Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, May 26, 2014

ኢትዮጵያን‬ ከነበልባል እሳት ውስጥ ለመጨመር የሚተጋ ሃይል እጁን ይሰብስብ

ኢትዮጵያን‬ ከነበልባል እሳት ውስጥ ለመጨመር የሚተጋ ሃይል እጁን ይሰብስብ

ከመፎከርም ከማውራትም በተግባር ምን እናድርግ? ማለት ተመራጭ ነው! ኢትዮጵያን ከነበልባል እሳት ውስጥ ለመጨመር የሚተጋ ሃይል እጁን ይሰብስብImage   ደጋግመን ብናወራ፤ ደጋግመን ብንቋሰል፤ ደጋግመን እዬዬ ብንል ለሀገራችን ጠብ የሚል ነገር የለም! ብንገማገም፣ ስብሰባ ብናበዛ ለሀገራችን ጠብ የሚል ነገር የለም! የሚያስፈልገን ልብ ነው! የሚያስፈልገን ቆራጥነት ነው! በቆራጥነት ጉዳያችንን መወያየትና ልባም መፍትሄ መስጠት ነው፡፡ “በላብ ያልፍልሃል! ተሸፋፍነህ ተኛ!” እንደሚባለው ያበሻ መድሃኒት ላቦት ብቻ መፍትሄ አይሆነንም! አውርተን አውርተን እፎይ ብሎ መተኛት ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም መፍትሄ አይሆነንም!
እድሜ ለቴክኖሎጂ የማህበርውድ ህረገጾች በሽ ናቸው ፡፡ የማይወራ ወሬ፣ የማይሰደብ ስድብ፣ የማይቀርብ ሃሳብ የለም፡፡ ችግሩ ግን ወሬ የትም አያደርሰንም፡፡ እፎይ ያሰኘናል – ከምን? ከትግል! በወሬ ወጣልና! ልክ ልካቸውን ነገራቸው! ብለን ለጥ ብለን እንተኛለና! ይሄ አንድ እርግማን ነው! በወሬ መፈታት ማለት ይሄ ነው!
ደጋግመን በመሳደብ፣ ደጋግመን በማማት ምንም አላፈራን! መሬት ላይ ያለው ችግር አሁንም መሬት ላይ ነው፡፡ “አለ ደሀ ዘውድ አለገበሬ ማድ” ዛሬም ዕውን ተረት ነው፡፡
የኑሮ ውድነት ከጭነት ልክ በላይ እየሆነ ነው፡፡ ብር እየመነመነችና እየከሳች ሞት አፋፍ ላይ ናት፡፡ ድንችን፣ ጤፍን፣ ልብስን፣ የቤት ኪራይን፣ ደብተርና ስክሪፕቶን መጋፈጥ ተስኗታል፡፡ የኑሮ ውድነት የሚያስከትለው የወንጀል ድርጊት አለ፡፡ተቋማትን በሚገባ አለመገንባታችንና ሥርዓቱን በሁሉም ዘርፍና መስክ አለመሞከራችን ብዙ ቀዳዳዎችን ከመፍጠሩም በላይ፣ ለችግርና ለአደጋ የሚዳርግ ሁኔታ መኖሩ እየተስተዋለ ነው፡፡ የዜጎች ወደ እስር ቤት መጋዝ ያስከተለው ጥያቄና አለመረጋጋት ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ማዕድን በመገኘቱ ሀብት ተፈጠረ ብለን ደስ ባለን ማግስት ፖታሽ ፍለጋ ሊቋረጥ ነው፤ ነዳጅ የሚፈልግ ኩባንያ ሥራ እንዲያቆም ተደረገ መባሉን ስንሰማ ያሳስበናል፡፡መሥርያ ቤቶች ሲልፈሰፍሱና ውሳኔ መስጠት ሲያቅታቸው ማየቱም ወዴት እየሄድን ነው የሚያሰኝ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ ደሃ አገር ናት ተብላ ትጠቀሳለች እንጂ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች በመንግስት ጣልቃ ገብነት ተከፋፈሉ ተጣሉ፣ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የሃይማኖት ነጻነታችንን ሲሉ ድምጻቸውን አሰሙ ፣ በመንግስት ፕሮፓጋንዳ የእስልምናና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ተባሉ፣ ወዘተ የሚል አንሰማም ነበር፡፡ አሁን በመስጊድም በቤተክርስቲያንም አካባቢ ይህን የምእመናን ሮሮ እየሰማን ነው፡፡ድሮ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር ለማስታረቅ ሩጫ ነበር፡፡ አሁን ለማባባስ የሚሯሯጥ ኃይል እንዳለም በግልጽ እየታየ ነው፡፡ መፍትሔ ከማስገኘት ይልቅ የበለጠ ብጥብጥ እንዲከሰት ከውጭም ከውስጥም ግፊት እየበዛ ነው፡፡
አንድነታችንን የሚፈታተኑ የጠባብ ጐሰኝነትና አካባቢያዊ ስሜት የተላበሱ አስተሳሰቦች እዚህም እዚያም ሲሰሙና በየካፌና በየድራፍት ቤቱ መሟሟቂያ ሲሆኑ ማስተዋልም እ – እ – የሚያሰኝ ሆኗል፡፡ በዳያስፖራው ያለው ዘረኝነት፣ ጐሰኝነት፣ መከፋፈል፣ መራራቅ፣ ሃይማኖትን መጠቀሚያ ማድረግ፣ ከጠላት ጋር ወግኖ መሟገት፣ አገርንና የአገርን ክብር አሳልፎ መስጠትና ፖለቲካን ቢዝነስ በማድረግ ለአትራፊነት መወራጨት፣ አስፈሪ የሆነ አቋምና እንቅስቃሴ ማድረግ ከዚህ ራቅ ቢልም አሳሳቢ ነው፡፡ ሊታሰብበት እና በጋራ ልንታገለው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)

No comments:

Post a Comment

wanted officials