Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, July 29, 2014

የተበታተነውን ትግል በአንድነት ሊመራ የሚችል የአንድነት ሀይል እንዲቋቋም የቀረበ ሀገራዊ ጥሪ

የሚችል የአንድነት ሀይል እንዲቋቋም የቀረበ ሀገራዊ ጥሪ

entcimgres
የተበታተነውን ትግል በአንድነት ሊመራ የሚችል የአንድነት ሀይል እንዲቋቋም የቀረበ ሀገራዊ ጥሪ

የወያኔን አፓርታይድ ስርዓት ለማስወገድና በሀሉ አቀፍ ህዝባዊ የሽግግር መንግስት ለመተካት ጥንስስ በመሆን መሰረት የሚጥልና የተበታተነውን ትግል በአንድነት ሊመራ የሚችል የአንድነት ሀይል (የስደት መንግስት እንደአማራጭ) እንዲቋቋም የቀረበ ሀገራዊ ጥሪ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብሄራዊ ውርደት አጥልቶባታል። ህዝባችን በሀገር ውስጥና በስደት ለአሰቃቂ ግፍና በደል ተዳርጓል። በሀገራችን ያለው የዕለት ከዕለት የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ አፈና፤ እስር፤ ግድያ፤ በዘር ከፋፍሎ ማጋጨትና፣ ሥር የሰደደው የወያኔ ሙስና በብዙ ሕዝብ ዘንድ አሜን ብሎ መቀበል የተለመደ ሆኗል። ሌሎች የሕብረተሰቡ ክፍሎች ደግሞ ተስፋ በመቁረጥ ግዜ ይለውጠዋል በሚል ዘይቤ ግፉን ተቀብለው ይኖራሉ። የኢትዮጲያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ተስፋ መቁረጥ አማራጭ ነው ብሎ አያምንም። እንደውም በየእለቱ በስርአቱ እየተክናወኑ ያሉት መጠነ ሰፊ ሰቆቃዎችን ስናጤን፤ ሀገርወዳድና ነጻነት ናፋቂ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን መሰረት ያደረገ የቆረጠና የመረረ ትግል የሚደረግበት ወሳኝ ምእራፍ ላይ መድረሳችንን ምክርቤቱ በጽናት ያምናል። በተለይም ወያኔ ላይ ያለው ግፊትና ውጥረት ከተለያየ አቅጣጫ እያደገ በሚገኝበት በዘህ ወሳኝ ወቅት የወያኔን አፓርታይድ ስርአት እንዴት ማስወገድ እንደሚቻልና ተተኪውን የመንግሰት ቅርፅና አስታዳደርን አስመልክቶ የዲሞክራሲ ሃይሎችና ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በመሰባሰብ የጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸው እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ፤ ለኢትዮጵያ የቆመ መንግስት የለም። በመሆኑም ሀገራችን በመንታ መንገድ ላይ ትገኛለች:: አንደኛው መንገድ ወያኔ/ኢህአዴግ የስልጣን እድሜውን ባራዘመ ቁጥርና እንዲሁም የማይቀረው ውድቀቱን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለው ብጥብጥ፤ ማናልባትም አይተን የማናውቀው አይነት የደም መፋሰስ ጎዳና ሲሆን ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ምክክርን፤ ቅድመ ዝግጅትንና የጋራ ስምምነትን መሰረት ያደረገ፤ ስርአቱን ለማስወገድና ለመተካት ሁሉንም አካላት የሚያሳትፍና ሀገራችንን ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲ ሊወስዳት የሚያስችል የሽግግር መንግስት ምሰረታን መሰረት የሚጥልና የተበታተነውን ትግል በአንድነት ሊመራ የሚችል የአንድነት ሀይል (የስደት መንግሰት እንደአማራጭ) ባስቸኳይ ማቋቋም ይሆናል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሽግግር ምክርቤት ከላይ የተዘረዘሩትን አደጋዎች ለመከላከል ስርአቱን በማስወገድና ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ የሽግግር መንግስት ምስረታን መሰረት በመጣል ሂደት ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴና ዘመቻ ባለምአቀፍ ዙሪያ በማካሄድ ላይ ይገኛል። ላለፉት በርካታ ወራት የአገራችን ጉዳይ ከሚመለከታቸው የፖለቲካና ሲቪክ ድርጅቶች፤ ምሁራን፤ ታዋቂ ግለሰቦችንና፤ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ በጉዳዩ ሲያወያይና የምክክር ጉባኤዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። እንዲሁም ስርአቱን በማስወገድና በመተካት የትግል ሂደት ላይ ወሳኝ ሚና ሊጫወት የሚያስችለውን የወደፈቱን የመንግስት ቅረጽ የሚያሳይና በሽግግር ወቅት መኖር ስለሚገባው የመተዳደርያ ቻርተር ረቂቅ በማዘጋጀት ለውይይትና ለምክክር በኢትዮጵያና በውጭ ለሚገኘው ህዝብ ማሰራጨቱን ቀጥሏል። ወያኔ ላይ ያለው ግፊትና ውጥረት ከተለያየ አቅጣጫ እያደገ በሚገኝበት በዘህ ወሳኝ ወቅት የወያኔን አፓርታይድ ስርአት ለማስወገድና ተተኪውን የመንግሰት ቅረጽና አስታዳደርን አስመልክቶ የዲሞክራሲ ሃይሎችና ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በመሰባሰብ በመመካከርና የጋራ ስምምነት ላይ በመድረስ አንድ ኢትዮጵያዊ የአንድነት ሀይል (በጥንስስነት የሚያገለግል የስደት መንግሰት እንደአማራጭ) አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው።
የሽግግር ምክር ቤቱ ከተነሳበት አላማ ጋር ተያይዞ የአምባገነናዊነት አዙሪት በአገራችን ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይሰበር ዘንድ፤ ይህን አፓርታይድ ስርዓት በማስወገድና በሁሉ አቀፍ ህዝባዊ የሽግግር መንግስት የሚተካውን አካል ወደፊት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቋቋም መሰረት የሚጥልና ጥንስስ በመሆን አጠቃላይ የለውጥ ትግሉን ሊመራ የሚችል ሀይል ማቋቋም አስፈላጊነት ወሳኝ ምራፍ ላይ እንደደረስን ምክር ቤቱ በጽኑ ያምናል። ይዋል ይደር እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ማሸነፉና የወያኔ ጸረ-ኢትዮጵያ ስርዓት መገርሰሱ አይቀሬ ነው። ጥረታችን በተደጋጋሚ በታሪካችን እንዳየነው ይሄኛው ሄዶ፤ ሌላ አምባገነን ስልጣን ላይ ወጥቶ፤ ትግል ሀ ብሎ መጀመር እዚህ ላይ እንዲያቆም ነው!
1-የአንድነትሀይል (የስደት መንግስት እንደአማራጭ) ምሰረታ ወቀታዊ ነው፤
የሸግግር ም/ቤቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያቀርበዉ ግልጽና የተሻለ አማራጭ “ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ የሽግግር መንግሥት” በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቋቋም ነዉ። ይህ የሚተገበረው ስርአቱ ሲወገድ ነው። ስለዚህ ሰርአቱን ለማስወገድና ለመተካት ሁሉንም የዲሞክራሲ ሃይሎች የሚወክልና ትግሉን በአንድ ድምጽ በአለም አቀፍ ደረጃ ሊመራ የሚችል የአንድነት ሓይል (unified force) ማቋቋም አስፈላጊነት አስቸኳይና ወቅታዊ ነው። ይህ የአንድነት ሃይል ትልቁን ራእይ ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ የሽግግር መንግሥት እውን ለማድረግ፤ መሰረት በመጣልና ጥንስስ በመሆን ስርአቱን ለማስወገድ ወይም ለማስገደድ ትግሉን በአንድ ወጥ መምራት ቢጀምር፤ ለኢትዮጲያ ህዝብና ለአለም አቀፉ ህብረተሰቡ ትልቅ አማራጭ በመሆን፤ ሰርአቱን በአጭር ጊዜ ማስወገድ፤ ቢያንስ ማስገደድ እንደሚችል፤ የሸግግር ም/በቱ በጽናት ያመናል። አንድን ስርአት ለመለወጥ የሚቻለዉ እርሱን በሌላ በተሻለ ስርአት በመተካት ነዉ። ዝም ብሎ ፍትህ፤ እኩልነት፤ ዲሞክራሲ ወዘተ… ይምጣ ብሎ አማራጭ ሳያቀርቡ መታገል ሀላፊነት የጎደለዉና መፍትሄ የማይሰጥ አካሄድ ነዉ። ህዝቡም ባሁኑ ሰአት በግልጽ እየጠየቀ የሚገኘዉ ይህንኑ ጥያቄ ነዉ። ስርአቱ ይዉደቅ ትላላችሁ በናንተ በኩል ግን ምን የተሻለ አማራጭ ይዛችሁ ነዉ ስርአቱን ለመጣል የምትታገሉት? እንዲያዉም አንዳንዶቹ “ከማያዉቁት መልአክ የሚያዉቁት ሰይጣን ይሻላል” እያሉም ተቃዋሚዋችን እየተቹ የሚገኙትም ለዚሁ ነዉ። ስለዚህ ተቃዋሚዋች ስርአቱን በማስወገድና በመተካት ሂደት ላይ ግልጽና ሊጨበጥ የሚችል፤ እንዲሁም የህዝቡን አመኔታ ሊያገኝ የሚችል ዲሞክራሲያዊ አማራጭ ለህዝቡ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ከዚህ በፊት ተቃዋሚ ሃይሎች ስንሄድበት የነበረዉ እየታገልን እንቀጥል ጊዜዉ ሲደርስና ለዉጥ ሊመጣ ሲል ይህንን ጥያቄ እናስተናግዳለን የሚለዉ አካሄዳችን የትም አላደረሰንም። በታሪካችን ከሶስት በላይ የዲሞክራሲያዊ ሽግግር እድሎች አምልጠዉናል። የተሻለ አማራጭ ይዘን ባለመገኘታችንና የሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ መንገድ በመከተላችን፤ በቅርቡ እንኳን የተፈጠረዉን የስልጣን ክፍተት መልካም አጋጣሚ መጠቀም ያልተቻለው ምንም አይነት ቅድመ ዝግጅት ባለመደረጉና አቅም ያለው ያንድነት ሃይል ባለመኖሩ ነው። ከዚህም ብዙ የተማርንና ወደፊትም የተሻለ አማራጭን ይዞ የመቅረብን አስፈላጊነት በተጨባጭ የተረዳን ይመስለናል።
2-ከላይ የተዘረዘሩትን ለመተግበር በቅድመሁኔታ ስምምነት ላይ መደረስ ካለባቸው በጥቂቱ፤
2.1. ለዘመናት የነበሩብን ችግሮች የገዢዎች ስርአት እንጂ፤ ኢትዮጵያና የህዝቧ አንድነት እንዳልሆነ በመረዳት፤ የምናካሂደው የጋራ ትግል የኢትዮጲያን አንድነትና ሉአላዊነት መሰረት ያደረገ መሆኑን መስማማት።
2.2 ዛሬ በኢትዮጵያ ዉስጥ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ መንግስት የሚባል እንደሌለና የአፓርታይድ ስርአት መሆኑን ስምምነት ላይ በመድረስ፤ ስርአቱን በአለም አቀፍ ደረጃ በሽብርተኝነት በይፋ በመፈረጅ የጋራ ትግል ለማድረግ መስማማት
2.3. ከላይ በተራቁጥር 1 እና 2 በተቀሱት ላይ መግባባት ካለ አገዛዙ ባስቸኳይ መወገድ ወይም መገደድ እንዳለበትና ሰላማዊ ሽግግር በማድረግ በጊዚያዊነት ሊያስተዳድር የሚችልና ዘላቂና የማያዳግም የዲሞክራሲ ስርአት በመፍጠር ነጻና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን የሚያመቻቸው ተተኪው አካል፤ ሀሉን አቀፍ ህዝባዊ የሽግግር መንግስት መሆን አለበት በሚለዉ መሰረታዊ ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረስ።
2.4.በሽግግር ምክር ቤቱ ተዘጋጅቶ ለውይይትና ለምክክር በኢትዮጵያና በውጭ ለሚገኘው ህዝብ በመሰራጨት ላይ የሚገኘውን፤ ስርአቱን በማስወገድና በመተካት የትግል ሂደት ላይ ወሳኝ ሚና ሊጫወት የሚያስችለውን የወደፊቱን የመንግስት ቅረጽ የሚያሳይና በሽግግር ወቅት መኖር የሚገባውን ስርአት ግልጽ የሚያደርገውን ጅምር የመተዳደርያ ቻርተር ረቂቅን በማዳበር ቋሚ የጋራ ሰነድ እንዲኖረን ስምምነት ላይ መድረስ።
2.5. በዉጭና በውስጥ ያለዉ ሀይል እንዴት እንደሚቀናጅና በጋራ የሚደረጉ ትግሎችን አስተባብሮ ማካሄድና ማታገል እንዴት እንደሚቻል፤ በተለይም የውስጥና የውጭ በሚል ክፍተት እንዳይፈጠር ስምምነት ላይ መድረስ።
2.6. የህብረተሰቡ ከፍተኛ ፍራቻ የሆነዉ ለዉጥ ቢመጣ ሀገር ዉስጥ ምን ሊፈጠር ይችላል ለሚለዉ እጅግ ከፍተኛ ፍራቻና አግባብነት ላለዉ ጥያቄ ግልጽ የሆነ ምላሽ ለመስጠት ስምምነት ላይ መድረስ።
2.7. ለዘመናት ተመሳሳይ ነገር በማድረግ የተለየ ውጤት ከመጠበቅና እኔ ያልኩት ብቻ መሆን አለበት ከሚል የከረረ አመለካከት በመውጣት አዳዲስ ሃሳቦችና አማራጮችን ለማስተናገድ ቀና መሆን።
2.8. ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ዛሬ ላለንበት አደጋና ተደጋጋሚ ብሄራዊ ቅሌት መግባት፤ ለዘመናት በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀናበረ ድረጊትና ቀጣይ ሂደት መሆኑን፤ ኢትዮጵያ ወዳጅ እንዴሌላትና ችግራችን ጥልቅና ውስብስብ መሆኑን በመገንዝብ ትግላችንን ዘላቂ ውጤት ላይ ለመድረስ ብቸኛው አማራጭ በራስ መተማመንና ኢትዮጵያን ሕዝብ መሰረት ያደረገ ትግል ማድረግ መሆኑን ስምምነት ላይ መድረስ።
2.9. ላለፉት 23 አመታት ለነጻነት በተደረገው ትግል በኢትዮጵውያን ከፈተኛ መስዋእትነት የተከፈለ ቢሆንም ፋይዳ ያለው ውጤት ላይ ያለመድረሳችን ዋናው ምንጭ ትግሉን የሚመራ ጠንካራ የአንድነት ሃይል በአማራጭነት ባለማቅረባችንና ማለቂያ በሌላቸው ከወያኔ ለሚሰጡ የተሸራረፉ አጀንዳዎች ቅጽበታዊና ስሜታዊ ምላሽ የመስጠት አዙሪት ውስጥ መውጣት ያለመቻላችንን ተረድተን ትግሉንም ሆነ ድሉን የጋራ የማድረግ አስፈላጊነት ላይ መስማማት።
3-ከላይ የተዘረዘሩትን መሰረት ያደረገ የአንድነት ሀይል (የስደት መንግስት እንደአማራጭ) መመስረትና አመራር የመስጠት አስፈላጊነት በጥቂቱ፤
3.1 ስርአቱን ለማስወገድ ቢያንስ ለማስገደድ የሚያስችሉ የትግል ስልቶችንና መንገዶች (strategy and tactics) ማለትም፤ ህዝባዊ እምቢተኝነት፤ የትጥቅ ትግል፤ የኢኮኖሚ እቀባ (boycott)፤ ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ፤ አለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ትግል፤ ወዘተ የሚያቀናጅና በአንድ ማእከል ሁለንተናዊ ትግሉን የሚመራ ሀይል ይሆናል።
3.2 ህዝቡ ለትግል በስፋት ቢነሳሳ ተስፋ የሚጥልበት የኔ የሚለዉ የሽግግር መንግስት ሊሆን የሚችል የተዘጋጀ ሀይል ይኖረዋል።
3.3 ህዝቡን ያሰባስል፤ ልቡን ያረጋጋል፤ በአንድ አቅጣጫ እንዲመለከት ይረዳዋል።
3.4 ሁሉም ድርጅት ለየብቻ ከሚጮህ አንድ ጠንካራና የሚሰማ ተቋም ይሆናል፡፡
3.5 ሃይልና ጉልበታችንን በማሰባሰብ አቅም ለማጎልበት ይረዳል፤ ከሚገነባዉም አቅም ተቃዋሚ ድርጅቶች ሁሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
3.6 በሽግግር ጊዜ ሊፈጠር የሚችለዉን ማናቸዉንም ግርግር ያስቀራል፤ በሽግግሩ ሂደት የሚኖሩ አለመተማመኖችን በቅድምያ በማስወገድ የሰከነ፤ የተዋጣለትና፤ የተፋጠነ የሽግግር ስርአትን ለማከናወን ይረዳል።
3.7 መንግስትን የማስተዳደር ብቃት ይገነባል ልምድም ይገኛል ብሎም ይዳብራል። መንግስትን በብቃት ሊመሩ የሚችሉ ግለሰቦችን ለማዉጣት ያስችላል
3.8 አሁን በስልጣን ላይ ያሉ በስርአቱ የተከፉ ባለስልጣንነትና የወታደሩ መሪዎችን በመደራደር ልባቸዉን በማሸፈት ለማስከዳትና ወደ ትግሉ ለመቀላቀል ያስችላል ለነሱም ተስፋ ይሰጣቸዋል። በስልጣን ላይ ተቀምጠው በህዝብ ህይወት ላይ ከፍተኛ ጥፋት የፈጸሙትንም በአለም አቀፍ ደረጃ ለፍርድ የሚቀርቡበትን ሁኔታ ያመቻቻል
3.9 ወያኔ፤ ኢሕአድግ በሚል ሽፋን በሁለተኛ ዜግነትና በባርነት ላደራጃቸውና መጠቀሚያ ያደረጋቸውን ኢትዮጵያውያን ነጻ በማውጣት የነጻነት ትግሉን እንዲቀላቀሉ ይረዳል
3.10 የመገንጠል ጥያቄን አላማ በማድረግ ለሚታገሉ የጎሳ ድርጅት አመራርና አባላት ለሆኑ ወገኖቻችን ሽግሽግ በመፍጠር ኢትዮጵያን መሰረት ያደረገ የጋራ ትግል እንዲያደርጉ ብርታት ይሰጣቸዋል።
3.11 የሽግግሩን ሂደት የተቀላጠፈ ለማድረግ መሰራት ያለባቸዉ ማናቸዉንም ዝግጅቶች በቅድሚያ ለማጠናቀቅ ይረዳል።
3.12 በዉጭ ሀገር መንግስታት ተሰሚነትን ያገኛል፤ ተበታትኖ ከመደራደር ይልቅ የተሻለ ድጋፍን የሚያገኝ የአማራጭ ሀይል በመሆን ፍራቻቸዉንም ይቀርፋል።
3.13 በሃገር ዉስጥና ከሃገር ዉጭ ያሉትን ድርጅቶትና የዲሞክራሲ ሀይሎች በሙሉ ትግላቸዉን እንዲያስተባብሩና እንዲየቃናጁ ብሎም የጋራ ትግልን በማድረግ የጋራ ሀገርን የመገንባት ባህል ለማዳበር ይረዳል።
3.14 ተባብሮ የመስራትን ባህል በማዳበርና አላስፈላጊ የሆነን የእርስ በርስ ሽኩቻንና አለመተማመንን በማስወገድ ጥረቶቻችንን ዉጤታማ ያደርጋቸዋል።
3.15 በማናቸዉም መንገድ የስልጣን ክፍተት ቢፈጠር የተዘጋጀዉ ሃይል ሀገሪቷን ሊያረጋጋ የሚችል ይሆናል
4- ከላይ የተዘረዘሩትን ለመተግበርና የአንድነት ሀይል ( የስደት መንግስት እንደ አማራጭ) እንዲቋቋም የምናከናወናቸው ድርጊቶች፤
4.1 ትግሉንና ድሉን የጋራ እናድርገው በሚል መርህ በቀጣይ ከተለያዩ የአገራችን ጉዳይ ከሚመለከታቸው የፖለቲካና ሲቪክ ድርጅቶች መሪዎች፤ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦችና የሃይማኖት አባቶች ጋር ከላይ የተዘረዘሩትን ለመተግበር የሁለትዮሽና የወል ግነኙነቶችና ውይይቶች ይደረጋሉ።
4.2 ከሁሉም አካላት የተወጣጣ የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲዋቀርና ዝግ የሆነ ጉባዔ እንዲደረግ ከፍተኛ ዘመቻና ጥረት ይደረጋል።
4.3 ከላይ የተዘረዘሩትን በሙሉ በመነሻነት (Initiative) በመውሰድ ሽግግር ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ጋር የአንድዮሽና የወል ግንኙነቶችና ውይይቶች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በማድረግ ለተግባራዊነቱ የጋራ እንቅስቃሴና ዘመቻ እናደርጋለን። ሽግግር ም/ቤቱ በጁላይ 2013 በዋሽንግተን ዲሲ ባዘጋጀው ታሪካዊው የምክክር ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ መካከል የተደረገው ስምምነት (memorandum of understanding) ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
5-ማጠቃለያ
ይህ ታላቅ ሀገራዊ ራእይና የአማራጭ መፍትሄ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እንዲያሳትፍ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገርን ከጥፋት የመከላከል ሕዝባችንን ከግፍ የማዳን ሀላፊነት አለበት። ትግሉንና ድሉን የጋራ እናድርገው ከሚለዉ መርህ በመነሳት ማናቸዉም ሀገር ወዳድና ነጻነት ናፋቂ ወገን ሁሉ ከላይ በተዘረዘሩት ሃገራዊ ራዕይና ሂደቱ ላይ የሚጫወተዉ ሚና አለ ብለን ስለምናምን ለተግባራዊነቱ፤ የግል ሃላፊነት በመውሰድ የፖለቲካ ድርጅቶችና ተቋማት ላይ የተለያዩ ግፊቶችን ማድረግና በትግል ሂደቱ ላይ የመሳተፍ የሞራል ሃላፊነት አለበት። በዚህም መሰረት ሀገር የማዳን ጥሪዉ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ተላልፏል። በዚህ አጋጣሚ፤ አማራጭ ብለን ከላይ ባጭሩ በዘረዘርናቸው ሀገራዊ ራእይ ላይ ለመተቸትም ሆነ ሌሎች የተሻሉ አማራጮችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን እየገለጽን፤ በተመሳሳይ የተለያዩ ድርጅቶች አሉኝ የሚሏቸዉን አማራጮች በግልጽ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ እንዲያደርጉ በአክብሮት እየጋበዝን የተለያዩ የድርጅት አባላትም ከድርጅታዊ ሳጥን ውስጥ በመውጣት አስፈላጊውን ግፊት እንደምታደርጉ እምነታችን ነው። በተለይ ህዝብ ከብዥታ በመውጣት የተለያዩ አማራጮችን በማነጻጸር ለነጻነት በሚደረገው የትግል ሂደት ላይ እንዲሳተፍ የመገናኛ በዙሃን ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። በመሆኑም የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጋር በተናጠል የሚደረጉ ቃለ ምልልሶች እንዳሉ ሀኖ፤ በቀጥታ ስርጭት ለህዝብ የሚተላለፉ፤ አማራጮችና መፍትሄዎች ላይ ያጠነጠኑ ውይይቶችና ክርክሮች የሚደረጉባቸው የተለያዩ የጋራ መድረኮች በማዘጋጀት ይህ የአማራጭ ሀይል ነጥሮ እንዲወጣ ታደርጉ ዘንድ ለነጻነት ለቆሙ ለሁሉም የሜድያ ተቋማት፤ ያክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ትግሉንና ድሉን የጋራ እናድርገው!
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክርቤት
source -http://etntc.org/ENTC/wp/wp-content/uploads/ENTC-PR-0727.pdf

No comments:

Post a Comment

wanted officials