Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, June 16, 2016

ሰበር ዜና – በጅማ ቁንቢ ቅዱስ ሚካኤል አክራሪ ሙስሊሞች ጥቃት አደረሱ

ሰበር ዜና – በጅማ ቁንቢ ቅዱስ ሚካኤል አክራሪ ሙስሊሞች ጥቃት አደረሱ

eotc patriarchate edd
  • 2 ኦርቶዶክሳውያን እና 5 ሙስሊሞች መጎዳታቸው እየተገለጸ ነው
  • ከ4ቱ የጥቃቱ አድራሾች አንዱ ተይዟል፤ 3ቱ አምልጠዋል፤ ተብሏል
  • ሀ/ስብከቱ ከወረዳው የአስተዳደርና የጸጥታ አካላት ጋር እየሠራ ነው
 በጅማ ሀገረ ስብከት የም ልዩ ወረዳ ቁንቢ ቀበሌ፣ በቁንቢ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች፣ ዛሬ፣ ሰኔ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ማለዳ በአክራሪ ሙስሊሞች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተሰማ፤ በነዋሪ ሙስሊሞችም ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡
ምእመናኑ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው፣ በቤተ ክርስቲያኑ የኪዳን ጸሎት አድርሰው በሚመለሱበት ወቅት ነው፤ ተብሏል፡፡
በጥቁር አልባሳት ፊታቸውን የሸፈኑ አራት የጥቃቱ አድራሽ አክራሪዎች፣ ወደ አካባቢው በመኪና እንደ ደረሱ ጥቃታቸውን የጀመሩት፣ በቀጥታ በአካባቢው ወደሚገኝ አንድ መስጊድ በመግባት እንደኾነ ተገልጧል፡፡
“ግንባር፣ አንገት፣ እጅ እየመቱ ያገኙትን በስለት ጨፈጨፉ፤” ያለው የስፍራው ምንጭ፣ በጭፍጨፋው አምስት ሙስሊሞች(አክራሪዎቹ እንደ ከሐዲ/ካፊር የሚቆጥሯቸው ነዋሪዎች) ክፉኛ መቁሰላቸውን ተናግሯል፡፡
ከመስጊዱ እንደወጡ ወደ ቁንቢ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አቅጣጫ በማምራት፣ የኪዳን ጸሎት አድርሰው በመመለስ ላይ በነበሩ ምእመናን ላይም በቀጠሉት ጥቃት፤ ኹለት ምእመናንን ክፉኛ አቁስለዋል፤ ከቆሰሉት የአንዷ እጇ በጥቃቱ ተቆርጦ ከቆይታ በኋላ መገኘቱ ተጠቅሷል፡፡ 
ከጥቃቱ አድራሾች ሦስቱ በመጡበት መኪና ከአካባቢው በመሰወር ያመለጡ ሲኾን፣ አንዱ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ታውቋል፡፡ “ወደ ጅማ አቅጣጫ ነው የነዱት፤ ቅስቀሳቸውንና ጥቃታቸውን ከማስፋፋታቸው በፊት በተጠናከረ ክትትልና አሠሣ ሊያዙ ይገባል፤” ይላል አንድ የአካባቢው ነዋሪ፡፡
በጥቃቱ ከተጎዱት ምእመናን፣ ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የደረሱ መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡
የቁንቢ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሚገኝባት የም ልዩ ወረዳ፣ በሰኩሩ እና ናትሪን መካከል ያለችና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ምእመናን፣ ከሚበዙት የእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር በመከባበርና በመገናዘብ የሚኖሩባት ወረዳ እንደ ኾነች ተመልክቷል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ እና ጽ/ቤታቸው፣ የተጎዱትን ምእመናን ለመርዳትና ጥቃት አድራሾቹን ለመቆጣጠር ከወረዳው አስተዳደርና የጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት እየሠሩ መኾኑ ተገልጧል፡፡
በጅማና በኢሉባቦር አህጉረ ስብከት ዴዴሳ ወረዳ፣ ክርስቲያኖች፣ የጦር መሣርያና ገጀራ በያዙ አክራሪዎች ተደጋጋሚ ጥቃት(ግድያ፣ ዘረፋ፣ የቤትና የንብረት ውድመት፣ መፈናቀልና ፆታዊ መደፈር) ሲፈጸምባቸው ቆይቷል፡፡ ከመስከረም 16 ቀን 1999 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩት ተከታታይ ቀናት፥ በጎማ፣ በማና እና በቶባ 12 ክርስቲያኖችን ገድለው፣ ሦስት አብያተ ክርስቲያናትን (የጨጎ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቦሬ ቅዱስ ገብርኤል እና በሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ) አቃጥለው ንዋያተ ቅድሳቱን ከመዝረፋቸውም በላይ፤ ከ800 በላይ የአባ ወራ ቤቶችን በማቃጠል ከቀዬአቸው ማፈናቀላቸውና በግዳጅም ማስለማቸው ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials