Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, July 19, 2014

በደቡብ ክልል በሸካና ሸኮ ጎሳዎች ግጭት ከ130 በላይ ቤቶች መቃጠላቸው ተሰማ



-ቁጥራቸው ያልተገለጸ ሰዎችም መሞታቸው ተጠቁሟል

-ለግጭቱ  ምክንያት ናቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች መታሰራቸው ተሰምቷል

በደቡብ ክልል በሸካ ዞን ውስጥ በሚገኙት ሸካና ሸኮ ጎሳዎች መካከል በተነሳ ግጭት ከ130 በላይ ቤቶች መቃጠላቸውንና ከሁለቱም ወገኖች ነዋሪዎች ወደ ቴፒ ከተማ በመሸሽ ላይ መሆናቸው ተሰማ፡፡

በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ግጭቱ ሊፈጠር የቻለው በጋምቤላ አዋሳኝ ድንበር አካባቢ፣ ጉስታ ቀበሌ ውስጥ በሚገኝ የማዕድን ሥፍራ ምክንያት መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ጎሳዎች ግጭት በ1985 ዓ.ም. የተጀመረ ሆኖ በ1994 ዓ.ም. ከረር ያለ ግጭት ውስጥ ገብተው እንደነበር ያስታወሱት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ልዩ የፖሊስ አባላትና የፌዴራል ፖሊሶች መሀል ገብተው ግጭቱን ያስቆሙት ቢሆንም፣ ውስጥ ለውስጥ መተነኳኮሱ ቀጥሎ፣ በተለይ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ የከረረ ግጭት በመጀመራቸው በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውንና የሰዎች ሕይወትም እንዳለፈ ይናገራሉ፡፡

የማዕድን ቦታውን ለማልማት ከሸካ ዞን ፈቃድ የጠየቁት ሸኮዎች ፈቃድ በመከልከላቸው፣ መዠንገር ዞን ሄደው ፈቃድ ማግኘታቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የሸካ ዞን የማዕድን ቦታውን ለሌላ አልሚ ሰጥቶ ስለነበር፣ ሸኮዎቹን ሲከለክሏቸው በተፈጠረ ግጭት ለኢንቨስተር የተፈቀደውን ቦታ ይጠብቅ የነበረ የጥበቃ ሠራተኛ በመገደሉ፣ ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉንና የሸኮ ጎሳዎች ሸካዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ እያደረጉ በመሆናቸው ንብረት እየወደመና ሕይወት እያለፈ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በጎሳዎቹ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆም ከተሰማሩት ልዩ ኃይሎች ውስጥ አንድ የፖሊስ ባልደረባ መገደላቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ የችግሩ አሳሳቢነት የተመለከተው የክልሉ መንግሥት የፌዴራል ፖሊስ እንዲገባ በማድረጉ ግጭቱ መብረዱን አስረድተዋል፡፡ የተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሥፍራው እንዲቆዩ ተደርጎ ፌዴራል ፖሊስ መመለሱንም አክለዋል፡፡ የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥትም ግጭቱን ለማብረድ መተባበሩን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ጎሳዎች ግጭት እጃቸው አለበት የተባሉ ነጋዴዎችና ግለሰቦች ታስረው ጊዜ ቀጠሮ እየተጠየቀባቸው ፍርድ ቤት እየተመላለሱ መሆኑንም ነዋሪዎች ጠቁመዋል፡፡ በሁለቱ ጎሳዎች ግጭት ምክንያት ቤታቸው የተቃጠለባቸው በርካታ ነዋሪዎች ቀዬቸውን ለቀው ቴፒ ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙም ነዋሪዎቹ አክለዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥና የክልሉ መንግሥት በጋራ ጉዳዩን እልባት ካልሰጡት ወደማያባራ ግጭት ሊያመራ ስለሚችል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ስለተፈጠረው ግጭት ማብራሪያ ለማግኘት ለሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በተደጋጋሚ የተደረገው ሙከራ ባይሳካም፣ የቴፒ ከተማ አስተዳደር ዓቃቤ ሕግ አቶ አሰፋ ደምሴ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ አሰፋ እንደገለጹት፣ ግጭቱ ያለው ከቴፒ ከተማ በ60 እና 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ያኮ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ ወደ ቴፒ ከተማ ሸሽተው የመጡ ነዋሪዎች መኖራቸውንና እስካሁን ድረስ በተሰባሰበው መረጃ 129 ቤቶች መቃጠላቸውን አስረድተዋል፡፡ ቦታው ሩቅና ገጠር በመሆኑ መረጃ ለማግኘት እንደማይቻል የገለጹት አቶ አሰፋ፣ ቤት የተቃጠለባቸው ነዋሪዎች በቴፒ ከተማ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ጠቁመው፣ ግጭቱ አሁን ስላለበት ሁኔታ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

Source http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment

wanted officials