Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, May 24, 2014

በፒያሳ ወርቅ ቤቶች ኮርኒስ ውስጥ ለ3 ቀን ያሸመቀው ወጣት ተያዘ

በፒያሳ ወርቅ ቤቶች ኮርኒስ ውስጥ ለ3 ቀን ያሸመቀው ወጣት ተያዘ

በፒያሳ ወርቅ ቤቶች ኮርኒስ ውስጥ ለ3 ቀን ያሸመቀው ወጣት ተያዘዘ
በረሃብ ደካክሞ ለ5ቀን ራስ ደስታ ሆስፒታል ህክምና ተደርጎለታል
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ፒያሳ እምብርት ላይ በሚገኘው ዝነኛው ላሊበላ ወርቅ ቤት ውስጥ ለብዙዎች ትንግርት የሆነ ነገር ተከስቷል፡፡ ያውም በጠራራ ፀሃይ፡፡ ላሊበላ ወርቅ ቤት፤ በአካባቢው ከሚገኙ ሌሎች ወርቅ ቤቶች ለየት የሚያደርገው ለምሳ ከ7-9 ሰዓት መዘጋቱ ነው የሚሉት የወርቅ ቤቱ ባለቤት አቶ ኢዛና ካሣዬ፤ የዚያን ዕለት ግን ገበያ በመብዛቱ ለምሳ ሳይዘጋ እንደቀረ ይናገራሉ፡፡
የላሊበላ ወርቅ ቤት ትንግርት የተጀመረው ከጎኑ በሚገኘው ኢየሩሳሌም ወርቅ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ኮርኒስ ውስጥ የመንደፋደፍ ድምፅ እንደሰሙ የሚናገሩት የኢየሩሳሌም ወርቅ ቤት ሰራተኞች፤ ለጊዜው ቢደናገሩም “እርግብ ነው” በሚል ተስማምተው ወደ ስራቸው መግባታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ሆኖም ድምፁ እየጨመረ በመምጣቱ ጥርጣሬ ይገባቸውና አንደኛው ሰራተኛ ክፍት በሆነው ኮርኒስ በኩል ባትሪ አብርቶ ተጠግቶ ይመለከታል፡፡
ኮርኒስ ውስጥ የሚንደፋደፈው እርግብ ሳይሆን ሰው መሆኑን ያረጋገጠው የወርቅ ቤቱ ሰራተኛ፤ “ሌባ… ሌባ” እያለ ሲጮህ ያልደነገጠ የለም፡፡ ኮርኒሱ ውስጥ ያሸመቀውን ወጣት ጨምሮ ሁሉም ድንብርብሩ ወጣ፡፡ ለማምለጥ የሞከረውም ወጣት ሲንደፋደፍ ከጎኑ ያለው የላሊበላ ወርቅ ቤት ኮርኒሱ ተቀዶ መሬት ሊፈጠፈጥ ሲል አንዱ የእንጨት ምሰሶ ደግፎት ይተርፋል፡፡  በዚህ ዱብዕዳ ወርቅ በመግዛት ላይ የነበሩ ደንበኞችና የወርቅ ቤቱ ሠራተኞች መደናገጣቸው አልቀረም፡፡ በዚህ ግርግር ወጣቱ ተመልሶ ወደ ኮርኒሱ  ውስጥ ይሸሻል፡፡ ይሄኔ ሁሉም ባለወርቅ ቤት በየራሱ ኮርኒስ ውስጥ ባትሪና ሻማ ይዞ በመግባት ወጣቱን ተጠርጣሪውን ማደን ጀመረ ይላል፤ የቅዱስ የብር ጌጣጌጥ መሸጫ ቤት ሠራተኛ ብርሃኑ አበበ፡፡ ተርታውን ያሉት የወርቅ መሸጫ መደብሮች የጥንት ቤቶች ስለሆኑ በኮርኒሳቸው ውስጥ ለውስጥ እንደሚገናኙ የነገሩን ሠራተኞቹ፤ ማታ ማታ ቤቱን ከመዝጋታቸው በፊት ወርቅና ብሮቹን ካዝና ውስጥ ከተው እንደሚቆልፉባቸው ገልፀዋል፡፡
