Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, June 4, 2016

ማንነት፣ ብሔርተኝነት እና ዜግነት ዘላለም ክብረት እና በፍቃዱ ኃይሉ

‹የማንነት ጥያቄ› ከማናቸውም ጊዜ በላይ አሁን እየገነነ የመጣ ይመስላል። ‹የጥያቄው ምንነት፣ መነሻው እና መድረሻው ምንድን ነው?› የሚሉትን ጥያቄዎች በመምዘዝ ዘላለም ክብረት እና በፍቃዱ ኃይሉ የውይይት ሐተታ አድርገው አቅርበውታል።

በአለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ ተጽፈው እጅግ አወዛጋቢ ከሆኑት መጽሐፍት መካከል ‹ስለ ጋሞ ሕዝብ ታሪክ አዲስ አተያይ ይዤ መጥቻለሁ› ያለው በአቶ ታደለ ቱፋ የተጻፈውን ‹ማዶላ› የተሰኝ መጽሐፍ የሚያክል አወዛጋቢ መጽሐፍ አለ ለማለት አይቻልም። የውዝግቡ ዋነኛ ትኩረትም ‹መጽሐፉ የጋሞ ብሔርን ሕልውና የሚክድ ነው› የሚለው ሲሆን፤ በተነሳው ውዝግብ ምክንያትም የመጽሐፉ ደራሲን ለእስር ከመዳረግ ጀምሮ መጽሐፉን እስከ ማቃጠል ድረስ የዘለቀ ሁኔታ ነበር የነበረው። የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት (ጋዴሕ) መጽሐፉን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በነሐሴ ወር 2007 በጻፈው ደብዳቤ መጽሐፉ ‹የጋሞ ብሔርን ሕልውና አደጋ ላይ ይጥላል፤ በብሔሩ መብት፣ ክብርና ማንነት ላይ አነጣጥሯል› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን የስድብ መጽሐፍ አንድ እንዲሉት ተማጽኗል። ነገር ግን መጽሐፉ ከአወዛጋቢነቱ ባለፈ አዲስ ማንነት የመገንባት ሒደት ላይ ትኩረት አድርጎ እናየዋልን። ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በመጽሐፉ ገጽ 29 ላይ ‹የኖህ መርከብ የተነሳባት ማላ ዶጋላ (የጋሞ ምድር) […] [ነች]› የሚል ማንነትን (Identity) ወደ ኋላ በመሔድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ለማስያዝ የተደረገን ጥረት እንመለከታለን።
ከደቡባዊው የሀገሪቱ ጫፍ ርቀን ወደ ሰሜን ምዕራብ የሃገሪቱ ጫፍ ስንጓዝ ደግሞ የአይከል ከተማን እናገኛለን። በቀድሞ አጠራሯ ጭልጋ እየተባለች የምትጠራውና በአሁኑ ስሟ አይከል ከተማ በያዝነው ዓመት ከማንነት ጋር ተያይዞ ታላቅ ትኩሳት ሲያተኩሳቸው ከነበሩት የሀገሪቱ ከተሞች አንዷ ስትሆን፤ የትኩሳቱም መነሻ የቅማንት ብሔረሰብ መንግሥታዊ ዕውቅና ከማግኝቱ ጋር የተያያዘ ነው። አይከል የቅማንት ብሔረሰብ መዲና እንደሆነች እየተነገረ ሲሆን ስያሜዋን አስመልክቶም የብሔረሰቡ ትውፊት እንደሚያስረዳው አይከል ማለት ሐይከል (Haykêl) ከሚለው የሰው ሥም የተወሰደ  ቃል ሲሆን ሐይከል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ኖህ ሚስት ሥም ነው የሚል ነው። ትውፊቱም ሔዶ ሔዶ የኖህ መርከብ ማረፊያዋ በቅማንት ምድር ነበር፤ የኖህ ባለቤት ሐይከልም የተቀበሩት በቅማንት ምድር በዛሬዋ አይከል ከተማ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳል።
የሁለቱን ማኅበረሰቦች ልኂቃን ‹የኖህ መርከብ በጋሞ ምድር ላይ ተነስታ በቅማንት ምድር አርፋለች› የሚል ምናብ ስንመለከት የምንረዳው ነገር፤ የራስን ማንነት ለማጉላት የማኅበረሰቦቹ ልኂቃን የቱን ያክል ርቀት እንደሚሔዱ ነው።

የማንነት ፖለቲካ
ማንነት (Identity) በዓለም ላይ በፍጥነት የተለያዩ ቅርፆችን እየያዘ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ አውራ የማንነት ጥያቄዎችን (dominant identity questions) መልክ ሲቀያየር እናያለን። የማንነት ፖለቲካ በተለይም በዚህ ዘመን በምዕራቡ ዓለም ብዙ መንኳሰስ እየቀረበበት የሚገኝ ሐሳብ ነው። ቶድ ጊቲን የአሜሪካ የማንነት ፖለቲካ ላይ መሠረት አድርገው በጻፉት ‘The Twilight of Common Dreams’ የተሰኝ መጽሐፋቸው የማንነት ፖለቲካን ሲተረጉሙት ‘Groups overly concerned with protecting and purifying what they imagine to be their identities’ (ማንነቴ ነው ብለው የሚያስቡትን በመጠበቅና ማጥራት ጉዳይ ሲበዛ የተጠመዱ ቡድኖች) በማለት ማንነት፣ ማንነቱ አለን የሚሉት ቡድኖች በራሳቸው ቅዥት (self delusion) የሚፈጥሩት ምናባዊ ኹነት እንደሆነ ያስረዳሉ። በተመሳሳይ ብዙ ማርክሲስቶችና የሊብራሊዝም ሊቃውንት የቡድን ማንነትን ‹ለቁም ነገር የማይበቃ የቡድን ቅዠት ነው› በማለት ሲያጣጥሉት ይታያሉ። ከዚህ መሰል አሉታዊ ግንዛቤ በተቃራኒው ደግሞ እንደ ታላቁ ፈላስፋ ቻርለስ ቴይለር ያሉት ደግሞ የማንነት/የልዩነት ፖለቲካ መነሻ ለክብር የሚደረግ እንቅስቃሴ መሆኑን በመግለጽ ማንነትን መሠረት አድርጎ የሚካሔድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሁሉ አሉታዊ እንዳልሆነ ይገልጻሉ። ከዚህም ባለፈ የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የሕግ ሊቁ ሪቻርድ ፓርከር በበኩላቸው አምስት የማንነት ፖለቲካ አንብሮዎች (thesis) በዘረዘሩበት መጣጥፋቸው በቅድሚያ ያስቀመጡት “ሁሉም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የማንንት ፖለቲካ” (‘all politics is identity politics’) መሆኑን በመግለጽ፤ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሁሉ ፉክክርን እና ልዩነትን መሠረት ያደረገ በመሆኑ በተዘዋዋሪ መንገድ ‘ሁሉም ፖለቲካ መሠረቱ ማንነት ነው’ ይሉናል። ፕ/ር ፓርከር ጭብጣቸውን ሲያጠናክሩ “…የማንነት ፖለቲካ እና የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ነጻነት በመርሕ እና ብዙ ጊዜ በተግባርም እርስበርስ የሚደጋገፉ ብሎም አንደኛው የሌላኛውን ሕልውና የሚያረጋግጡ ናቸው” እስከማለት ይደርሳሉ።
የማንነት ፖለቲካ ‹ከምስስሎሽ እና ትስስሮሽ ይልቅ ልዩነት እና ብሶትን አጉልቶ የማውጣት ፖለቲካ ነው› ለሚለው ሙግት ፕሮፌሰር ፓርከር የተለየ ምላሽ አላቸው። ‹ልዩነት እንዲያውም ራስን ለመረዳትና ለመግለጽ (self‐assertion) ወሳኝ ጉዳይ ነው። ብሶትም ቢሆን ፖለቲካዊ ነጻነት ለማምጣት የሚያነሳሳ ነዳጅ ሆኖ ስለሚያገለግል ልንቀበለው እንጂ ፈፅሞ ልንጠላው አይገባም› በማለት ይሟገታሉ። ፕ/ር ፓርከር ይልቁንም አደገኛ ብለው የሚያስቡት የማንነት ፖለቲካን የምንመለከትበት እና እንድናፍነው የሚያስገድድ ብለው የሚሏቸው አዝማሚያዎችን ነው። የማንነት ፖለቲካን እንደአንድ ሕልው (ለምሳሌ ሥርዓተ-ፆታ) ተፈላጊ ሁኔታ (essentialism) አድርጎ መውሰድ ሲቻል፣ በበዳይ (demonization) - ተበዳይ (victimhood) አዝማሚያዎች መረዳት ጠቃሚ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፤ ‹wrongdoers have no identity› (ክፉ አድራጊዎች ማንነት የላቸውም) በማለት።   
ከሁለቱም ወገኖች ብያኔ መሐል ላይ ሊሰፍር የሚችል ትርጉም የሚሰጠን የማክሚላን ፖለቲካዊ እሳቤዎች መዝገበ ቃላት የማንነት ፖለቲካን “ሕዝቦች ስለማን እና ምንነታቸው በቅድሚያ ካላወቁ እና አንዱ የሌላውን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት በጋራ ዓላማና መተማመን ለምን መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ካላወቁ በስተቀር ስኬታማ አይሆኑም በሚል እምነት፣ ማንነትን ቀዳሚ አጀንዳው የሚያደርግ የፖለቲካ ገቢር ነው” በማለት ያፍታታዋል።
ነገር ግን ማንነት ሰፊ ዘርፎችን ያቀፈ ከመሆኑ አንፃር ፖለቲካዊ መልክ ብቻ መስጠቱ ማንነትን ማሳነስ ከመሆኑም በላይ ስለ ማንነት ያለንን ግንዛቤም ዝቅ ያደርገዋል።
በዛሬዋ ኢትዮጵያ ካሉ የዘርፈ ብዙ የማንነት ጥያቄዎች መካከል ሌሎች የማንነት ጥያቄዎች የሌሉ ያክል እስኪሰማን ድረስ የዘውግ ማንነት (Ethnic Identity) ጉልሁን ድርሻ ይዞ ይገኛል። ለአንዳንዶች ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያን አገረ-መንግሥት (state) የሚያፈራርስ መስሎ ሲታያቸው፤ ለሌሎች ደግሞ የጥያቄው መልስ ማግኝት ብቻ ነው ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የሚያቆያት።

የዘውግ ማንነት ሽንኩርታዊ ባሕሪ
የማንነት ፖለቲካ የዘውግ ማንነት ላይ ብቻ ያለቅጥ ማተኮሩ ዓለም እየተጓዘችበት ካለችው መንገድ - ሉላዊነት (globalization) ሊያፈነግጥ ይችላል። ግሎባላይዜሽን ‹ማንነታችን በኃያላኑ አገራት ይዋጥብናል› የሚል ስጋት ውስጥ የከተታቸው አገራት በሮቻቸውን ከሌሎች አገራት (በተለይም ከምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔ ለመሸሸግ ሲሉ) ዘግተዋል። በተለይም የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ከነዚህ ተርታ ተጠቃሽ ናቸው። አንዳንዴ የሽብር ጦስ ከዚሁ በሉላዊነት ሰበብ በባሕል (እና ማንነት) የመዋጥ ፍራቻ እንደሚመነጭ የሚከራከሩ አሉ። እነቻይናም ለምዕራቡ ትርክትና መገናኛ ብዙኃን በራቸውን የዘጉት (ምንም እንኳን ‹ፖለቲካዊ ሰበብ ነው› እየተባለ ቢተችም) በሕጋዊ ድንጋጌ ማንነታችን በምዕራባውያን እንዳይዋጥ በሚል ምክንያት ነው። ይህ አገረ-መንግሥታት (states) ራሳቸውን (ማንነትን በመጠበቅ ሰበብ) ከውጪው ዓለም ለመነጠል የሚሰጡት ምክንያት በአገር ውስጥ ባሉ ግንኙነቶች (intra-state relations) ሲንፀባረቅ ማቆሚያ እያጣ ይመጣል። በአንድ አገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ ማንነቶችን ‹እንዳይበረዙ› መጠበቅ ከሌሎች ላለመቀላቀል በርን መዝጋት ለራሱ ለብሔረሰቡም ይሁን ተጎራባች/ተዛማጆቹ የማይመች አካሔድ ነው። የጠራ ማንነትን ለማግኘት የማንነት መሥፈርቱ እየጠበበ በሄደ ቁጥር በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ሌላ ማንነት ያለው ሌላ ማኅበረሰብ፣ በዚያም ውስጥ ሌላ ማኅበረሰብ እያገኘን በቤተሰብ የሚቆጠር ስብስብ ላይ ልንደርስ እንችላለን። ይሄን የማንነት ሽንኩርታዊ ባሕሪ የፍልስፍና ሊቁ አንድሪያስ እሸቴ 'Beyond National Self-Determination’ ባሉት ጽሑፋቸው ‘[ማንነትና] ብሔርተኝነት ከአጠቃላይ መለያቸው ባለፈ በትንንሽ የማንነት ጥያቄዎች የሚናጡ በመሆናቸው በመሠረቱ ወለፈንድ (absurd) ናቸው’ በማለት ይገልጹታል።

