Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, July 25, 2014

ሰላማዊ ትግሉን ያከበደውና የሀገሪቱ መፃኢ ላይ አደጋ የደቀነው ዋነኛው የተሳሳተ የተቃዋሚዎች ስሌት፤ 2006/7ን በ1997 መነፅር ማየት፡ ክፍል አንድ


በ1997 ዐ.ም ቅንጅት ለአንድነትና ዲሞክራሲ የተጠቀመው ስሌት “5 ሚልዮን ህዝብ አስኮርፎ 80 ሚልዮን ህዝብን ማሰለፍ” የሚል ነበር፡፡ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አዲስ አበባ ከገባ 14ኛ ዐመቱ ነበር፡፡ በተለይም እስከ 1993 ዐ.ም ህ.ወ.ሐ.ት በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ውስጥ ሙሉ የበላይነት ነበረው ብቻ ሳይሆን ሌሎቹ ተጣማሪዎች ለስም ብቻ የተቀመጡ ነበሩ፡፡ ይህ በሁሉም ዘርፍ በሀገድ የሚታይ እውነታ ነበር፡፡ የጦርነት አውድማ የነበረችው ትግራይም ሰላሟን አግኝታ ከዜሮ (de novo )ተነስታ የልማት ስራዎችን ማቀላጠፍና የሚታይ ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስመዝገብ የቻለችበት ጊዜ ነበር፡፡ በክልሉ የነበረችው አንድ የኲሐ ዱቄት ፋብሪካም እነ ት.እ.ም.ት/EFFORT አጀቧትና ትልቅ ለውጥ ነበር፡፡ ሰሀራ በረኸ ላይ ያለች አንድ ትንሽ ኩሬ እጅግ ደምቃ ትታያለችና እንዲያ ሆነ፡፡
ከስርዐቱ የተጠጉቱ ጥቂቶችም በሀብት ተተኮሱ፡፡  የእለት ጉሮሮውን ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች ምፅዋት የሚዘጋ በርካታ አስር ሺህ የትግራይ ተወላጅም ነበር፡፡ “ትግሬዎች አዲስ አበባን ተቆጣጠሯት፤ ከለማኙ እስከ ጠቅላይ ሚኒስተሩ እነሱው ናቸውና” መሰል ስላቆች በሄድክበት ሁሉ የሚሰሙ ነበሩ፡፡ የግል ሚድያዎቹም የትግራይን “የምድር ገነትነት” የነመቐለም “ሁለተኛይቱ ፓሪስነት”በፊት ገፆቻቸው ማቅረቡ ዋነኛ አሻሻጭ ርእስ ሆኖላቸው ነበር፡፡ “ትግራይ እስክትለማ ኢትዮጵያ ትድማ” በሀገሪቱ ዝነኛና ተዘውታሪ የግል ሚድያዎችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሀረግ ነበረች፡፡ በዚህም በዚያም ሁሉም ነገር በትግራይ ተወላጆች ቁጥጥር ያለ እንዲመስል ሆነ፡፡ በርካቶችም ይህንን ከልባቸው አምነው ተቀበሉ፤
ቅንጅት ይህንን በግላጭም በስውርም የሚወራ የተቀናጀ ሐሜትና በበርካታ ትግራይን በጋዜጣ ብቻ የሚያውቃት ህዝብ ዘንድ የተፈጠረውን ስሜት ማጋጋል ተያያዘው፡፡ ስሌቱ ቀላል ነው፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ትግራይን በጋዜጦችና በመንደር ወሬ እንጂ በአካል አይቷት አያውቅም፡፡ እናም ስሌቱ “በ4ና 5 ሚልዮን የትግራይ ህዝብ ዋጋ የቀሪውን 80 ምናምን ሚልዮን ድጋፍ ማግኘት!” ቀላል ስራ ነበር፡፡ ሙሉ ትኩረቱ ህ.ወ.ሐ.ትና አለፍ ብሎም የትግራይ ህዝብ ላይ በማነጣጠር መነጠልና ሌላውን በስሜት መያዝ ነበር፡፡ የህዝቡ ስሜት ቋፍ ላይ ነበር፡፡ ከተመሰረተ ገና 6 ወሩ የነበረው ስሙ ብቻ የተቀናጀው ቅንጅትም በትንሽ ጥረት ህዝቡን በስሜት ንጦ ከጎኑ አሰለፈው፡፡ ይህ የፖለቲካ ስሌት ነው፡፡ በትግራይ ህዝብ ላይ ክፉ ጉዳት ለማድረስ እቅዱ ነበረው ማለት ግን አልችልም፡፡ ሲጀምር በፓርቲው ቁንጮ አመራርነት በርካታ የትግራይ ተወላጆች ሁሉ ነበሩ፤ ሲቀጥል እንዲህ በአንድ ህዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚፈቅድ ኢትዮጵያዊ ህሊና ኖሮም አያውቅም፣ ለወደፊቱም አይኖርም፡፡ ለኔ በቀላሉ የህዝቡን ስሜት የሚገዛበትና ድጋፍ የሚሸምትበት አቋራጭ መንገድ ይህ ሁኖ ስላገኘው ይመስለኛል፡፡ ከዚያ በኃላ የሆነው ግን ብዙ ነውና ባልነካካው፡፡
2006/07፡
2006/07 ከ1997 በእጅጉ ይለያል፡፡ እጅግ መሰረታዊና ፍፁም ተቃራኒ የሆኑ እውነታዎች ናቸው ያሉት ፡፡ ዘንድሮን በ1997 ዐ.ም መነፅር ማየት እጅግ አክሳሪው የፖለቲካ ስሌት ነው፡፡ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መሰረታዊ ባሕርይ ባይቀየርም ግዜውና ሁኔታዎች በእጅጉ ተቀያይረዋል፡፡
1. ህ.ወ.ሐ.ት በመከላከያውና ድህንነቱ ካለይ የበላይነት በቀር በመሰረታዊና የየዕለት መንግስታዊ ክንውኖች፣ በመሰረታዊ የሐሳብና ፖሊሲ አመንጪነትና አስፈፃሚነትና መሰል መንግስታዊ መዋቅሮች ያሉት ድርሻ ተመናምኗል፤ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ጭንቅላትነቱም አብቅቷል፡፡
2. በአንፃሩ የነብአዴንና ደኢህዴን መጠናከር፣ የኦ.ህ.ዴ.ድ.ም አለሁኝ አለሁኝ ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ በግልፅ የሚያየው እውነታ ሆኗል፡፡ በፌደራል መዋቅር ያላቸው አቅምና ሚና ጎልቶ እየወጣ ነው፡፡ በሚያስተዳድሩት ክልል 100 በ100 ማለት ይቻላል ከህ.ወ.ሐ.ት ጥላ ወጥተዋል፡፡
3. የነገሮች መገጣጠም ይሁን ሆነ ተብሎ ባለፉት 9 ዐመታት ሌሎቹ ክልሎች በአንፃራዊ በኢኮኖሚ ፈቀቅ ሲሉ ትግራይ ግን ቁልቁል እንድታድግ ሆኗል፡፡ ከህ.ወ.ሐ.ት ክፍፍል ጀምሮ የስልጣናቸው ዋነኛ አደጋ ከራሱ ከህ.ወ.ሐ.ት እንደሚመጣባቸው የተገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር የተያያዙት የተጠራጣሪነት፣ አቅም ያለውን የትግራይ ተወላጅ ሁሉ በስጋት የመፈረጅና ዙርያቸውን በአቅመ-ቢሶች የማጠር ሂደት ከ1997 ዐ.ም በኃላም ተጠናክሮ ቀጥሎ ህ.ወ.ሐ.ት በተላላኪ አቅመቢሶች ሲወረር ክልሉ በአፈፃፀም በሁሉም ዘርፍ የመጨረሻውን ረድፍ የሚይዝ፣ በየዐመቱ ከ30-50% የክልሉን በጀት ፈሰስ የሚያደርግ፤ በሙስና፣ በጥቅም፣ በዝምድና የተሳሰረ፤ ማልማትን ሳይሆን የውሸት ዳታ መፈብረክን የመረጠ የክልል አስተዳደር ተሰራ፡፡ ይህም በውጤቱ ክልሉን የገደለና የህዝቡም መጀመርያ ላይ ፈነጠቅ ብሎ የነበረውን የእድገት ተስፋ ያመከነ ነበር፡፡
4. በየአካባቢው የተከፈቱት የስምም ቢሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ከአካባቢው ወጣ ብሎ የሌላውን አካባቢ ነባራዊ ሁኔታ እንዲገነዘብ አስችሎታል፡፡ ጀማሪዎቹ አክሱምና ዐዲግራትን ተቃቸውና ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ብቻ እስካሁን ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተመርቀዋል፡፡ ከዚሁ ከ25 ሺሁ በላይ ከሌላ ክልሎች የመጡ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች በዙርያቸው ስንት ህዝብ እንዳለ መገመት ይቻላል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ከት/ት መልስ በየአካባቢው የሚፈጥሩት የሐሰብ ተፅዕኖ አስቡ፡፡ የትግራይን ህዝብ እውነተኛ ማንነት፣ ያለበት የኢኮኖሚና የፖለቲካ እውነታና መሰል መረጃ ለመጡበት ማሕበረሰብ ማስተላለፋቸው አይቀርም፡፡ በዐይናቸው ያዩትን እውነት የፈለገውን ቃላት ጠምዘህና እውነታ አዛብተህ ብታቀርብ አይሰሙህም- የመጡበት ማሕበረሰብም አይሰማህም፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ መቸም ቢሆን አጠገቡ ያለው ወዳጁ የነገረውን የበለጠ ይቀበላል፡፡
5. አሁንም ቢሆን የፌደራሊዝም መዋቅሩ በትክክል እየተተገበረ ነው ባይባልም ክልሎች በ99% የውስጥ ጉዳያዮቻቸው ላይ በራሳቸው የማቀድ፣ የመወሰን፣ የማስፈፀምና እርምጃ የመውሰድ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ በየክልሉ ለሚደረጉ የሰብዐዊ መብት ጥሰት፣ ሙስና፣ የልማት ጥያቄዎች መልስ ማግኘትና አለማግኘት ክልሎችና የሚመሯቸው ፓርቲዎች ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ አንድን የመቱ ሰው መቱ ላይ ለሚታሰረው፣ ለሚገረፈው፣ ለሚለማው፣ ለሚፈርሰው ሁሉ ተጠያቂው ኦ.ህ.ዴ.ድና ተሿሚዎቹ እንደሆኑ በዐይኑ የሚያየው ሐቅ ሁኖ ሳለ “ህ.ወ.ሐ.ት ነው እንዲህ የሚበድልህ፣ የህ.ወ.ሐ.ት የበላይነት ምናምን” ብትለው እንዴት አምኖ ይቀበልሀል- እንደውም ይንቅሀል፡፡ የወሎ ህዝብ ማን እንደሚመራው፣ እንደሚጮቁነው፣ እንደሚገርፈው፣ እንደሚሰራለት፤ ይህንን እቅዱንም ማን አውጥቶ ማን እንደሚያስፈፅም ወ.ዘ.ተ በዐይኑ የሚያየውን እውነታ ዐይንህ ግንባርህ ነው ብትለው ሊሰማህ አይችልም፡፡ አንድ የጉራጌ ገበሬን የቀበሌው፣ የወረዳውና የዞኑ የደ.ኢ.ህ.ዴ.ን ተጠሪ የሚያደርስበት የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ ያልተፈቱ የልማት ጥያቄዎቹ ወ.ዘ.ተ ነቅሰህ ዘርዝረህ እንደምትፈታለት ብትነግረው እንጂ ስለ’ህ.ወ.ሐ.ት ወይም የትግሬ በላይነት ምናምን..’ ብትሰብከው ምን ብሎ ይሰማሀል፣ እንዴትስ ይቀበልሀል? ዐይኑ የሚያየው እውነታና የሚያሳስበው ነገር ሌላ፤ አንተ የምትለው ሌላ- አራምባና ቆቦ፡፡
የዲያስፖራ ፖለቲከኞች ይሀንን ነው እያደረጉ ያሉት፡፡ በ1997 ዐ.ም በሬ ዘንድሮም ማረስ ይፈልጋሉ፡፡ (የሰሞኑ ባንዴራ ማቃጠል ትንሹ ማሳያ ነው)፡፡ ይህ ደግሞ አንድም እንደተደራሽ የሚያስቡትና ድጋፉን የሚሹት target አይቀበላቸውም፤ ሁለትም የትግራይ ህዝብ እያደረገ ያለውን ብርቱ ሰላማዊ ትግል ማኮላሸትና በግድ ወደ ህ.ወ.ሐ.ት እንዲጠጋ የሚያስገድድ ይሆንበታል፡፡ በዚህም በዚያም ስሌቱ ኢ-አመክንዮአዊና ፉርሽ ነው፡፡ በራሱ በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ሜዳና ካርድና ተጫውተው እንዴት እንዲያሸንፉስ ይጠብቃሉ?
እንደዘንድሮ ድንብርብሩ፣ እንደዘንድሮ አምባገነንነቱና እንደዘንድሮ ሙሰኝነቱ ለመገዳደር ቀላል የነበረው ኢህአዴግ የነዚህ ጭፍንና በጥላቻ የታወሩ ሰዎች መላቅጡ የጠፋበት አካሄድ ተጨማሪ ዕድሜና ጉልበት እየሰጡትና የኢትዮጵያን ስቃይ እያስረዘሙት ያለ ይመስለኛል፡፡ እንደኔ ግን በ1997 ዐ.ም በሬ 2006/07 ላይ አይታረስምና ስሌታቸውን ቢገመግሙ፤ እራሳቸውንም ሀገሪቱንም ተሸናፊ የሚያደርገውን የሀገርን አንድነትና ፍቅር ከመፈተን አልፎ አንዳች በጎ ውጤት የማያመጣላቸውን መንገድ ትተው የተሻለውንና እራሳቸውንም ሀገሪቷንም አሸናፊ የሚሆኑበት ቀናውን መንገድ ቢመርጡስ እላለሁ፡፡
(ለዛሬው በተቃዋሚዎች ዘንድ ያለውን መሰረታዊ የስሌት ስህተት ብቻ ለማተኮር ስለታሰበ ነው፤ ቀሪው እንሄድበታለን፡፡)

No comments:

Post a Comment

wanted officials