Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, June 8, 2016

ከእግዚአብሔር ይልቅ ባለስልጣንን የሚያከብሩት አባ ማትያስ

አባ ማትያስ ስልጣን ላይ የቆዩት ሶስት ዓመት ነው:: በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ ግን የሰሯቸው ሥራዎች አቅማቸውን( capacity) ያስገመተ ነበር:: በርካታ ስብሰባዎች ላይ የሚናገሩት ቋንቋ ለክብራቸው የማይመጥንና (disgraceful) የአዕምሯቸውን አቅም ( caliber) ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነበር:: የሚወስዷቸው ውሳኔዎችም ቤተ ክርስትያኗን ለከፋ ትችት ዳርጓታል::
ይህንን መሰል ጉዳዮችን ግምት ውስጥ በማስገባት ቅዱስ ሲኖዶስ ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚገባቸው አለበለዚያ ግን ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ተወያይቶ እሳቸውንም አሳውቋል:: እንደራሴው ባጭር ቃል የፓትርያርኩ ረዳት ናቸው:: የስራ ጫናውን ግምት ውስጥ በማስገባት ፓትርያርኩን በአግባቡ የሚያማክርና የሚያግዝ ነው::
በመሰረቱ መጽሓፉ እንደሚለው አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል:: ሁለትም ከመሆን ሶስት መሆን በጎ ነው:: አንድ ሰው አንድ ነው:: ከተቻለ አጋዥ ማግኘቱ አይከፋም ነበር:: ቅዱስ ሲኖዶስም ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር ለፓትርያርኩ እንደራሴ ይኖራቸው ዘንድ የተማጸነው::
እንደ ትውፊታችን የቤተ ክርስትያን የመጨረሻው ውሳኔ ሰጭ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው:: በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን ይህን የሲኖዶስ ውሳኔ ምዕመንም ሆነ ካህን እምቢ ማለት አይችልም- ውሳኔው የመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ:: ምንም የተሰብሰቡት ሰዎች ቢሆኑም( ጳጳሳቱና ሊቃነ ጳጳሳቱ) መሀከላቸው እግዚአብሔር አለ:: ጉባኤውንም የሚመራው መንፈስ ቅዱስ ነው::
ፓትርያርክ ማቲያስ ግን እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ የመንፈስ ቅዱስ አባቶቻቸውን ውሳኔና ልመና እምቢ ብለው ” ባለስልጣን ይጠራልኝ” አሉ:: አልፎ ተርፎም ” ልዩ ኃይል አለኝ” እያሉ እስከማስፈራራት ደረሱ:: በዚህም ምክንያት መንፈስ ቅዱስ የሚመራው ስብሰባ ተቋረጠ:: የእግዚአብሄርን ጉዳይ ለመወሰን ቄሳር እንዲጠራ ሆነ:: ከወንድሞቻቸው ሊቃነ ጳጳሳት ይልቅ ” ልዩ ኃይላቸውን ” ተማመኑ:: እጅግ የሚደንቅ ነገር ነው:: የሃይማኖት ውሳኔን ለማስወሰን ባለስልጣን ይጠራልኝ የሚል ቃል ከአንድ ፓትርያርክ ሲሰማ አባ ማቲያስ የመጀመርያው ሳይሆኑ አይቀሩም::
የአምላክ ሥራ ሆነና የመንግስት ተወካዩ ” እንደራሴ መሾሙ” ጥሩ እንደሆነ ገለጹ:: ፓትርያርኩም ውሳኔውን ተቀበሉ:: ያሁሉ ሊቃነ ጳጳሳት ይህን ውሳኔ ይቀበሉ ዘንድ ቢለምኗቸው እምቢ ብለው አንድ የመንግስት ባለስልጣን ” ተቀበሉ” ሲላቸው እሺ በጄ አሉ:: በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ሲኖዶስ ሲማጸናቸው አሻፈረኝ ያሉት ፓትርያርክ : በአንድ ባለስልጣን ንግግር ውሳኔውን ተቀበሉ:: አባ ማቲያስ ከእግዚአብሔርን ይልቅ የሚፈሩት ባለስልጣንን ነው:: ነገ እግዚብሐርን ፍሩ ብለው ያስተምሩ ይሆን? ባለመድሀኒት ራስህ አድን!!!
እኔ ሳውቅ ለዳኛ እምቢ ያለ ሰው የሚዳኘው በካህን ነበር:: አልታረቅ ያለ ጸበኛ ልቡ የሚሰበረው ካህን ሲገስጸው ነበር:: አሁን ግን አባ ማቲያስ ሐዲስ ትምህርት እያስተማሩ ነው:: ለካህን እምቢ ብለው ለምዕመን እሺ ይላሉ:: ስልጣነ ክህነትን ረግጠው ሄደው በጥቁር ራስ ይዳኛሉ:: የክህነትና የካህናት ምስጢር በምዕመን ይዳኛል:: ክብረ ካህንን እዚህ ድረስ አዋረዱት::
አይ ግዜ?
“ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ
ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡ”

No comments:

Post a Comment

wanted officials