ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዙሪያ መረጃ እንዳያቀርብ ታገደ
በሳውዲ አረቢያ እና በመካከለኘው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በደል እና ስቃይ በማለዳ ወጎቹ ዘገባው የሚታወቀው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ በመረጃ ቅበላው ባልተደስቱ ወገኖች ለእስር መዳረጉ ይታወሳል። ነብዩ ሲራክ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ከኖረባት ሳውዲ አረቢያ «ጅዳ» ከተማ በስሙ በከፈተው ሶሻል ሚዲያ እና ከቅርብ ግዜ ወዲህ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ወኪል በመሆን በአረቡ አለም የሚገኙ ወገኖች የሚያሰሙትን እሮሮ በማስተጋባት በህዝብ ዘንድ ክብር እና አድናቆትን ያተረፈ ጋዜጠኛ ነው።
ይህ ጋዜጠኛ እንደማንኛውም ሰው የስደት አለም ህይወቱን ለመግፋት በግል ተቀጥሮ ከሚሰራበት መ/ቤት የስራ ሰዓት ውጭ የእረፍት ግዜውን መስዋት በማድረግ ሰለቸኝ፡ ደከመኝ ሳይል «ሳይማር ያስተማረውን ወገኑን» በሙያው ሲያገለግል የኖረ ጋዜጠኛ መሆኑ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይነገራል። ነብዩ ሲራክ በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፀሙ ቅጥ ያጡ ግፍ እና በደሎች መቋጫ ይበጅላቸው ዘንድ በሚያቀርባቸው ተከታታይ ዘገባዎቹ በስልክ እና በጽሑፍ ይሰነዘሩበት ለነበሩ ስድብ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ቅንጣት ያህል ሳይሸበር ወህኒ እስከገባበት ዕለት የወገኑን ህይወት ለመታደግ ከማለዳ ወግ የመረጃ ቅበላው ባሻገር በስው ሃገር በወረበሎች የታገቱ እህቶቻችንን ነጻ ለማውጣት ከህግ አስከባሪዎች ጎን ቆሞ የአጋች እና ታጋች ድራማ በሠላም እንዲጠናቀቅ ያደረገ ከህዝብ የወጣ ለህዝብ የኖረ ኢትዮጵያዊ ነው።
ከዚህ ባሻገር ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ለውጭ ሃገር ዜጎች ያወጣውን የ 6 ወር እና የ 3 ወር የግዜ ገደብ መጠናቀቅ ተከትሎ ሰነዶቻቸውን ለማስተካከል ጅዳ ቆንስላ ጽ/ቤት አይን ያልገልጹ ህጻናት ልጆቻቸውን ታቀፈው በጠራራ ጸሃይ ሲነፍሩ ለነበሩ እናቶች እና በስደት አለም ግራ ተጋብተው በተስፋ ቆንስላ ጽ/ቤት በር ላይ ድንጋይ ተንተርሰው ጸሃይ እና ነፋስ ሲፈራረቅባቸው ለነበሩ ዜጎች ቀዝቃዛ ውሃ በማደል ከሰው ምስጋናንን ከፈጣሪ ጽድቅን ያገኘ ሩሩሁ እና ለወገን አዛኝ መሆኑ ይታወቃል።
በሰው ሃገር ተስፋ ሰንቀው ግፍ በደሉ የስደት አለም ኖሮቸውን መቅኔ ላሳጣው ወገኖች ድምጽ በመሆን የሚታወቀው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቆንስላው ጽ/ቤት በአግባቡ መስተናገድ እና ፈጣን የሆኑ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚገባው ባቀረበው የመፍትሄ ሃስብ በተበሳጩ አንዳንድ የጽ/ቤት ሹማምንቶች ቂም ተይዞበት ጉድጓድ ሲማስለት መሰንበቱ ይታወሳል። ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ እንደ ዜጋ በጅዳ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር ስር የሚገኙ ንብረቶችን ለማስተዳደር በት/ቤት የወላጆች ኮሚቴ እና በተለያዩ የኮሚኒቲው መዋቅሮች የሃላፊነት ቦታዎች እንዲያገለግል በማህበረሰቡ ተመርጦ የመረጠውን ህዝብ በቅንነት እና በታማኝነት ለማገልገል በነበረው ሂደት ውስጥ ህሊናው የማይቀበላቸውን አያሌ ሚስጥራዊ አሰራሮች በመቃወሙ ብቻ ከነበረበት የሃላፊነት ቦታ እንዲነሳ ከማድረጉም በላይ ላልተወሰነ ግዜ ቆንስላ ጽ/ቤት አካባቢ እንዳይደርስ ህገወጥ ውስኔ ተላልፎበት እንደነበር የሚያስታውሱ ወገኖች ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ ከወህኒ ነጻ ከወጣም በኃላም ስለወገኑ ስቃይ እና በደል እንዳይጽፍ እና እንዳይናገር የተጣለበት የህሊና ነጻነት ገደብ ከዚህ በላይ በተገለጹ መስረታዊ ጉዳዩች ህዝብ መረጃ የማግኘት መብቱን ለመቀልበስ በእጅ አዙር የተውሰደ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል።
ከሁለት ወራት ወህኒ ቆይታ በሃላ በቀርብ ቀን ነጻ የወጣው ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ በአሁኑ ሰአት በመልካም ጤንነት ላይ መሆኑን ቢታወቀም ጋዜጠኛው ከእንግዲህ በስደተኞች ዙሪያ ምንም አይነት መረጃዎችን በሶሻል ሚዲያ ሆነ በጀርመንድ ድምጽ እንዳይዘግብ ከባድ ማስጠንቀቂያ የተላለፈበት መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል ። የጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ የህሊና እስረኛ መሆንን ተከትሎ አንዳንድ ወገኖች በመካከለኛው ምስራቅ ግፍ እና በደል የሚፈጸምባቸውን በሚልዮን የሚቆጠሩ ድምጽ አልባ ኢትዮጵያውያን ህይወት የከፋ ሊያደርገው እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment