Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, July 31, 2014

ሦስት የኢቴቪ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከሥራቸው ለቀቁ

ሦስት የኢቴቪ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከሥራቸው ለቀቁ

በ ፍሬው አበበ (ሰንደቅ ጋዜጣ)
በርካታ ጋዜጠኞች በለውጡ ደስተኞች ሆነዋል
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት) ሦስት ከፍተኛ ኃላፊዎች በቅርቡ ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የወቅታዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር የነበረው ጋዜጠኛ አሸብር ጌትነት፣ የትምህርታዊ ፕሮግራሞች ክፍል ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው አቶ ተመስገን ገ/ህይወት፣ የመዝናኛ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበረው አቶ ፍቅር ይልቃል በወራት ልዩነት ድርጅቱን መልቀቃቸው ታውቋል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ከጥር ወር 2006 ዓ.ም ጀምሮ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ከኃላፊነታቸው ተነስተው በኢቴቪ ከተሾሙ በኋላ የድርጅቱን የአሠራር ሥርዓት ለማስተካከል የወሰዱት ጠንካራ እርምጃዎች በኃላፊዎቹ እንዳልተወደደ ምንጮች ተናግረዋል።
በኢቴቪ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የሚደረጉ የውጪ አገር ጉዞዎች በጥቂት ግለሰቦች ሞኖፖሊ ብቻ ተይዞ የቆየ ሲሆን፤ አዲሱ ዳይሬክተር ይህን አሰራር በመሰረዝ የሚመለከታቸው ሪፖርተሮች በየተራ ተመድበው እንዲሰሩበት ማድረጋቸው፣ አንዳንድ ኃላፊዎች የጥቅም ግጭት በሚያስከትል መልኩ ኢቴቪ ውስጥ እየሰሩ በግል ድርጅታቸው አማካይነት ሥራዎችን ለመወዳደር ማመልከታቸውና ይህም ተቀባይነት ማጣቱ፣ እንዲሁም ለሙስናና ብልሹ አሰራር ክፍት የነበሩ አሰራሮች እየተዘጉ መምጣታቸው ኃላፊዎቹን ሳያበሳጭ እንዳልቀረ ምንጮቹ ጠቁመዋል።
አንድ የድርጅቱ ባልደረባ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገረው፤ አዲሱ ማኔጅመንት ሥር ነቀል ለውጥ እያደረገ መምጣቱ በአብዛኛዎቹ ጋዜጠኞችና ሠራተኞች ዘንድ ድጋፍ ማግኘቱን ተናግረዋል። አንዳንድ ኃላፊዎች ያለ ችሎታቸው ጭምር ተመድበው የሚሰሩበት ሁኔታ እንደነበርና ይህም በሰራተኛው ዘንድ ቅሬታ ሲቀርብበት ነበር ያሉት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፤ ይህ ሁኔታ አሁን እንዲስተካከል መደረጉ አስደስቶናል ብለዋል። በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ የሚካሄደው ለውጥ በዚሁ ከቀጠለ በቀጣይ ሕዝባዊ ሚዲያ ለመፍጠር የሚያስችል ይሆናል ብለው እንደሚገምቱ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝን በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
    ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ወደ ኮርፖሬሽን ደረጃ እንዲያድግ የሚደነግገውን አዋጅ ተቀብሎ ማጽደቁ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials