በአዲስ አበባ ከሚፈርሱ ቤቶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እየተከሰተ ነው
ግንቦት ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-
ሰሞኑን ተጠናክሮ በቀጠለው የቤት ፈረሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በድንገት ቤቶቻቸው እየፈረሱባቸው ንብረቶቻቸውን እየተዘረፉ ሜዳ ላይ እየወደቁ ሲሆን፣ ትናንት ሌሊት በድንኳን ተጠልለው ከነበሩት ነዋሪዎች መካከል የ4 ልጆች አባት የሆኑ ግለሰብ በጅብ ተበልተው ዛሬ ከፊል አካላቸው በፖሊሶች መነሳቱን የአካባቢው ሰዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ፖሊሶች መረጃው እንዳይወጣ አካባቢውን ተቆጣጥረው ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ ሲያደርጉ የዋሉ ሲሆን፣ ቀሪው አስከሬን ከተነሳ በሁዋላ ደግሞ በማይክራፎን እየዞሩ በላስቲክ ድንኳን የተጠጉትን ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ እያዘዙዋቸው ነው። ብዙዎቹ ልጆቻቸውን የት እንደሚያስጠጉዋቸው ጨንቋቸው ለኢሳት በመደውል የድረሱልን ጥሪ አቅርበዋል
የሟቹን ግልሰብ ስም ለማግኘት ጥረት ብናደርግም እስካሁን አልተሰካላንም።ፖሊስ አስፈላጊውን መረጃ እንዲሰጠን ተደጋጋሚ ሙከራ ብናድርግም አልተሰካላንም።
ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች ለኢሳት በጻፉት የጋራ ደብዳቤ ደግሞ ፣ እንደ አዲስ ሰሞኑን የሚፈርሱ ቤቶች በዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተስፋ በተደረገ ፈንድ ለሚገነባው የኦሎምፒክ መንደር ፕሮጀክት ቦታ ለማዘጋጀት ሲባል በመሆኑ ኦሎምፒክ ኮሚቴው የህዝቡን ስቃይ አይቶ፣ ድጋፉን እንዲያዘገይ ጠይቀዋል።
ነዋሪዎቹ በደብዳቤያቸው “የኢትዮጵያ መንግስትና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 2 ሚሊዩን የኢትዮጵያ ብር እንደሚሰጣቸው” ገልጸዋል።
“በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሦስት ቀናት ውስጥ መኖሪያቸውን ነቅለው ከአካባቢው እንዲወጡ ጥብቅ ትዕዛዝ የተላለፈው ከዚህ ፕሮጅክት ጋር በተያያዘ መሆኑን ነዋሪዎች በደብዳቤያቸው ጠቁመዋል።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ” የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ከዚህ በፊት ቤታቸውን ነቅለው አካባቢውን እንዲለቁ በተደጋጋሚ እንደ ተገለጸላቸው የሚጠቁም ቢሆንም ፣ ከዚህ በፊት ቤት ግን አንድም ቀን ነዋሪዎቹ ነቅለው እንዲነሡ እንዳልተነገራቸውና ደብዳቤም ተጽፎላቸው እንደማያውቅ” ጠቅሰዋል፡፡
በሦስት ቀናት ውስጥ ቤቶች እንዲፈርሱ የታዘዘበት ምክንያት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት ሁሌም እንደ ሚያደርጉት የኗሪዎችን ቤት ነቅለው በመወሰድ እንጨቶችን፣ ቆርቆሮዎችን፣ በሮችንና መስኮቶችን በወረዳ አሰተዳደር ቅጥር ግቢ እያጫረቱ በመሸጥ ቤት አፍራሾቹና አመራሩ እንዲካፈሉት ለማድረግ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
“የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከክፈለከተማው አስተዳደር የመጣ ትእዛዝ ነው ምንም ማድረግ አልችልም የሚል መልስ ለአቤቱታ አቅራቢዎች ሲሰጡ፣ የክፍለ ከተማው አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ደግሞ አቤቱታ አቅራቢዎች ከቢሯቸው እንዲባረሩ ማስደረጋቸውን ነዋሪዎች በጽፋቸው አስፍረዋል።
ኗሪዎች በንብረታቸው ላይ ሊካሄድ የታቀደውን ዝርፍያ በመፍራት የቤቶቻቸውን ጣራና በር አንስተው ዘመድ ያለው ከዘመድ የሌላቸው ደግሞ ላስትክ ዘርግተው በተጠለሉበት ቅዳሜና እሁድ ባለማቋረጥ የዘነበውን ዝናብ በላያቸው ማሳለፋቸውን፣ አራስ እናቶች እና አዲስ የተወለዱ ሕጻናት፣ ነፍሰጡር ሴቶች በበሽታ ላይ መውደቃቸውንም አመልከተዋል።
የኢህአደግ መንግስት በሕይወት እያለን ገድሎን በድኖቻችንን በሜዳ ላይ በትኗል የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ በካሬ እስከ ሠላሳ ሺ ብር ድረስ የሚያጫርቱትን የአዲስ አበባ መሬት 18 ብር ብቻ ተቀብለው እንዲለቁ የታዘዙ በዙሪያችን ያሉ የኦሮሚያ አርሶ አደሮች እያለቀሱ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ በደብዳቤያቸው መጨረሻ ” የኦለምፒክ ፌዴሬሽን በዓላማውና ባለው እሴት ሰብዓዊ መብትን ከሚጋፋ ተግባር ጋር የማይተባበር ተቋም ቢሆንም በጭካኔ ከሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት መተባባሩን ኮንነዋል።
” በኢትዮጵያውያን ላይ በኦሎምፒክ ኮሚቴ ስም እያረፈ ያለውን ሊረሳ የማይችል ጠባሳ በተመለከተ በማስገንዘብ በእኛ ላይ ለሚፈጸመው ግፍ ከዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የሚያገኘውን ፈንድ እንዲቆምላቸው” ጠይቀዋል።
ከአለማቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎችም ጉዳዩን እንዲያደርሱላቸው ተማጽነዋል።
ደብዳቤውን የጻፉትን ሰዎች በስልክ አነጋግረን እንደተረዳነው፣ ደብዳቤያቸውን ከጻፉ 2 ሳምንታት ያለፈው ሲሆን፣ መንግስት የሚወሰድውን እርምጃ በመፍራት እስካሁን ይፋ ለማድረግ ሳይፈልጉ ቀርተዋል።
No comments:
Post a Comment