ኢትዮጵያና የዘውግ ማንነት ከፍና ዝቅ
ጀማል ዲጋ (ሥሙ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል የተቀየረ) በጉራጌ ዞን፣ የቀቤና ማኅበረሰብ አባል ነው። ፍቅረኛው ከሰባት ቤት ጉራጌ ብሔረሰብ አባላት ነው የተወለደችው። ሁለቱ ፍቅረኛሞች ተፈቃቅደው ከጨረሱ በኋላ፣ ጀማል ለቤተሰቦቹ ኒካ ሊያስር (ከፍቅረኛው ሊተጫጭ) እያቀደ መሆኑን ሲነግራቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው። ተቃውሞው የመነጨው ደግሞ ፍቅረኛው የቀቤና ማኅበረሰብ አባል ባለመሆኗ ነው። ጀማል ከቤተሰቦቹ የደረሰው ማሳሰቢያ ‹እሷን ካገባህ ከእኛ ጋር ያለህ እህል ውኃ አልቋል› የሚል ነበር። የጀማል የመጨረሻ ውሳኔው ከፍቅረኛው መለያየት ነው። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ይህ ዓይነቱ ገጠመኝ የጀማል ብቻ አለመሆኑን ነው።
ይህ ዓይነቱ አዝማሚያ በማንነት ፖለቲከኞቹ እየተኮተኮተ፣ ባሕል እና ቋንቋን በመጠበቅ ሥም ከሌሎች አለመቀየጥን ወደ ማበረታታት ሲያድግ አደገኛ አዝማሚያ ይኖረዋል። ባሕል መወራረስንም ሆነ ከሌሎች መቀላቀልን ለማንነት ጠንቅ አድርጎ መውሰድ አይቻልም። ማንነት እንደ ማንኛውም ባሕላዊ እሴት የሚወለድ፣ የሚያድግ እና የሚሞት መሆኑን በማንነት ፖለቲከኞቹም ይሁን በኅብረተሰቡ ውስጥ በትምህርት ማስረጽ አስፈላጊ ነው የሚሆነው።   
ብዙ ጊዜ የማንነት ጥያቄ የፖለቲካ ልሒቃን በቀላሉ ሕዝብ የማነቃነቂያ (mobilization) መሣሪያ ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል። ነገር ግን ማንነት በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ሚናም መመልከት ጥያቄውን እንዴት መመለስ እንደሚያስፈልግ ለመረዳት ያስችላል።
ዘውግ (ethnicity) በተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪነት ብቻ እንደማይበየን በዘርፉ የረዥም ዓመት ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ፍስሐ አስፋውን ጨምሮ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው። ይሁን እንጂ አሁን አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ከማንነቶች ሁሉ ገዝፎ የሚታየው ማንነት በዚሁ በተመሳሳይ ቋንቋ ተናጋሪነት ላይ የተመሠረተው የዘውግ ማንነት (Ethnic Identity) ነው። በአንድ በኩል ዘውግን በቋንቋ የሚበይነውን የዘውግ ማንነትን መሠረት ያደረገ የፌደራል ስርዓት መኖሩ፤ በሌላ በኩል የተለየዩ ዘውጎችን የሚወክሉ ልኂቃን እነሱ የሚወክሉትን ዘውግ ጥቅም ማስከበር የለውጥ መሠረት መሆኑን መነሻ አድርገው መንቀሳቀሳቸው የዘውግ ማንነትን የኢትዮጵያዊያን የቀን ተቀን ግንኙነትና መሠረት አድርጎታል።
ለዚህ የዘውግ ማንነት ጥያቄ ማበብ ወይም ማንሰራራት ብዙዎች ሙገሳውን/ወቀሳውን ለስልሳዎቹ ማርክሲስት ትውልድ በመስጠት ሲያወድሱ/ሲነቅፉ ይስተዋላሉ። ነገር ግን ልኂቃኑ ያልነበረን ጥያቄ አራግበው ለዚህ አደረሱት ብሎ ማመኑ ለራስ ምቾት ከመስጠት ባለፈ መሠረታዊውን የጥያቄው የትኩረት ነጥብ ያገኘ ነው ማለት አይቻልም።
በዘውግ ማንነት ላይ ብዙ ጥናቶችን ያደረጉት የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ጀን ፒኒ የዘውግ ማንነት አንድ ነገር ላይ ረግቶ የሚቆም ነገር እንዳልሆነ በማስረዳት ‹ግለሰቦች በማኅበረሰባቸው ውስጥ ራሳቸው ያላቸውን ቦታ የበለጠ እያወቁ በሄዱ ቁጥር የራሳቸውን ጠንካራ/አዲስ የዘውግ ማንነት እየገነቡ ይሄዳሉ› ይላሉ። በሌላ በኩል ሊቁ ዳንኤል ቤል የ1960ዎቹን የዘውግ ማንነት ውጣ ውረድ በዳሰሱበት ‘Ethinicity and Social Change’ መጽሐፋቸው ዘውግ የተገፉ ቡድኖች መብታቸውን ለማስጠበቅ እና የተነፈጉትን ክብር ለማስመለስ የሚጠቀሙበት መሣሪያ እንደሆነ በመግለጽ የዘውግ ማንነት ማቆጥቆት ጭቆናን ከማስወገድ ጋር በማመሳሰል ይተነትናሉ።
እንግዲህ የዘውግ ማንነት ሰዎች ስለተነገራቸው ብቻ የሚለብሱት ነገር ሳይሆን ጥልቅ ሥነ ልቦናዊ ኹነትም ነው ማለት ነው። ይሄን ጥልቅ ጉዳይ የአንድ ትውልድ ጣጣ ብቻ አድርጎ ማቅረቡም የጉዳዩን ጥልቅ መሠረት ያለመረዳት የዋህነት ከመሆን አይዘልም።
የወታደራዊው መንግሥት በመጨረሻው የሥልጣን ዘመኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዘውጎችን ጥያቄያቸውን በሕጋዊ ስርዓት ማስተናገድ ተገቢ መሆኑን በማመን እና ‹…በሕዝብ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ብሔረሰብን ምርኩዝ ያደረገ ዘለቄታ ያለው የአስተዳደር ክልል እና ሕገ-መንግሥት ለመንደፍ…› በማሰብ ‹የብሔረሰቦች ጥናት ተቋም› የተባለ ተቋም በማቋቋም እስከ አሁን ድረስ የላቀ ሁኖ የሚታየውን ጥናት በኢትዮጵያ ዘውጎች ላይ ያደረገ ሲሆን፤ በጊዜው የተቋሙ አባላት የነበሩ ግለሰቦች እንደሚገልጹት ኢሕአዴግ ወደሥልጣን በመጣበት ጊዜ የዘውግ ስርዓት ለመዘርጋት የተጠቀመበትም የተቋሙን ጥናት እንደሆነ ይገልጻሉ። በወቅቱ የተቋሙ አባል የነበሩት ሶሺዎሎጅስቱ ዶ/ር ፍስሐ አስፋው ተቋሙ የሠራው ሥራ እጅግ ጠቃሚና ዛሬ ላሉ የማንነት ጥያቄዎች መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን አቅርበው የነበሩ መሆናቸውን ያስታወሳሉ።
ኢሕአዴግ በሽግግር መንግሥቱ ወቅት ‹የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳደሮችን ለማቋቋም› በሚል ባወጣው አዋጅ ቁጥር 07/1984 በተቋሙ ጥናት ላይ ከተጠቀሱት ዘጠኙን የኤርትራ ብሔረሰቦች ጨምሮ ሰባ አምስት ብሔረሰቦች መካከል ስልሳ ሦስት የሚሆኑትን ብሔረሰቦች በዐሥራ አራት ክልሎች አዋቅሯል። ይህ የዘውጎች ቁጥር በየጊዜው አንዳንዶቹን እያጠፋና ሌሎችን እየጨመረ አሁን ከሃያ አራት ዓመታት በኋላ ሰባ ስድስት ዘውጎችን በዘውግነት ተቀብሎ የሚገኝ ቢሆንም፤ ሌሎች ማኅበረሰቦች በዘውግነት እንዲታወቁ ጥያቄያቸውን አፋፍመው ቀጥለውበታል። ኢሕአዴግም ይሄን ጉዳይ በመርሕና በሕግ አግባብ ከማስተናገድ ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠትን (ማፈንን ጨምሮ) እንደ አማራጭ ይዞ በመሔዱ ራሱ በሚያነደው እሳት እየተጠበሰ ይገኛል። ይህ የዘውግ ማንነት ጥያቄ ከማንነት አጠቃላይ ተለዋዋጭ (dynamic) ባሕርይ አንፃር እንዲሁም ጥያቄውን በሕግ አግባብና በዘላቂነት  ማስተናገድ የማይችል ኃይል በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ እየጨመረ የሚሔድና ገና ብዙ ርቀት የሚያስኬድ መሆኑ አይቀሬ ነው።

‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ የለም›
ዘውግን መሠረት ያደረገ የማንነት ጥያቄ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ገፍቶ ወደ አደባባይ መውጣቱ ለብዙዎች የፖለቲካል ኢኮኖሚውን ለመረዳት እንደ አንድ መሠረት እየተወሰደ ያለ ነገር ነው። ማንነትን እንደ ትልቅ የአገዛዝ መሣሪያ የሚያየው ገዥው ፓርቲ ግን አሁን የማንነት ጥያቄን ማራገቡ ለራሱ የማይበጀው መሆኑን በግልጽ እየተናገረ እንደሚገኝ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ባለፉት ወራት ውስጥ የተሰጡትን መንግሥታዊ መግለጫዎችና ማብራሪያዎች መመልከቱ ብቻ ይበቃል።
ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ መጋቢት 01/2008 ፓርላማ ቀርበው ከማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ከፓርቲያቸው አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ የለም። የማንነት ጥያቄ ተመልሶ አልቋል የሚል ምላሽ መሰጠት አለበት› በማለት ነበር። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ለብዙዎች አስገራሚ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ ‹የአፍ ወልምታ ሊሆን ይችላል› የሚል መላምት ከብዙዎች ዘንድ እንዲሰነዘር አድርጎ ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሆኑት አቶ ታገሰ ጫፎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ‹ማንነትን ለንግድ የሚጠቀሙ ግለሰቦች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው› በማለት ሊያለዝቡት ቢሞክሩም፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማያሻማ አነጋገር ግን መንግሥታቸው ራሱ መሠረታዊ የፖለቲካ ካርድ አድርጎ እየተጫወተበት የነበረው የማንነት ፖለቲካ ሰለባ መሆኑን አመላካች ነበር።

የሁለት ዘውጎች ወግ
‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ የለም። የማንነት ጥያቄ ተመልሶ አልቋል› የሚለው አስተያየት መሬት ላይ ያለን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ያለማስተዋል ውጤት ነው ብለን ከመደምደም ባለፈ በሦስት የተለያዩ መሠረታዊ ምክንያቶች የተሳሳተ እንደሆነ መረዳት እንችላለን።
የመጀመሪያው ማንነትን ቋሚና የደም ጉዳይ ብቻ አድርጎ የመመልከት ስህተት ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆኑ ዘንድ የዶርዜንና የቅማንትን ዘውጎች እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል።
የዶርዜ ዘውግ በወታደራዊው መንግሥት የመጨረሻ የሥልጣን ዘመናት የተደረገውና የሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገው ‹የብሔረሰቦች ጥናት ተቋም› ጥናት ላይ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ብሔረሰብ ተመዝግቦ “የዶርዜ ማኅበረሰብ በጋሞ ጎፋ ክፍለ ሀገር፣ በጋሞ አውራጃ፣ በአርባ ምንጭ ዙሪያና በጨንቻ ወረዳዎች፣ በጎፋ አውራጃ በጎፋ ዙሪያ ወረዳ ይኖራል” ተብሎ የተገለፀ ሲሆን፤ በ1987 ሕዝብና ቤት ቆጠራ ወቅትም በብሔረሰብነት ተቆጥሮ ነበር። ነገር ግን በ1999 በተደረገው የአገርዐቀፍ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ዶርዜ ራሱን የቻለ ብሔር መሆኑ ቀርቶ የጋሞ ብሔረሰብ ውስጥ ካሉ ሃምሳ ጎሳዎች እንደ አንዱ በመሆን ተመዝግቧል። የክልሉ ምክርቤትም ይሄን ጉዳይ አፅድቆት በአሁኑ ወቅት ዶርዜ የሚባል ብሔር/ብሔረሰብ በመንግሥት ደረጃ አይታወቅም።
በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ በብሔረሰብነት በመንግሥት ደረጃ ዕውቅና ያገኘውን በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኝውን የቅማንት ብሔረሰብ እናገኛለን። በወታደራዊው መንግሥት ወቅት ተቋቁሞ የነበረው ‹የብሔረሰብ ጥናት ተቋም› ጥናት ላይ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ብሔረሰብ ተመዝግቦ “የቅማንት ማኅበረሰብ በጎንደር ክፍለ ሀገር፣ በወገራ አውራጃ በወገራ ወረዳ፣ በጎንደር ዙሪያ አውራጃ በላይ አርማጭሆ በጎንደር ዙሪያና በደንቢያ ወረዳዎች እንዲሁም በጭልጋ አውራጃ በጭልጋና በማጠቢያ ወረዳዎች፣ በጎጃም ክፍለ ሀገር በመተከል አውራጃ በዳንጉር ወረዳ ይገኛል። ቅማንት በጎንደር በአማራና በትግራይ ትግሪኝ መሐል፣ በጎጃም በአማራ፣ በጉሙዝና በሽናሻ መሐል ተቀላቅሎ ይገኛል” ተብሎ የተገለፀ ሲሆን፤ የቅማንት ብሔረሰብ በ1987 ሕዝብና ቤት ቆጠራም ላይ እንደ ብሔረሰብ ተቆጥሮ ነበር። ነገር ግን በ1999ኙ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በአማራ ብሔርነት ተመዝግቦ ብዙ ውዝግብ አስነስቶ ነበር። እንደገና በ2007 በአማራ ክልል ምክር ቤት በተደረገ ውሳኔ የቅማንት ሕዝብ በድጋሚ በብሔረሰብነት ዕውቅና ተሰጥቶታል። ከዚህ የምንረዳው በኢሕአዴግ መሥፈርት እንኳን ከሃያ ዓመታት በፊት ዶርዜ የነበረ ሰው ዛሬ ጋሞ ተብሎ በመንግሥት ሲታወቅ፣ የያኔው ቅማንት አማራ ሁኖ ከርሞ አሁን ደግሞ ወደ ቅማንትነት ተመልሷል። ይህን መሰል ሁኔታዎች ስንመለከት ማንነት ተለዋዋጭ (dynamic) ጉዳይ እንጅ እንዲሁ ለዘላለም ተለብሶ የሚቆይ ብልኮ አለመሆኑን ነው። በዚህ አግባብም ‹በኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄ ተመልሶ አልቋል› ማለት ምንም ያክል ፋይዳ የሌለው ጉዳይ ነው።
ሁለተኛው ‹የማንነት ጥያቄ አክትሞለታል› የሚለው መከራከሪያ ስህተት የሚመነጨው ደግሞ ማንነትን ከዘውግ ጉዳይ ጋር ብቻ አያይዞ የመመልከት ሸውራራ ዕይታ ነው። አንድ ግለሰብ እንደ ግለሰብ፣ እንዲሁም አንድ ማኅበረሰብ እንደ ማኅበረሰብ የራሱ የሆኑ ከአንድ በላይ የሆኑ መገለጫ ማንነቶች (Authenticity) ሊኖሩት ይችላሉ (በአብዛኛው አለው)። ሃይማኖታዊ፣ ዘውጋዊ፣ ፖለቲካዊ… ማንነቶችን በአንድ አጣምሮ መያዝ የአብዛኛው የሰው ልጅ ደንብ ነው። በዚህ ሁኔታ ዘውግን ብቻ ነጥሎ ማንነት በዚህ አገር ውስጥ ብቸኛ መጠሪያው ዘውግ ነው በሚል የተሳሳተ መነሻ (premise)፤ የተሳሳተና መሬት ላይ ያለን ችግር የማይፈታ ‹የአብቅቶለታል› ድምዳሜ መሠረታዊ ስህተት ነው የሚሆነው።
ሦስተኛውና የማንነት ጥያቄ ተመልሶ አልቋል ከሚለው መደምደሚያ ተነስተን ልናየው የሚገባን ነገር፤ አንድ ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ራሱን በፈለገው ማንነት እየጠራ እያለ፤ ሌላ ማንነት የመጫን ጉዳይ ነው። አንድ ማኅበረሰብ እኔ እከሌ የምባል ዘውግ ነኝ፤ ማንነቴም በዚሁ ዘውግ የሚገለጽ ነው እያለ› እይያለ፣ ‹አይ፣ የማንነት ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመልሶ አልቋል፤ እናንተም የዚህ ዘውግ አባላት ናችሁ› ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ የማይፈለግ ማንነትን ከመጫኑም ባለፈ ራሱን የአገረ-መንግሥቱ አካል አድርጎ (belonging) እንደያስብ እና እንዲነጥል (auto-segregation) የሚገፋ ነው የሚሆነው። በሌላ አነጋገር አንድ ዘውግ ለብቻው በመንግሥት ተቀባይነት አላገኝም ማለት ያ ዘውግ የለም ማለት አይሆንም።

የዘውግ ማንነት ጥያቄ እየጨመረ መጥቷል?
ፕ/ር ዓለም ሀብቱ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2003 ‹Ethnic Federalism in Ethiopia› በሚል ርዕስ በሠሩት ጥናት ላይ ያያያዙት የሕዝብ ብዛት እንደሚያመለክተው በ1983፣ ሰባ ዘጠኝ የዘውግ ቡድኖች ነበሩ፤ በ1993 ደግሞ ስልሳ ሰባት ብቻ ሆነዋል። ሁለቱም ቁጥሮች የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ ለማመልከት እንደሞከርነው በሽግግር መንግሥቱ ወቅት ‹የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳደሮችን ለማቋቋም› በሚል ባወጣው አዋጅ ቁጥር 07/1984 ስልሳ ሦስት የሚሆኑት የዘውግ ቡድኖችን የምናገኝ ሲሆን፤ ዛሬ በፌደሬሽን ምክር ቤት ወንበር ያላቸው ሰባ ስድስት ዘውጎች እንዳሉ ምክር ቤቱ ገልጾ እናገኛለን። በዶ/ር ፍስሐ አስፋው በቅርቡ ‹የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን የሚገልጥ ጥናታዊ መዘክር› በሚል ርዕስ በወታደራዊው መንግሥት ወቅት ተቋቁሞ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረገውን ‹የብሔረሰቦች ጥናት ተቋም› የጥናት ውጤት ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ እንደዘረዘሩት ደግሞ፣ በወቅቱ በተደረገው ጥናት መሠረት ሰማኒያ ዘጠኝ ብሔረሰቦች ነበሩ።

እነዚህ የተደበላለቁ የቁጥር ከፍታ እና ዝቅታዎች የማንነት ጥያቄ በየወቅቱ ሲጨምር ሲቀንስ የተፈጠሩ ናቸው ወይስ በማንነት ተቀያያሪ ፀባይ ባለፉት ሁለት ዐሥርታት ብቻ የጠፉና የተወለዱ ዘውጎች በመኖራቸው? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ የሚፈልጉ ናቸው። ብዙዎች የማንነት ጥያቄ እየጨመረ መምጣቱን አሁን ድረስ መልስ ያላገኙ የተለያዩ ብሔረሰቦችን እየዘረዘሩ ይሟገታሉ። ለዚህ በዋነኛ ምክንያትነት የሚያስቀምጡት የዘውግ ማንነት ላይ ያተኮረውን ፌዴራሊዝም ነው። ከዚህም ተነስተን ‘ፌዴራሊዝሙ የማንነት ጥያቄን አባብሶታል ወይ?’ የሚል ጥያቄ ለመጠየቅ እንገደዳለን?

በታኅሣሥ ወር 2008 የታተመው የዶ/ር ፍስሐ አስፋው “የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን የሚገልጥ ጥናታዊ መዘክር” መጽሐፍ የመግቢያ ማስታወሻው ላይ “የንጉሡን አገዛዝ አውርዶ በትረ-ሥልጣኑን የጨበጠው ወታደራዊ መንግሥት ከተራማጅ ኃይሎች ከቀረቡለት ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች መሬትን በአዋጅ የሕዝብ ሲያደርግ የሁለተኛው ‹የብሔረሰብን ዕኩልነት› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በወቅቱ ቀላል ሆኖ አላገኘውም” ይሉና ጥያቄውን ለመመለስ ምሁራን ተሰባስበው የተለያዩ ተቋማት እንደተመሠረቱ ይነግሩናል። ይሁን እንጂ የጥናቱ ውጤት ምን ዓይነት አስተዳደር “የብሔረሰብ ዕኩልነት” ጥያቄን ይመልሳል የሚለውን ደራሲው በ‹መዘክሩ› አይነግሩንም።

የብሔረሰብ ጥናት ተቋም የነበሩት አቶ አሰፋ ጫቦ ጥናቱ በተደረገበት ወቅት ለዘውግ የማንነት ጉዳይ “በመላ-ምት ሳይሆን ጥናት ላይ በተመሠረተ መፍትሔ ለመሻት እንቅስቃሴ መደረጉን አስታውሰው፤ የዚያ ጥናት ውጤት ሰባት የመፍትሔ አማራጮችን ያቀፈ እንደነበርም ይገልጻሉ። አሰፋ “ኢሕአዴግ ከዚህ የደርግ ጥናት ውስጥ ሰባተኛ የነበረውን አማራጭ ወስዶ አገሪቱን ‹ክልል› በሚል መጠሪያ አዋቀረ…” ብለው ድምዳሜ ላይ የሚደርሱ ሲሆን፤ ለዚህ ተመሳሳይ ሐሳብ ለዶ/ር ፍስሐ ላቀረብንላቸው ጥየቄ ይህን በተመለከተ ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‘’እኛ እንደመፍትሔ ያቀረብናቸው ለሁሉም ብሔረሰቦች የራስ ገዝነት መብት መስጠት የሚልን መፍትሔ ጨምሮ አምስት መፍትሔዎች ሲሆኑ፤ ተቀባይነት አግኝቶ በመንግሥት ተግባራዊ ሊደረግ ተጀምሮ የነበረው ሐሳብ ግን እንደ ኤርትራ ክፍለ አገር ሁሉ ለአፋርና ለሶማሊ ብሔረሰቦች ካላቸው ወጥ የባሕል፣ የሃይማኖትና የሥነ-ልቦና አንድነት አንፃር ራስ ገዝነት መብት መስጠት የሚል ነበር’’ ይላሉ። ‘’ነገር ግን’’ ይላሉ ዶ/ር ፍስሐ  ‘’ነገር ግን ኢሕአዴግ በሽግግር መንግሥቱ ወቅት የእኛን ጥናት ተግባራዊ አድርጎታል የሚል እምነት የለኝም፤ ጥናቱን ተግባራዊ አድርገውት ቢሆን ኑሮ ዛሬ ያሉት ችግሮች ይኖራሉ ብዬ አላሳብም’’ በማለት ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ።

አሁንም ድረስ በጥቅሉ ‘ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች’ እየተባለ የሚደጋገመው የዘውግ ማንነት የቃላቱ ትርጉም እንኳን ግልጽ መሆን ሳይችል በችግር ላይ ችግርን እየደረበ በመሔድ ላይ ይገኛል።

ያልለየለት ‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት›
በቅርቡ በሞት የተለዩን ኬኒያዊው ሊቅ አሊ ማዝሩኢ የአፍሪካ የዘውግ ግንኙነቶች እና ሥልጣኔ ላይ አተኩረው ለረጅም ዓመታት ጽፈዋል። በተለይም ዘውጌ ፖለቲካን በከበርቴ ርዕዮተ ዓለም አንፃር በመተንተን አዳዲስ ዕይታዎችን በማቅረብም ይታወቃሉ። ማዙርኢ የቀዝቃዛ ጦርነት ማብቂያ ማግስት በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1994 ‘Ethnicity in Bondage: Is Its Liberation Premature?’ ንግግራቸው ላይ ዘውግን (Ethinicity) በአንድ ጎራ አገረ-መንግሥትን (State) እና የምዕራቡ ዓለምን ሥልጣኔ (Western Civilization) ደግሞ በሌላ ጎራ በማስቀመጥ ተፎካካሪ እውነቶች መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ጠንካራ አገረ-መንግሥት ባለ ቁጥር የዘውግ ኃይላት እየተዳከሙ እንደሚሄዱም ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያን ሁኔታ በማዝሩኢ መነፅር ስንመለከተው የኢትዮጵያ አገረ-መንግሥት መጠናከር በውስጧ ላሉት የዘውግ ኃይላት መዳከም ምክንያት የሚሆን ሲሆን፤ የዘውግ ኃይላት መጠናከር ደግሞ በተቃራኒው ለኢትዮጵያ አገረ-መንግሥት መዳከም ምክንያት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ያደርሰናል።
በኢትዮጵያ እያደገ ከመጣው የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ አንዳንዶች መፍትሔው ‹ሰፊ የሆነ የማንነት ብሉኮ መስፋት ነው› በሚል ሐሳብ መነሻነት ‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን› (Ethiopian Nationalism) እንደመፍትሔ ሲያቀርቡ ይታያል። ‹የዚህ ዓይነት ሰፊ የማንነት ዓይነትም ነው አገሪቱን ከመበታተን የሚያድናት› የሚል መደምደሚያ ላይም ሲደርሱ ይስተዋላል። ነገር ግን ‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት› የተባለው ሐሳብ ገና ብዙ ያልተተነተነ ሐሳብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፊቱ ትልቅ ፈተናን ያዘለ ጉዳይ ነው።
አንቶኒ ስሚዝ የተባሉ በብሔርተኝነት ላይ ብዙ ሥራዎችን ያቀረቡ ጸሐፊ ‘National Identity’ ባሉት መጽሐፋቸው አንድ ብሔራዊ ማንነት ለመገንባት አምስት መሠረታዊ ነገሮችን ማሟላት ይኖርባቸዋል ይላሉ። እነዚህም አምስት መሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች (1) ታሪካዊ አንድ ድንበር፣ (2) የጋራ አፈ ታሪክና ታሪክ፣ (3) የጋራ ባሕል፣ (4) እኩል የሆነ መብትና ግዴታ እና (5) የጋራ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ናቸው።
እንግዲህ ‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት› የተባለውን ጥቅል ሐሳብ ከላይ በመዘዝናቸው አምስት መመዘኛዎች ስንመዝነው የሐሳቡ አቅራቢዎች ሐሳቡን በታሪካዊና መሬት ላይ ባለው እውነታ አስደግፈው የማቅረብ ከባድ ፈተና ከፊታቸው እናዳለባቸው እንረዳለን።
ሑሴን ሰለሞን እና ሳሊ ማቲውስ የተባሉ ተመራማሪዎች ‹Transforming Ethnic Conflict› በሚለው ‹Politics of Identity and Exclusion in Africa› በሚል ርዕስ የታተመ የጥናቶች መድብል ውስጥ በተካተተ መጣጥፋቸው “…ማንነት ፈፅሞ የማይለዋወጥ ነገር አይደለም፤ ይልቁንም ተለዋዋጭ እና ሊቀረፅ የሚችል ነው። ስለሆነም… ማንነት አንዴ ሊቀረፅ እና እንደገናም ተስተካክሎ እንዳንዲስ ሊቀረፅ ይችላል” በሚል ይደመድማሉ። በዚሁ ጥናታቸው ላይ ሁለቱ ምሁራን በዘውጎች መካከል ለሚነሱ ግጭቶች በመፍትሔነት ከሚያስቀምጧቸው አራት አማራጮች መካከል የጋራ ማንነት ግንባታ (Nation Building) አንዱ ነው። የጋራ ማንነት ግንባታ ዘውግ ላይ የቆመ ማንነት በመመሥረት ፈንታ የጋራ ድንበር እና ታሪክ ላይ አተኩሮ አዲስ ማንነት መፍጠርን የሚያካትት ነው።
የዚህ የጋራ ማንነት አቀንቃኝ የሆኑት ዩሱፍ ያሲን በቅርቡ ባሳተሙት ‹አሰባበሳቢ ማንነት፣ ባንድ ሃገር ልጅነት› ባሉት ዳጎስ ያለ መጽሐፋቸው የማንነት ጉዳይ እጅግ ውስብስብ መሆኑን ከተቀበሉ በኋላ፤ ኢትዮጵያዊያንን በአንድ የሚያኖር ማንነት ይኖር ዘንድ የሕገ-መንግሥታዊ አስተዳደር መኖርን፣ የአዳዲስ  አስተሳሳሪ ታሳቢዎችን ማፍለቅንና የወል ታሪክ አተረጓጎም መኖርን እንደ ዋነኛ ግብዓት አድርጎ በመያዝ ሰፋ ያለ ማንነት በመፍጠር በውስጡ ያሉትን ራሳቸውን የቻሉ ማንነቶች በአንድ ጣራ ስር ማስቀመጥ ይቻላል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ‹ቋንቋ የማንነት እናት ነው› ከሚል መነሻ ዘውግ ዘለል የአፍ መፍቻ ቋንቋ (trans-ethnic lingua franca) መኖርን የሰፊ ማንነት መሠረት አድርገው ሲወስዱ ይታያል።
የማንነት ጥያቄ ለኢትዮጵያ ፈተናና ተስፋን ይዞ ነው ከጥያቄዎች ሁሉ ቀድሞ የተሰለፈው። ሰዎች ልዩነቶቻቸውን ማጉላት መፈለጋቸው የራሱ መልካምና እና መጥፎ እውነቶች አሉት። ነገር ግን የማንነት ፖለቲካን መልካምነት ሰባኪ ከሆኑት ሊቃውንት አንዱ የሆኑት ሪቻርድ ፓርከር ሳይቀሩ እንደሚሉት፣ የማንነት ፖለቲካ አላግባብ መጠቀሚያ ሲሆን የነጻነት የራሷም ጠር ሊሆን ይችላል፡-  
When the construction and presentation of identities becomes a weapon of manipulation with which to stifle conflict—especially if taken to the extreme of claiming to create a “new man”—it becomes the deadly enemy of political freedom.

No comments:

Post a Comment

wanted officials