በየግል ተጀምሮ የነበረው ወጣቱን የማደን ዘመቻ ከደቂቃዎች በኋላ በፖሊስ ሃይል ተጠናክሮ ቢቀጥልም ወጣቱ እምጥ ይግባ ስምጥ ሊታወቅ አልቻለም – ይላሉ አቶ ኢዛና፡፡ ከዚያም ጣራው አናት ላይ ወጥተው አሰሳውን ቀጠሉ፡፡ ወጣቱን ባያገኙትም ስለእሱ ድርጊቶች የሚጠቁሙ ፍንጮችን ለማግኘት እንደቻሉ የሚናገሩት አቶ ኢዛና፤ አንድ ቦታ ላይ ጣራው መቀደዱን ማየታቸውን፤ እዚያው አካባቢም ጣራው የተቀደደበት መቀስ መገኘቱን ገልፀዋል፡፡ወዲያው የተቀደደውን ቆርቆሮ በባለሙያ እንዳስደፈኑ ጠቁመው፤ አሰሳው ግን ያለውጤት መቋጨቱን ተናግረዋል፡፡
በነጋታው አርብ ጠዋት ደግሞ ቅዱስ የብር ጌጣጌጥ መሸጫ መደብር ውስጥ ሌላ ፍንጭ ተገኘ፡፡ በሩን ለመክፈት ሲሞክር የበሩ ቁልፍ (ጋን) እንዳስቸገረው የሚያስታውሰው ብርሃኑ፤ የቤቱን ባለቤት ጠርቶ አብረው ከፍተው መግባታቸውን ይገልፃል፡፡ ውስጡን ሲቃኙም አንዳንድ ነገሮች ተመሰቃቅለው ያገኛሉ፡፡ ወዲያው ፖሊስ ይጠሩና ሌላ የፍለጋ ዘመቻ ይጀመራል፡፡ ሆኖም ተፈላጊው አልተገኘም፡፡
ቅዳሜ ጠዋትም ብርሃኑ ከሱቁ ባለቤት ጋር ነበር በሩን የከፈትነው፡፡ የብር ጌጦቹን የሚደረድርበትን የመዝጊያ ብረት ሸርተት ሲያደርግ ነው ፈፅሞ ካልጠበቀው ነገር ጋር የተፋጠጠው፡፡ ሁለት ቀን መከራቸውን ያበላቸው ወጣት፤ ትልቅ የብር መስቀል በእጁ ይዞ መስተዋቱ ጋ ተለጥፎ ቆሟል፡፡ “ፊት ለፊት ቢያገኘኝ ግንባሬን ብሎኝ ወደ ውጭ ለመፈትለክ አስቦ እንደነበር ያስታውቅበታል” ያለው ብርሃኑ፤ በመስተዋት ውስጥና ውጭ ሆነን እንፋጠጣለን ብሎ የጠበቀ አይመስልም ብሏል፡፡ በሩን ከፍተው ሲገቡ ወደ ውስጥ ሊያመልጥ ቢሞክርም ወዴትም ሳይደርስ እንደያዙት የሚናገረው ብርሃኑ፤ ወዲያው  ተዝለፍልፎ መውደቁንም ገልጿል፡፡ ሰውነቱ ደካክሞና አቅም ክዶት እንደነበር በመግለፅም የምግብ እጥረት ሳያጋጥመው እንዳልቀረ ግምቱን ገልጿል፡፡
ወጣቱ ኪሱ ሲፈተሽ የብር ጌጦችና ጥቂት የወርቅ ቀለበቶች የተገኙበት ሲሆን ጀርባው ላይ ባዘለው ቦርሳ ውስጥ ደግሞ ውሃ፣ ቆሎ፣ መቀስ፣ ባትሪ እና የስለት መሳሪያዎች እንደተገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ተጠርጣሪው ወጣት ሰውነቱ በመጎዳቱና አቅም በማጣቱ፣ ራስ ደስታ ሆስፒታል ገብቶ ለአምስት ቀናት የህክምና እርዳታ የተደረገለት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በአራዳ ክ/ከተማ ፒያሳ ፖሊስ ጣቢያ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ፖሊስ ጠቁሟል፡፡ ፒያሳ የሚገኙ አብዛኞቹ ወርቅ ቤቶች በመደብራቸው ውስጥ እያንዳንዳቸው ከ2 ሚ.ብር ያላነሰ የወርቅና ብር ጌጣጌጦች እንዳላቸው ምንጮች ሲገልፁ፤ በዚህ ዓመት ብቻ በእነዚህ ወርቅ ቤቶች ከአራት ጊዜ በላይ የዝርፊያ ሙከራ እንደተፈፀመባቸው ፖሊስ ገልጿል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials