ቋንቋችንን እንታዘበው (፪)፤ Government, State (የቱ መንግሥት ነው? የትኛው አይደለም?)
እንደመንደርደሪያ ስለመብቶች እናውራ። በተለይ ደግሞ ስለሰብኣዊ መብቶች። ሰብኣዊ መብቶች በማንም የሚሰጡን አይደሉም። በተፈጥሮ የምናገኛቸው ናቸው። ይህንን መንግሥታት በሕግ ለማስከበር ቃል ይገባሉ። መንግሥታት ይህንን ቃልኪዳናቸውን የሚገቡት መብቶቻችንን ሊጠብቁ እና ሊያስጠብቁ ነው፤ እኛ [ዜጎች] ደግሞ በምላሹ በሹመት ኃላፊነቶችን እንሰጣቸዋለን። አምባገነኖች ግን ይህን መሠረታዊ የመንግሥት እና ዜጎች የግንኙነት መስፈርት ስተው ራሳቸውን የመብት ሰጪ እና ነሺ አስመስለው ያቀርባሉ። ይህንን ተገዢዎችም ሳይታወቃቸው ይቀበሉታል። “መንግሥት የሰጠኝን መብቴን…" ሲባል እንሰማለን። ዜጎች መብታቸውን መንግሥት እንደሰጣቸው ካሰቡ አለቀ፣ ደቀቀ። ሊቀማቸው እንደሚችልም ያስባሉ። ስጦታውን እንዳይቀማቸው በመፍራት ሰጥ-ለጥ ብለው ይገዙለታል፤ በእጅ አዙር መብታቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ ማለት ነው። በነገራችን ላይ አምባገነኖች ዜጎች እንዳይቀሟቸው የሚፈሩትን መብት በመንጠቅ በዜጎቻቸው መብት ላይ ያላቸውን "ሥልጣን" በማሳየት የበለጠ ዜጎች እንዲግገዙ ያደርጋሉ እንጂ ‘መብቴን እንዳይነጥቀኝ ብሎ ታዝዛልኛለች/ታዝዞልኛልና አልነጥቀውም’ ብለው አያስቡላቸውም።
የቋንቋ አጠቃቀማችን የነገሮች አረዳዳችንን፣… የነገሮች አረዳዳችን ደግሞ አኗኗራችንን፣… አኗኗራችን ደግሞ የመንግሥታችንን ዓይነት ይወስናል።
በማኅበረሰባችን ዐሳብ ውስጥ መንግሥት የአገር መሪው (head of State) ነው። ትንሽ ሲያድግ ደግሞ መንግሥት ገዢው ፓርቲ ነው። አንዳንዴ በሌላ መንገድ ደግሞ በአገር እና በመንግሥት መካከል ያለው ልዩነት ይምታታል፡፡ በመንግሥት የተማረሩ ዜጎች የአገሪቱን ሥም እንኳን መስማት እስከመጠየፍ የሚደርሱት በመንግሥት፣ በሕዝቡ እና በአገሪቱ መካከል ያለው ልዩነት ሲምታታባቸው ነው፡፡ ችግሩ ከመንግሥቱ ይሁን ከአገረ-መንግሥቱ (ወደታች እንበይነዋለን) ወይም ከሕዝቡ/ከአገሩ ለመለየት የተቸገረ ሕዝብ/ልኂቅ እንደመገንጠል፣ እንደመሰደድ ያሉ መፍትሔዎችን ይመርጣል፡፡
ይህንን ለመጻፍ የተገደድኩት የተለያዩ ሰዎች ‹መንግሥት› ወይም ‹ኢትዮጵያ› እያሉ ሲጽፉ እነዚህን (ከታች የምዘረዝራቸውን ልዩነቶች) ሳያጤኑ ይሆንና በተለይ ማንን ለማለት እንደፈለጉ ግራ የሚገባኝ ግዜ እየበረከተ ስለመጣ ነው፡፡ በአንድ ቋንቋ እያወራን መሆናችንን በመጠራጠር!
በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ‘Government’ (‹መንግሥት›) እና ‘State’ (አሁን አሁን ‹አገረ-መንግሥት› እየተባለ ያለው) ቃላት ‘መንግሥት’ በሚለው ቃል ነው በጥቅሉ የሚተረጎሙት። በፖለቲካዊ እሳቤ ግን እነኚህ ሁለቱ የተለያየ ትርጉም ነው ያላቸው። የጉግል ተርጓሚን ተውሰን ብያኔያቸውን እናጢን፣
Government (መንግሥት) ~ “the group of people with the authority to govern a country or state.” (በግርድፉ፣ «አንድን አገር ለማስተዳደር/ለመምራት ሥልጣኑ ያላቸው ሰዎች ስብስብ»)
State (አገረ-መንግሥት) ~ “a nation or territory considered as an organized political community under one government.” (በግርድፉ፣ «በአንድ መንግሥት ስር የተዋቀረ የአንድ ‘ሕዝብ’ ወይም አካባቢ የፖለቲካ ማኅበረሰብ»)
የላይኛው ፍቺ መንግሥት (government) እና አገረ-መንግሥት (State) መካከል ያለውን ልዩነት ቁልጭ አድርጎ ለማስረዳት በቂ ነው። በምሳሌ ብንመለከተው፣ አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ሕወሓት/ኢሕአዴግ ነው። ቀደም ሲል ደርግ (ወታደራዊ ኮሚቴው) ነበር፡፡ መንግሥት ይቀያየራል። አገረ-መንግሥት ግን ከአንድ መንግሥት የበለጠ ዕድሜ አለው፡፡ ለምሳሌ የአሁኒቷ ኢትዮጵያ አገረ-መንግሥት ከዐፄ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት ጀምሮ በአንድ ዓይነት ካርታ (ከመጠነኛ የአጭር ወቅቶች ልዩነት ጋር) እስካሁን አለ፡፡ ነገር ግን የተለያዩ መንግሥታት መጥተው ሲያልፉ የተለያየ አስተዳደር ተከትለዋል፡፡
አንዳንድ ሰዎች የኢትዮጵያን አገረ-መንግሥት ይቃወማሉ፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ አሁን ባላት ቅርጽ መቀጠል የለባትም እያሉ ነው ማለት ነው፡፡ ሌሎች የኢትዮጵያን መንግሥት ይቃወማሉ፤ እነዚህኞቹ ፀባቸው አገሪቱን ከሚያስተዳድሩት ቡድኖች ጋር ነው ማለት ነው፡፡ አገረ-መንግሥቱን እና መንግሥቱን በመቃወም መካከል ያለውን ልዩነት የማያስተውለው ብዙኃን ደግሞ በመሐል ቤት ከነፈሰው ጋር ይነፍሳል፡፡ ልዩነቱን የማይረዳ ብዙኃን እንደሌለ ለመረዳት ፅንሰ-ሐሳቦቹን ነጣጥለው የሚገልጹ ቃላት ብዙኃን የሚናገሯቸው የአማርኛ ወይም የኦሮምኛ ቋንቋዎች ውስጥ አለመኖራቸውን እንደማስረጃ ወስጄ ነው፡፡ በኦሮምኛ ‹mootummaa› የሚለው ቃል ሁለቱንም ‘Government’ እና ‘State’ የሚሉትን ቃላት ለመተርጎም ይውላል፡፡ (በነገራችን ላይ ተቋማት የማይፀኑልን አዲሱ መንግሥት ሲመጣ የአሮጌውን መንግሥት አሻራ ለማጥፋት የአገረ-መንግሥቱን ቅርፅ ድራሹን በማጥፋት ስለሚጀምር ነው። ምክንያቱም አገረ-መንግሥቱን ከመንግሥቱ ለይቶ አያየውም።)
በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ዘጠኝ የክልል አገረ-መንግሥታት እና አንድ የፌዴራል አገረ-መንግሥት አለ፡፡ ይህ የቅርፅ ጉዳይ ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ እኛ በፌዴሬሽኑ ውስጥ መሆን አንፈልግም፣ ‹መነጠል› እንፈልጋለን የሚሉትም(1)፤ ፌዴሬሽኑ አያስፈልግም ማዕከላዊ አገረ-መንግሥት ይኑረን የሚሉትም(2)፤ የፌዴሬሽኑ አወቃቀር ላይ ችግር የለብንም ሥልጣን ክፍፍሉ እና አተገባበሩ ላይ እንጂ የሚሉትም(3)፤ ፌዴሬሽን መሆኑ ላይ ሳይሆን አወቃቀሩ ላይ ችግር አለብን የሚሉትም(4)፤… ሁሉም መንግሥትን ይቃወማሉ፡፡ ነገር ግን ምክንያታቸው አንድ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ አገረ-መንግሥቱንም ጭምር ነው የሚቃወሙት ነገር ግን ራሳቸውን ግልጽ ማድረጊያ ቋንቋ ስለሚያጥራቸው ሁሉም ቡድኖች ሳይግባቡ እንደተግባቡ ሆነው አብረው ይሠራሉ፡፡
(ይቀጥላል)
ክፍል ፫ - Nation, Country, State (የትኛው ነው አገር? የትኛው አይደለም?)
No comments:
Post a Comment