Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, May 28, 2014

ነዋሪዎች ግንቦት 20 ዳግም በኢትዮጵያ ሲከበር ማየት እንደማይሹ በምሬት ገለጹ

ነዋሪዎች ግንቦት 20 ዳግም በኢትዮጵያ ሲከበር ማየት እንደማይሹ በምሬት ገለጹ

ግንቦት ፳(ሃያ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-
ኢሳት ያነጋገራቸው አንዳንድ ዜጎች ” የግንቦት20ን በአል ተገደው እንዲያከብሩ መደረጋቸውን ሲገልጹ” ፣ ሌሎች ደግሞ  በአሉ ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ተከብሮ ማየት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ የግንቦት 20 ድል የመግብ ዋስትናችንን እንድናረጋግጥ እረድቶናል ያሉ ሲሆን፣ አገሪቱ በ1983 ዓም ታመርት ከነበረው 50 ሚሊዮን ኩንታል የግብርና ምርት ወደ 250 ሚሊዮን ኩንታል መሸጋገሩዋን ገልጸዋል። አቶ ሃይለማርያም ይህን ይበሉ እንጅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም በያዝነው አመት ከ6 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
በአሉ በሚከበርበት በአዲስ አበባ ስታዲየም የተገኙት አቶ ሃይለማርያም ፣ ከግንቦት20 በሁዋላ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሚሊየነሮችና ቢሊየነሮች መፈጠራቸውንም ገልጸዋል።  እነዚህ ሚሊየነሮች የየትኛው ብሄር እና የየትኛው ስርዓት ደጋፊ መሆናቸውን አልተናገሩም።
የኢህአዴግ ባለስልጣናት በግንቦት20 በርካታ ድሎች የተመዘገቡበት እንደሆነ ቢገልጹም ዜጎችና የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች ግን የግንቦት 20ን ድል አጣጥለውታል።
አንዲት እናት ኢህአዴግ በመጪው ምርጫ ካሸነፈና በሚቀጥለው አመት ግንቦት20ን የሚያከብሩ  ከሆነ እራሴን አጠፋለሁ ሲሉ ለኢሳት ገልጸዋል። በሀረር ከተማ የሚኖር ሌላ ወጣት ደግሞ ህዝቡ ሳይፈልግ እየተገደደ ሰልፍ እንዲወጣ መደረጉን ተናግሯል።
መንግስት በአሉን ለማክበር ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ማፍሰሱን መረጃዎች ያሳያሉ።
በአዲስ አበባ ብቻ በአንድ ቀበሌ ብቻ ለሻማ ፣ ጧፍ፣ ባንዲራ መስቀያ እንጨት፣ መፈክሮች፣ ለለስላሳ መጠጦችና እሽግ ውሃ ፣ ኩኪስና ቆሎ ፣ለትራንስፖርት እና ለመሳሰሉት ወጪዎች እስከ 5 ሺ ብር የሚደርስ ገንዘብ ሲወጣ፣ በክፈለ ከተማ ደረጃ ለሚደረጉ ስብሰባዎች ደግሞ ለአዳራሽ ኪራይ ከሚወጣው እስከ 15 ሺ ብር ከሚደርስ ገንዘብ ጀምሮ፣ ለኬክ፣ ለውሃ፣ ሻሂና ቡና አቅርቦቶች የሚወጡት ወጪዎች እጅግ ከፍተኛ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
በአገር አቀፍ ደረጃ ለበአሉ ወጪ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚወጣ ግምቶች የሰፈሩ ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲ የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን በጅጅጋ ለማክበር ካወጣው ወጪ ጋር ሲተያይ የዘንድሮው የግንቦት 20 በአል በብዙ እጥፍ ይበልጣል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials