Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, May 28, 2014

ግብፃዊው ጋዜጠኛ ከደኅንነት ሥጋት ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ተባረረ


ግብፃዊው የመካከለኛው ምሥራቅ ዜና አገልግሎት ድርጅት (MENA) የአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበረው ጋዜጠኛ ሀምዲ አል አናኒ፣ ከአገር ደኅንነት ሥጋት ጋር በተያያዘ ምክንያት ከኢትዮጵያ ተባረረ፡፡

የጋዜጠኛውን መባረር የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ግንኙነት አካማሪ አቶ ጌታቸው ረዳ አረጋግጠዋል፡፡ ምክንያቱን በተመለከተም ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን፣ መንግሥት ብዙ ጊዜ በውጭ አገር ዜጎች ላይ ከአገር የማባረር ዕርምጃ የሚወስደው የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ሲኖረው እንደሆነ ጠቅሰው፣ ‹‹አንድን ሰው ጠላሁት ብለህ ከአገር አታባርረውም፤›› በማለት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ 

በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የግብፅ ኤምባሲ የሕዝብ ግንኙነት አታሼ ሚስተር ሙስጠፋ አህመዳይ፣ ‹‹በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ማብራሪያ ባለማግኘታችን ማብራሪያ እንዲሰጠን ጠይቀናል፤›› በማለት አስታውቀው፣ ‹‹መንግሥት አስፈላጊውን የምርመራ ሒደት አጠናቆ ማብራሪያ እንደሚሰጠንም እንጠብቃለን፤›› ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ የተባረሩት ጋዜጠኛ ሀምዲ አል አናኒ አዲስ አበባ የሚገኘውን የመካከለኛው ምሥራቅ ዜና አገልግሎት ድርጅት ዳይሬክተር ሆነው የመሩት ከአንድ ዓመት ላነሰ ጊዜ እንደሆነም ሚስተር ሙስጠፋ ገልጸዋል፡፡

የጋዜጠኛው ከአገር መባረር ተከትሎ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ባድር አብዱላሪ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የጋዜጠኛው መባረርን ለምን ቀድሞ እንዳላሳወቀን ማብራርያ እንጠይቃለን፤›› ያሉ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የግብፅ ኤምባሲም ጥያቄውን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስገባቱን አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረች ወዲህ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የሻከረ ሲሆን፣ ግብፅ የግድቡን እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ ከመጠየቅ ባለፈ ኢትዮጵያን የማተራመስ ዕቅድ ነድፋ ለመንቀሳቀስ የሚቻልበትን ሁኔታ የግብፅ ፖለቲከኞች ሲወያዩ የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል ከወራት በፊት አፈትልኮ መውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡

ምንም እንኳን በግብፅ መንግሥት በኩል እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያ ግን የግድቡ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በሰፊው እየሠራች ትገኛለች፡፡

የመካለኛው ምሥራቅ ዜና አገልግሎት ድርጅት በግብፅ መንግሥት ሥር የሚተዳደር የመገናኛ ብዙኃን ሲሆን፣ የተመሠረውም እ.ኤ.አ. በ1955 ነው፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials