መኢአድ “ሕዝባዊ አንድነት ለነፃነት” የሚል የሕዝብ ንቅናቄ ጀመረ
ሰንደቅ
በሳውላ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አደረገ
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በደቡብ ክልል በጎፋ ልዩ ዞን በሳውላ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂዷል። ፓርቲው በሳውላ ከተማ ያካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ “ሕዝባዊ አንድነት ለነፃነት” በሚል መሪ ቃል መሆኑን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ የእዮብዘር ዘውዴ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። በቀጣይ በዚሁ መሪ ቃል መሠረት በጎንደር፣ በአሶሳ እንዲሁም በሌሎች ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ በእቅድ ላይ መሆናቸውንም አያይዘው ገልፀዋል።
“ሕዝባዊ አንድነት ለነፃነት” የሚለው መሪ ቃል “ነፃ የምንሆነው አንድ ስንሆን ነው” የሚል ኃይለቃል መሆኑን የጠቀሱት አቶ የእዮብዘር በዚሁ መሪ ቃል በሳውላ ከተማ የተሳካ ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉን ተናግረዋል።
በሳውላ ከተማ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ በተመለከተ የፓርቲውን ፕሬዝዳንት አቶ አበባው መሓሪን በስልክ አነጋግረናቸዋል።
ሰንደቅ፡- ፓርቲያችሁ በሳውላ ከተማ ሰላማዊ ሰልፉን ለማካሄድ የወሰነበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ አበባው፡- በሳውላ ከተማ ሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ ያነሳሳን ምክንያት የሕወሓት /ኢህአዴግ ተፅዕኖ ወይም የሰብአዊ መብት ጥሰት፤ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የከፋ ቢሆንም፤ የበለጠ የከፋው ደግሞ በደቡብ ክልል ስለሆነ በተለይ በብዛት ከ16 እስከ 20 የሚሆኑ የፓርቲያችን አባላት የታሰሩበት አካባቢ ስለሆነ ነው። የሰልፉም ዋና ዓላማ የታሰሩ አባሎች ያለአግባብ መሆኑን ለመግለፅና ለመቃወም ነው። በአካባቢው ከዚህ በፊት የፓርቲያችን አባላት የሚታሰሩበትና አሁንም የታሰሩ ስላሉ እነሱ እንዲፈቱልን ነው። በአሁኑ ወቅት 12 የታሰሩ ሰዎች ሲኖሩ በዚያው አካባቢ ጎዳዱፍቱ ወረዳ ከ16ቱ ታሳሪዎች 13ቱን በፍርድ ቤት አስፈትተን ሦስቱ ደገሞ ታስረውብናል። በጋሞ ጎፋ ዞን በተመሳሳይ ወደ 12 ሰዎች ተደብድበውና ታስረው የፓርቲውን መታወቂያ ተቀምተዋል እና በአካባቢው የተለየ የሰብአዊ መብት የሚጣስበት ዞንና ወረዳ በመሆኑ ነው ሰላማዊ ሰልፉን ለማካሄድ የወሰነው።
ሰንደቅ፡- በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ጥያቄአችሁ ምን ነበር?
አቶ አበባው፡- በሰልፉ ላይ በርካታ መልዕክቶችን አስተላልፈናል። በተለይ በአካባቢው ወረዳዎች ላይ ከሚፈፀመው የሰበአዊ መብት ጥሰት ባሻገር እንደ ሀገር በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ጠቅላላ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ እስራትና ግድያ ተቃውመናል። ፍትህን ያልተከተለ የእስራት ውሳኔ እንዲቆም፣ ዘረኝነት እንዲወገድ በተለይም ለኢትዮጵያ ዘረኝነት የማይበጅ አስተሳሰብ መሆኑን በመግለፅ የሕወሓት ኢህአዴግ ስርዓት ይሄንኑ እንዲያስወግድ፣ ዜጎች በአንድ ላይ ተሳስረው የሚኖሩ እንደመሆኑ መጠን በቀጣይም አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ፣ ሊከፋፍላቸው የሚችለውን ይሄንኑ ስርዓት በሰላማዊ መንገድ ሊለወጥ የሚችልበትን መፈክርና መልዕክት አስተላልፈናል።
ሰንደቅ፡- የታሰሩ አባሎቻችሁን ለማስፈታትም ሆነ ጥያቄአችሁን ለማን አቀረባችሁ? ሰልፉስ በምን መልኩ ነበር የተካሄደው?
አቶ አበባው፡- ሰልፉ ሰላማዊ ነበር። በከተማዋ ዋና ዋና መንገድ ላይ ተካሂዶ በመጨረሻ በከተማዋ ስታዲየም ላይ ንግግር ተደርጓል። በኋላም ወደ ጽህፈት ቤታችን በመመለስ ከተወሰኑ አባላት ጋር ቀጣይ ስብሰባ አድርገናል። ለአካባቢ ባለስልጣን በተመለከተ እንደውም የሰለፉ ዋዜማ ሕዝቡ ከ12ቱም ወረዳዎች ጎርፎ ወደ ከተማዋ ሲገባ በፍርሃት ተነሳስተው ቅዳሜ ዕለት እኛን አስረውን ነበር። ካሰሩን በኋላ ይሄን ሕዝብ ካላረጋጋችሁ ለሚፈጠረው ችግር እኛ ተጠያቂ መሆናችንን ገልፀው ፈቱን። በኋላም ሕዝቡ ወደግቢው ገብቶ በጩኸት ተቃውሞውን ሲገልፅ ሕዝቡን አረጋጉ ብለው ለቀቁንና እኛም ሕዝቡን አረጋግተን በነጋታው ሰላማዊ ሰልፉን ለማካሄድ በቅተናል። ሕዝቡ በአካባቢው ባለው ችግር የተቆጣ ነው። ችግሩንና ያለውን ሁኔታ ጠንቅቆ ያውቃል።
ሰንደቅ፡- ለሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ እውቅና በመጠየቅ ረገድ የገጠማችሁ ችግር ነበር?
አቶ አበባው፡- ለሰልፉ ፈቃድ መጠየቅ የጀመርነው ከክልሉ ጽ/ቤት ነበር። የክልሉ ጽ/ቤት ወደዞኑ መራን። ዞኑም ለሳውላ ከተማ ከንቲባ እንድንሄድ በማድረጉ የእውቅና ደብዳቤውን ሰጠን እና የእውቅና አጠያየቁ ላይ ብዙም አላስቸገሩንም። ነገር ግን ችግር ያጋጠመን ቅዳሜ ዕለት ከ12ቱም ወረዳዎች ሕዝቡ ወደ ከተማ ሲገባ ተደናግጠው በከተማው ካሉት የፀጥታ ኃይሎች በተጨማሪ ከሌሎች አካባቢዎች አምጥተው አፍስሰዋል። በእውቅና አሰጣጥ ላይ ችግር አልገጠመንም። ቅስቀሳ ስናካሂድ ደግሞ ሳንሱር ለማድረግ ተሞክሯል።
ሰንደቅ፡- ፓርቲያችሁ በክልሉ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርግ ይሄ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው?
አቶ አበባው፡- በዚህ ዓመት በደቡብ ብሔራዊ ክልል ሲያካሂድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በቀጣይም በሌሎች ትልልቅ ከተሞችም እንቀጥላለን። በአካባቢው ፓርቲያችን ጥሩ አደረጃጀት አለን። በ12ቱም ወረዳዎች ጠንካራ መዋቅር አለን። ለምሳሌ በደቡብ ኦሞ ዞን ሴሚናሪ ወረዳ ከሳውላ ከተማ 280 ኪሎ ሜትር ቢርቅም፤ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ለመሳተፍ ከዘጠኝ ቀበሌ የተውጣጡ 320 ሰዎች መምጣታቸው በአካባቢው ጠንካራ መዋቅር እንዳለን አመላካች ነው።
በሰልፉም ላይ ሕዝቡ ከየወረዳው ስለመጣ የከተማውን ሕዝብ ጨምሮ ሰፊ ቁጥር ያለው ሕዝብ ዓላማችንን ደግፎ ወጥቶልናል። በእርግጥ ሰልፉ ከመካሄዱ በፊት የከተማው ባጃጆች አሽከርካሪዎች በመታገታቸው በሰልፉ እንዳይሳተፉ ቢደረግም፤ በሰልፉ ላይ መሳተፍ የፈለገው ሁሉ እንዳለ ነበር የወጣው። ከሰልፉ በኋላ አዳዲስ መዋቅሮችን ለመክፈትና ለማጠናከር የተለያዩ ስብሰባዎች አድርገናል። ዛሬ (ግንባት 4 ቀን 2006 ዓ.ም) ሶዶ ከተማ ስብሰባ አድርገናል። በዚያም ስብሰባ ላይ ተጨማሪ 12 ወረዳዎችና ሁለት ልዩ ከተሞችን በአጠቃለለ መልኩ ገንቢ ውይይት አድርገናል። አሁን በወረዳ ያለውን አመራር በቀበሌ አመራር እየፈጠርን ተናበው እንዲሰሩ የተጠናከረ ስራ እንዲሰራ ነው የምንፈልገው።
ሰንደቅ፡- በአጠቃላይ ፓርቲያችሁ በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? የውህደቱስ ጉዳይ ከምን ደረሰ?
አቶ አበባው፡- ይህ ጉዳይ እየሄደ ያለ ጉዳይ ነው። በተለይ ውህደትን በተመለከተ አሁን የምንለው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ፓርቲያችን በጥንካሬ እየተንቀሳቀሰ ነው።
No comments:
Post a Comment