Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, May 26, 2014

ሕዝቡ አማራጭ ይፈልጋል!

ሕዝቡ አማራጭ ይፈልጋል!

በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በተሟላ ሁኔታ ይሰፍን ዘንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው፡፡
በዘመናዊው ዓለም የውክልና ዲሞክራሲ ያለፓርቲዎች ህልውና አይታሰብም፡፡ ለዚህም ሲባል ነው የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሥርተው ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ አማራጮችን እንዲያመጡ የሚፈለገው፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 23 ዓመታት ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ተመሥርተዋል፡፡ ፓርቲዎቹ እንደሚያቀነቅኑት ርዕዮተ ዓለም ከሞላ ጐደል ዓላማቸውን ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል፡፡ በአገራችን የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በተለይ ገዥውን ፓርቲ የሚቃወሙት በተለያዩ ጊዜያት በተናጠል፣ በግንባር፣ በቅንጅትና በውህደት ታይተዋል፡፡
ምርጫዎች በሚቃረቡበት ወቅት በተወሰኑ ወይም ለዓመታት በታወቁ ጉዳዮች ላይ ከገዥው ፓርቲ ጋር ሲፋጩ ዘልቀዋል፡፡ በተለይ የመሬት፣ የፌዴራሊዝምና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዋነኛ መነጋገሪያ ሲሆኑ፣ በእነዚህ ላይ በመመሥረት የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለዓመታት ሳያግባቡባቸው ወይም ምንም ዓይነት ውጤት ሳይገኙባቸው የዘለቁት እነዚህ ጉዳዮች ባለፉት አራት ምርጫዎች የተስተዋሉ ናቸው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ ዋነኛ ጭብጦች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝቡንና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን የሚያገናኙ መሣሪያዎች መሆናቸው ነው፡፡ በዚህም መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች አራት መሠረታዊ ጉዳዮችን ያከናውናሉ፡፡
የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን የመቀመር ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ ሊታፍ የማይገባው ዋነኛው ኃላፊነታቸው ነው፡፡ በዚህ የፖሊሲና የፕሮግራም ቅመራ አማካይነት በፖለቲካው ገበያ ውስጥ አማራጮችን ይዘው ይመጣሉ፡፡ ይህ ማለት ለፖሊሲና ለፕሮግራም አፈጻጸም ዕጩዎችን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን የተሻሉ ሐሳቦችን ያፈልቃሉ፡፡ በዚህ ሒደት የመንግሥት ሥልጣንን ሲረከቡ አገር ለመምራት ብቁ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች የዘወትር ተግባር የሕዝቡን ፍላጐቶች እግር በእግር እየተከሉ ማወቅና የድርጊት መርሐ ግብራቸው ግብዓት ማድረግ ነው፡፡ የሕዝብ ፍላጐቶች ከመበርከታቸው በላይ የሚጣረሱ ጭምር ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰፋ ባሉ ውይይቶችና ግምገማዎች ቅርፅ ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቅርፅ የያዙትን የሕዝብ ፍላጐቶች የፖሊሲ አማራጭ አድርገው ይይዙዋቸዋል፡፡ ይህንንም በማድረጋቸው ዲሞክራቲክ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችለው የፖለቲካ ሒደት ባለድርሻ ይሆናሉ፡፡
ሦስተኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ደረጃ ላይ ሆነው አገርን እንደሚመራ አካል ለመንግሥት አመራርነትና ለፍትሕ አካሉ የሚሆኑ ብቁ ሰዎችን ማሠልጠንና ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር በዚህ ደረጃ የሚመጥኑ ሰዎችን ማቅረብ እንደማይችሉ መተቸታቸው ነው፡፡ የመንግሥት አመራርን በፖለቲካ ሰዎች ብቻ ለመሙላት የሚደረገው አሰልቺ ተግባር ሰዎችን ከታች ጀምሮ ኮትኩቶ አለማብቃት መሆኑ ዋነኛው ችግር በመሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኃላፊነት ስሜት ለዚህ ተግባር ትልቅ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡
አራተኛውና የመጨረሻው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባር የመንግሥት አሠራርን መከታተል ወይም መቆጣጠር ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ቢይዙም ወይም ተቃዋሚ ፓርቲ ቢሆኑም የመንግሥትን አሠራር በቅጡ ማወቅ አለባቸው፡፡ የመንግሥት አሠራርን በሚገባ ማወቅ አገርን ለመምራት ወይም ሥልጣን ለመያዝ ከሚንቀሳቀስ የትኛውም ፓርቲ የሚጠበቅ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ሥልጠናዎችና ተግባራዊ ልምምዶች ራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡
ከላይ እንደ ምሳሌ ካስቀመጥናቸው እውነታዎች አንፃር በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ስንገመግም የምናየው ተቃራኒውን ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብቃትና በተዓማኒነት እነዚህን ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችን ሲጠቀሙባቸው አይታዩም፡፡ አንዳንዶቹ ደካማ ከመሆናቸው የተነሳ የሚንጠላጠሉት በግለሰብ አመራር ላይ ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጊዜያዊና ስሜት ኮርኳሪ ድርጊቶች ካልተላቀቁና ከሕዝቡ ጋር ያላቸውን ትስስር በሚገባ ካልጠበቁ፣ ከመራጩ ሕዝብ ማግኘት የሚገባቸው ትኩረት የትም ባክኖ ይቀራል፡፡
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በተደጋጋሚ የሚጠየቀው የፖለቲካ አማራጭ ጉዳይ አሁንም መልስ እያገኘ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን የቱንም ያህል የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ አስጨናቂ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሠለጠነና በሰላማዊ መንገድ በመታገል አስፈላጊውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የግድ ይላቸዋል፡፡ ፖለቲካ በከፍተኛ ጫና፣ ውጣ ውረድና በዓላማ ፅናት የሚከናወን እንደመሆኑ መጠን ለሕዝብ አማራጭ ይዞ መምጣት የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ግዴታ ነው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ከገዥው ፓርቲ ጋር ካላቸው እንካ ሰላንቲያ በተጨማሪ በመካላቸው ያለውን ልዩነት ለማስታረቅ የሚጐድላቸው ተነሳሽነት እንዳለ ሆኖ፣ በሰከነ መንገድ ከሕዝቡ ጋር የሚያደርጉት ግንኙነትም መፈተሽ አለበት፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉዋቸውን የፖሊሲ አማራጮች በተጨባጭ መረጃዎች አስተንትነው ማቅረብ ካልቻሉ ፈተናው የበለጠ ከባድ ይሆናል፡፡ በአማራጭ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ያልተቃኘ እንደወረደ የሚቀርብ የፖለቲካ ሙሾ ማንንም የትም አያደርስም፡፡
ባለፉት አራት ብሔራዊ ምርጫዎች መራጩ ሕዝብ ከሚገባው በላይ የሰማቸው የክርክር አጀንዳዎች ገታ ተደርገው ለመጪው ምርጫ ዘመቻ የሚሆኑ አዳዲስ ሐሳቦች ይቅረቡ፡፡ የሕዝቡን የልብ ትርታ በማዳመጥ በርካታ አገራዊ ጉዳዮች በጥልቅ ጥናትና ትንተና ታጅበው መቅረብ አለባቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ በልማታዊ መንግሥት ፖሊሲው አስፈጽማቸዋለሁ የሚላቸውን ጉዳዮች በይፋ ለሕዝብ አሳውቆ በርቀት እየተጓዘ ነው፡፡ ለሕዝቡ የተሻለ ጠቃሚ አማራጭ ሐሳቦች አሉን የሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በዚህ ደረጃ ላይ ሊገኙ ይገባል፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ያስፈልጋል ስንል ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጉናል ማለት ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትን አራት ወሳኝ ግብዓቶችን በሚገባ ሊያስቡባቸው ይገባል፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ቢሆንም፣ እነዚህ ፓርቲዎች ግን በከፍተኛ ሁኔታ ራሳቸውን ማጠናከር አለባቸው፡፡ የሕዝብን ፍላጐት ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር አሳማኝ በሆነ መንገድ ቁርኝት መፍጠር አለባቸው፡፡ የፖሊሲ አማራጮችን በደረጀ ሁኔታ የማቅረብ ብቃትና ባህል ሊኖራቸው የግድ ይላል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲ መዋቅር በበለጠ የመንግሥትን መዋቅርና አሠራር ሊያውቁ ይገባል፡፡ አማራጭ ሐሳቦች በውስጣቸው በማንሸራሸር ዲሞክራሲን በሚገባ መለማመድ አለባቸው፡፡ የፖለቲካው ከባቢ የቱንም ያህል ባይመች እነሱ ራሳቸው የዲሞክራሲያዊ ሒደቱ ባለድርሻ አካል ሊሆኑ የግድ ነው፡፡ በተውረገረገና ግራ በሚያጋባ አጀንዳ ላይ ተለጥፎ መኖር ፋይዳ የለውም፡፡ ሕዝቡ አማራጭ ይፈልጋልና!

No comments:

Post a Comment

wanted officials