር ቃል እየተጠቀምን እንቀጥላለን እንጂ ቴክኖሎጂው አፍሪካዊ አይደለም፣ ከምዕራብ የመጣ ነው ብለን ሳንጠቀምበት አንቀርም፡፡
ባሕል እና ሥልጣኔም እንዲሁ ነው፤ ከባዕድ አገራት (ባዕድ የሚለው አግላይ በመሆኑ ባልጠቀምበት እመርጥ ነበር) ሲመጡ ከትውፊታዊው ባሕላችን እና ሥልጣኔ የተሻለ ከሆነ እንኳን በዘመነ ሉላዊነት በጋርዮሽ ዘመንም ቢሆን ከመቀበል እና የራስን ከመጣል አንተርፍም፡፡ ቋንቋ ደግሞ የባሕል ዋና ቅንጣት ነው፡፡ ስለዚህ ቋንቋችን እና የቋንቋ ክኅሎታችን ዘመኑ መስጠት የሚችለውን ያህል እንዲረዳ እና እንዲያስረዳ የተቻለውን ያህል መለጠጥ አለበት፡፡
‹አገር› ስንል ምን ማለታችን ነው?
በክፍል ፪ ትዝብቴ “‹State› የሚለው ‹አገረ-መንግሥት› እያልን አሁን-አሁን የምንተረጉመውን ከ‹መንግሥት› የሰፋ ትርጉም ይሰጣል፤ ፅንሰ-ሐሳቡ ግን ለኢትዮጵያውያን እንግዳ ነው” ብዬ ነበር፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ቃሉ (‹State›) ‹መንግሥት› ከሚለው’ጋ ብቻ ሳይሆን የሚምታታው ‹አገር› ከሚለውም ጋር ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ቃሉ ‹መንግሥት› የሚለውን በከፊል፣ ‹አገር› የሚለውንም በከፊል እንደሚገልጽ በመረዳቷ/ቱ ነው ‹አገረ-መንግሥት› የሚለውን ጥምረ-ቃል መጀመሪያ የተጠቀመ/ች/በት ሰው የመረጠ/ች/ው፡፡ ‹country› የሚለው ቃል አገር፣ ‹nation› የሚለው ቃል ደግሞ ‹ሕዝብ› ተብለው በቀላሉ (በተለምዶ) ይተረጎማሉ፡፡ ነገር ግን ትርጉሞቹ እውን እያግባቡን ነው? ምሳሌ በማንሳት እንጀምር!
ዞን ፱ የበኩር የበይነመረብ ዘመቻውን ‹ሕገ-መንግሥቱ ይከበር!› በሚል ርዕስ ሲያደርግ የተጠቀመበት (እና ኋላ በአንዳንዶች ተቃውሞ ስለገጠመው፣ ሁሉን ዐቀፍ ለማድረግ ሲባል የተፋቀው) ዓ/ነገር ‹Our Nation is Ethiopia, Our Nationality is Ethiopian and We are the People of Ethiopian.› የሚል ነበር፡፡ በወቅቱ ትርጉሙን በአማርኛ ለማስቀመጥ አልሞከርንም ነበር፡፡ ምናልባት ብንሞክር ኖሮ እንዲህ የሚሆን ይመስለኛል ‹አገራችን ኢትዮጵያ፣ ዜግነታችን ኢትዮጵያዊ፣ እኛ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነን›፡፡ ነገሩ ችግር ያለው አይመስልም፤ አንዳንድ የበይነመረብ ላይ የብሔርተኝነት (nationalist) አራማጆች ግን በዚህ መንገድ አልተረዱንም ወይም ሊረዱን አልፈለጉም ነበር፡፡ ‹Ethiopia is not a nation; it is an empire› (‹ኢትዮጵያ ‹ብሔር› አደለችም፤ ግዛተ-ዐፄ ናት› እንደማለት) የሚል ነበር አንዱ አስተያየት፡፡
“ኢትዮጵያ ‹ብሔር› አይደለችም፤ የ‹ብሔሮች› ስብስብ ነች” የሚለው አስተሳሰብ መንግሥታዊ ዕውቅና ያለው አባባል ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ስሌት ‹ብሔራዊ› መዝሙር፣ ‹ብሔራዊ ቡድን› እና ‹ብሔራዊ ደኅንነት› የሚባሉት ነገሮች ትርጉማቸው ምንድን ነው? ለመመለስ ያስቸግራል፡፡ ነው ወይስ ‹አገራዊ› እየተባሉ መተካት አለባቸው? “የኢትዮጵያ ብሔራዊ…” የሚባል ነገር ካለ ኢትዮጵያ “ብሔር” ናት የሚል ሐሳብ ውስጡ ያለ ይመስለኛል፡፡
“Nation-State” የሚል ፖለቲካዊ ቃል አለ፤ በቀላሉ ሲተረጎም ‹አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦችን ያቀፈ አገረ-መንግሥት ማለት ነው›፤ ለምሳሌ እንግሊዝ ‹ኔሽን-ስቴት› ናት፡፡
በ dictionary.com ብያኔ መሠረት፣
Nation: a large body of people, associated with a particular territory, that is sufficiently conscious of its unity to seek or to possess a government peculiarly its own. (‹ብሔር›፡ የራሳችን የሚሉት መንግሥት ያላቸው/የሚፈልጉ እና ኅብረታቸውን የሚያውቁ፣ በአንድ ግዛት ሥር የተሰባሰቡ ሕዝቦች ናቸው፡፡)
ወይም
፡ the territory or country itself (ግዛት ወይም አገር)
፡ the territory or country itself (ግዛት ወይም አገር)
Nation-state: a sovereign state inhabited by a relatively homogenous group of people who share a feeling of common nationality. (‹ብሔረ-መንግሥት›፡ የወል ብሔርተኝነት ስሜት በሚጋሩ አንፃራዊ ወጥ ማንነት ባላቸው ሕዝቦች የተመሠረተ ሉዓላዊ አገረ-መንግሥት)
Country: a state or nation (‹አገር›፡ አገረ-መንግሥት ወይም ብሔር)
ወይም
፡ the territory of a nation (የአንድ ብሔር ግዛት)
፡ the territory of a nation (የአንድ ብሔር ግዛት)
ኢትዮጵያ የብሔረ-መንግሥታት ፌዴሬሽን ነች፤ ቢያንስ በሕግ ድንጋጌ መሠረት፡፡ ነገር ግን የደቡብ ክልልን እንደምሳሌ ብንወስድ ደግሞ ክልሉን ብሔረ-መንግሥት ብለን ለመጥራት ከላይ ከሰጠነው ብያኔ አንፃር መግባባት አንችልም፡፡ ‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት› የሚባል ነገር አለ/የለም የሚለው ጭቅጭቅ መቋጫ ሊያገኝ ያልቻለው ‹ብሔር› በሚለው ቃል ላይ መግባቢያ ላይ መድረስ ስላልቻልን ይመስለኛል፡፡ ‹ብሔርተኛ› የሚለው ቃል ያለው ትርጉም በራሱ አዎንታዊ ይሁን አሉታዊ መገመት እንኳን አልተቻለም፡፡
በኢትዮጵያ ያለው ችግር ‹ብሔር› (Nation) የሚለውን የመበየን አይደለም፡፡ ዘውግ (ethnicity)፣ አንድ የ‹ብሔር› ንዑስ ስብስብ ነው፡፡ ማለትም አንድ ብሔር ውስጥ ብዙ ዘውጎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የዘውግን የፖለቲካ ትርጉም ስንመለከት ደግሞ በኢትዮጵያ በተለምዶ ‹ብሔር› የሚለውን ከምንበይንበት የተለየ አይደለም፡፡ ዘውግ በዋነኝነት በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ነገር ግን በቋንቋ ብቻ ያልተወሰነ የሕዝቦች የወል ማንነት ነው፡፡ ይህ ትርጉም ኢትዮጵያ ውስጥ ‹ብሔር› እያልን የምንጠራቸው ቡድኖችን በትክክል ይገልጻቸዋል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡
ኦሮምኛ ሁለቱን ቃላት (ብሔር፡ saba; አገር: biyyaa)የተሻለ የሚገልጻቸው ይመስላል፡፡ አማርኛ የተዋሰው ቃል ‹ጎሳ›ም፣ ምንጩ ከዚያው ነው የተቀዳው፡፡ በኦሮምኛ ‹ጎሳ› የሚለውን ቃል፣ ዘውግ ከምንለው ጋር ዕኩያ ነው የሚሉ አሉ፤ ከዚያም አጥብበው በእንግሊዝኛ ‘tribe’ ከሚለው እና በዘር ሐረግ ከሚቆጠረው ጋር የሚያመሳስሉት አሉ (በእርግጥም ይህንኛው ለእውነታው የቀረበ ይመስላል)፡፡ ‹ጎሳ› የምንለውን ቃል በነባራዊው ሁኔታ ‹ብሔር› የምንለውን ነው የሚተካው ‹ብሔር› እነዚህን ጎሳዎች ዐቀፏ ኢትዮጵያ ናት የሚሉ አሉ፡፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም፣ የዘውግ ፌዴራሊዝም፣ የብሔር ፌዴራሊዝም እያልን በምንፈልገው ሥም በጠራነው ቁጥር ፌዴራሊዝሙም የተለያየ ትርጉም ያለው ፌዴራሊዝም ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስንቃወመው ወይም ስንደግፈውም (እንደአጠራራችን/አተያያችን) የተለያየ ዓይነት ፌዴራሊዝም ነው የምንደግፈው ወይም የምንቃወመው ማለት ነው፡፡ ግራ መጋባት አይታያችሁም?
(ይቀጥላል)
ክፍል ፬፤ nationalism, ethnocentrism, racism (የትኛው ዘረኝነት ነው? የትኛው አይደለም?)
ክፍል ፬፤ nationalism, ethnocentrism, racism (የትኛው ዘረኝነት ነው? የትኛው አይደለም?)
No comments:
Post a Comment