በጣሊያን ራሳቸውን እንዳጠፉ የተነገረላቸው ኢትዮጵያዊው ዲፕሎማት አሟሟት መንስኤ በውል አልታወቀም
ግንቦት ፲፬(አስራ አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከትናንት በስቲያ ከመደበኛ የስራ ሰአት ውጭ ከጧቱ 1 ሰአት ተኩል ላይ ወደ ቢሮአቸው በመግባት ራሳቸውን ከ2ኛ ፎቅ ወርውረው የገደሉት የ62 አመቱ ዲፕሎማት አቶ ፍሰሃ ተስፉ ስለ አሟሟታቸው መንስኤ መንግስት እስካሁን ይፋዊ መግለጫ አልሰጠም።
ክሮናካ ዲ ሮማ የተባለው የጣሊያን ጋዜጣ ዛሬ ይዞት በወጣው ሰፊ ዘገባ ዲፕሎማቱ ከመሞታቸው ከሁለት ቀናት በፊት ከስራ ተነስተው ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ተነግሮዋቸው እንደነበር አንዳንድ ጓደኞቻቸውን ጠቅሶ ዘግቧል። ሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው ግን ዲፕሎማቱ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ስለመታዘዙ እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ጋዜጣው እንደዘገበው ዲፐሎማቱ ራሱን ያጥፋ ወይም ሌላ ሰው ይግደለው እንደማይታወቅ ገልጾ፣ ራሱን ካጠፋ ግን አንድ መልእክት ለማስተላለፍ አስቦ ያደረገው ሊሆን እንደሚችል የፖሊስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በዲፕሎማቱ ቢሮ ውስጥ ምንም አይነት ማስታወሻ አለመገኘቱን፣ የተዘበራረቀ ነገር አለመኖሩንም የገለጸው ጋዜጣው፣ የረጅም ጊዜ ዝግጅት የተደረገበት ነበር ብሎ ለመናገር እንደማይቻልም አትቷል።
ፖሊስ ኢምባሲውን በመዝጋት ካለፉት 2 ቀናት ጀምሮ ምርመራ በሰራተኞች ላይ እያደረገ ይገኛል።
ዲፕሎማቱን ያገኙት የኢምባሲው ሰራተኞች ሲሆኑ ከሞተ ከአንድ ሰአት በሁዋላ አምቡላንስ በቦታው ቢደርስም የዲፕሎማቱን ህይወት ለማትረፍ እንዳልተቻለ ታውቋል።
አንዳንድ ጣሊያን ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግለሰቡ ራሱን አጥፍቷል ብለው እንደማያምኑ እየተናገሩ ነው።
አቶ ፍስሃ ወደ ኢጣሊያ ከመዛወራቸው በፊት በአውሮፓ ህብረት ዴስክ ኦፊሰር ሆነው ከሰሩ በሁዋላ፣ የአለማቀፍ ተቋማት ጊዜያዊ ዳይሬክተር እንዲሁም የዲያስፖራ ክፍል ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው ሰርተዋል።
አቶ ፍስሃ የህወሃት አባል መሆናቸውን አንዳንድ ወገኖች ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment