Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, June 5, 2016

ሰውን ሰው ያ'ረገው የፊት ጥርሱ ነው ( ሄኖክ የሺጥላ )

ሰውን ሰው ያ'ረገው የፊት ጥርሱ ነው ( ሄኖክ የሺጥላ )
« ሰውን ሰው ያረገው ስራ ነው » የሚል ሌኒናዊ መፈክር ልጅ ሳለሁ በአንደኛው የሰፈራችን መስታወት ቤት ተለጥፎ ያየሁት ትዝ ይለኛል። ጋሽ ሌኒን አጎቴቼን እና የነሱን ጓደኖች መቅኖ አሳጥቶ ፥ በሀገራቸው እንዳይሰሩ ፥ ተከባብረው እንዳይኖሩ ፥ አውጫጭኙን እና አፈርሳታውን በቅጡ ሳይረዱ ፥ በ « ዘ ካፒታል አናውዞ» ፥ እርስ በእርስ እናክሶ ፥ ወንድማማቾችን ሽጉጥ አማዞ ፥ እኩሌታውን ማሌሊት ፥ እኩሌታውን ኢህአፓ ፥ እኩሌታውን መኢሶን፥ የተቀረውን ደሞ ደርግ ብሎ ከፋፍሎ ፥ ስለ አንድ አይነት ነገር እያወሩ ፥ እንደባቢሎን ተውሰው የቀሰሙት የባዕድ ፍልስፍና አናውዟቸው ፥ ባሊ ሲለው መጥረቢያ እያቀበለ ፥ እርስ በእርስ ተበላልተው እና ተራርደው ካለቁ በኋላ ፥ ሰፈሩ ወጣት መክኖ ፥ እኔና መሰል ጨቅላዎች ብቻችንን አቧራ ላይ በምንንከባለልባት ባዶ ሃገር ላይ ጋሽ ሌኒን የሩሲያ ቶክሲዶውን ለብሶ « ሰውን ሰው ያደረገው ስራ ነው ይለናል»! ጥቅሱ ለማን ነው ? ለኛ ? ባንተ ርዕዮት ተባልተው ለሞቱት አጎቶቻችን ? በቀይ ሽብር ልጆቻቸውን ተነጥቀው ጧሪ ቀባሪ ላጡት አያቶቻችን ነው ? በማሌሊት ሰክረው ደደቢት በርሃ ሸምቀው ድልድይ ለሚያፈርሱት ፥ ባንክ ለሚዘርፉት የያኔው ወንበዴዎች ነው ? ኢህአፓ ብለው ጀምረው ወንድሞቻቸውን አስበልተው ( አላስበላንም ካሉ ደሞ «እሺ ይሁንላችሁ ፥ የወንድሞቻቸውን ደም ሳይመልሱ» ) በሱዳን በኩል መጭ ብለው አማሪካ ለመጡት እና የበቆሎ ማሳ ውስጥ የታጠቁት ክላሽንኮቭ ለዛገባቸው ጎበዛዝት ነው ? በአየር ንብረት መለወጥ ምክንያት ፥ በቲማቲም ቆርቆሮ እንደሚሰራ ራዲያተር ተንተፋትፈው ለደርግ ለገበሩት እኩሌታ መኢሶኖችን ነው ወይስ ከሩሲያ ተጭነው ኢትዮጵያን ሊያለሙ የታሰቡ « ሰውን ሰው ያደረገው ስራ መሆኑን የሚያምኑ ቶሎስቶዊያንን ይሆን ?»
ይቺ ሌኒን አላት የተባለችው ጥቅስ እየገረመችኝ ነው ያደግሁት ። ምክንያቱም በሰው እና በስራ መሃከል ያለውን ልዩነት እና አንድነት እንዳንረዳ ሆነን ስላደግን ። ባንድ ግጥሜ ላይ
«ሰው በስራ ውሎ ግብሩ
እስተዳደጉ ይወጣል
ባንዳነትም እንደ ዛር ነው ሰባት ዘር ቆጥሮ ይመጣል »
ብዬ የከተብኳት ግጥም ምናልባት ፥ በስራ እና በማንነት ማሃል ስላለው መስተጋብር ለመናገር ፈልጌ ይሆናል ። እርግጥ ሌኒን እንደሚለው « ሰውን ሰው ያደረገው ስራ ከሆነ» ፥ የሌኒንን መጥሃፍ አንብበው እርስ በእርስ ተጋድለው የሞቱት ወንድሞቻችን እዚች ጥቅስ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ነበር እንዴ ጠቡን የጀመሩት ? እርግጥ ስራ የሰው ልጅ መገለጫ ይመስለኛል ። ግን ሰውን ሰው የሚያደርገው ስራ ነው ለማለት ይከብደኛል ። ምክንያቱም ከስራ በፊት የሚቀድሙ ብዙ የሰውነት መከሰቻዎች አሉና።
እንደውም አንዳንዴ ሳስበው ወያኔ ከተማ ከገባች በኋላ ይቺን የሌኒን ጥቅስ እኛ ሰፈር መስታወት ቤት ላይ ተለጥፎ አንብባ መሆን አለበት « ልማት ላይ ነን ! ለወሬ ግዜ የለንም ፥ እንደጀመርን እንጨርሰዋለን » እና ወዘተ እያሉ የሚያደናቁሩን ። እርግጥ የሰው ማንነት በሚሰራው ስራ ሊገለጥ ይችላል ብለን ልንሞግት እንችላለን ። የሰራው ነገር ግን ስለ ሰውነቱ ማረጋገጫ ሊሆን እንዴት ይችላል ። በስራ የሚለካም ሰውነት ካለ ሰውነቱ ቅቡል የሚሆነው ለሚወክለው ማህበረሰብ እንጂ ለሁልም ላይሆን ይችላል ። ምን ለማለት ነው ፥ ሂሮሽማ እና ናጋሳኪ ላይ የወደቀውን ቦምብ የሰራው ሰው ለአማሪካኖች ሰው ሊሆን ይችላል ፥ ለጃፓኖች ግን ነው ብሎ ማለት ግብዝነት ይመስለኛል ። መለስ ዜናዊ ለትግራይ ሰዎች ከሰራው ስራ አንጣር የሰው ጥግ ሊሆን ይችላል ፥ መለስ ከሰራባቸው ወገኖች ጎን እንደኔ ቆሞ ለሚያይ ሰው ግን ከድንቅነቱ ይልቅ ፊቴ ላይ ድቅን የሚልብኝ ውዳቂነቱ ነው ። ምን ለማለት ነው « ሰውን ሰው ያደረገው ስራ ሳይሆን የስራው በረከት ነው » ፥ ሰውን ሰው የሚያደርገው እንስሳ አለመሆኑ ነው ፥ የፈለገውን ማድረግ ( መስራት ) መቻሉ ብቻ ሳይሆን ፥ ፍላጎቱን ( ስሜቱን ) ተቆጣጥሮ ከፍላጎት ባሻገር ስላለ ጥቅም እና ጉዳት ማሰላሰል ፥ መመዘን ብሎ ስሜቱን ማሳለፍ እና መጣል መቻሉም ጭምር ነው ።
ስለሰሩ ሰው የተባሉትን ሳይሆን ፥ ሰው በመሆናቸው በስራቸው የተወደዱትን አምላክ ያብዛልን የሚል ነው የዛሬ መልዕክቴ። አለበለዚያ በዚህ ከቀጠልን ፥ በንክሻ እና በቡጭሪያ ሰውነታችንን ማስመስከር ትልቅነት ብሎም ስራ መስሎ ከታየን ፥ ከሰውነት ወደ አውሬነት ተጋምሰን ፥ በመግደላችን ፥ በማሰራችን ፥ ሰላም በመንሳታችን ፥ በማፈናቀላችን እና ህዝቡን በመሳሪያ አፈሙዝ በመደቆሳችን ሰውነታችን የወጣ አውሬዎች ከሆንን ማን ያውቃል የልጅ ልጆቻችን እኛ ሰፈር መስታወት ቤት ላይ « ሰውን ሰው ያ'ረገው የፊት ጥርሱ ነው» የሚል ጥቅስ ያነቡ ይሆናል ።
ቸር እንሰንብት

No comments:

Post a Comment

wanted officials