አንድነት “መንግስት የውንብድና ጥቃት እያደረሰብኝ ነው” አለ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የአዲስ አበባ ም/ቤት ስራ አስፈፃሚዎች፤ ገዢው ፓርቲ በአንድነት አባላት ላይ የመንግስታዊ ውንብድና ጥቃት እያደረሰብን ነው ሲል የከሰሱ ሲሆን ጥቃቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ጠይቀዋል፡፡
የፓርቲው የአዲስ አበባ ምክር ቤት፤በመንግስት ውንብድና ጥቃት ደርሶባቸዋል ያላቸውን የአመራር አባላት ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን ስማቸው ከተጠቀሰው 13 የፓርቲው አባላት ውስጥ የአንድነት የአዲስ አበባ ስራ አስፈፃሚና ፀሀፊ አቶ እንግዳወርቅ ማሞ፤ በመንግስት ደህንነቶች ደረሰብኝ ያሉትን የአካል ጉዳት አሳይተዋል፡፡ ፀሐፊው የወለቀውን የታችኛው ጥርሳቸውን ለጋዜጠኞች ያሳዩ ሲሆን፣ “ይህ ጥቃት የደረሰብን በጠራራ ፀሐይ በመንግስት ወንበዴዎች ነው” ሲሉ አማረዋል፡፡ “የማላውቃቸው ሰዎች በተደጋጋሚ እየደወሉ ማስጠንቀቂያ ይሰጡኝ ነበር ያሉት” አቶ እንግዳወርቅ፤ ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም በመጀመሪያ በመኪና ሊገጩኝ ሞክረው አልተሳካላቸውም” ካሉ በኋላ፤ ዞረው መጥተው የእኔንና የፓርቲዬን ስም በመጠየቅ መኪና ውስጥ በግድ ሊያስገቡኝ ሞክረው “ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልሄድም” በማለቴ፣ በሽጉጥ ሰደፍ በደረሰብኝ ድብደባ ጥርሴ ከመውለቁም ባሻገር፣ መላ ሰውነቴ ተጎድቷል በማለት የወለቀ ጥርሳቸውን አሳይተዋል፡፡ የአዲስ አበባ አንድነት ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ነብዩ ባዘዘው እንደተናገሩት፤“ኢህአዴግ በወንበዴዎቹ በኩል በአንድነት አባላት ላይ ዘርፈ ብዙ ጥቃት እያደረሰ ያለው ፓርቲው በምርጫው ውጤት እንዳያመጣ ከወዲሁ ለማዳከምና ለማስተጓጎል ነው” ብለዋል፡፡
አንድን መንግስት እንዴት ወንበዴ ማለት ይቻላል፤ ከህግስ አንፃር ገለፃው እንዴት ይታያል? በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ “ብሄራዊ ደህንነትና መረጃ ተቋም ዜጎችን መጠበቅ እያለበት፤ ባሰማራቸው የደህንነት ሰራተኞች ዜጎችን በየአደባባዩ የሚዘርር ሆኖ ሲገኝ፤ ከወንበዴነት ሌላ ምን ቋንቋ ይገልፀዋል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል – የስራ አስፈፃሚ አባላቱ፡፡
አንድን መንግስት እንዴት ወንበዴ ማለት ይቻላል፤ ከህግስ አንፃር ገለፃው እንዴት ይታያል? በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ “ብሄራዊ ደህንነትና መረጃ ተቋም ዜጎችን መጠበቅ እያለበት፤ ባሰማራቸው የደህንነት ሰራተኞች ዜጎችን በየአደባባዩ የሚዘርር ሆኖ ሲገኝ፤ ከወንበዴነት ሌላ ምን ቋንቋ ይገልፀዋል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል – የስራ አስፈፃሚ አባላቱ፡፡
በተለያዩ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ አደራጅ ሀይሎች በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ድብደባ፣ የአካል ጉዳትና ማስፈራሪያ ይደርስባቸዋል ያሉት ስራ አስፈፃሚዎቹ፤ጥቃቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን ብለዋል፡፡ ጥቃት ደርሶባቸዋል ተብለው ስማቸው የተዘረዘሩት 13 የአንድነት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አመራሮች እንደሆኑ የገለፀው ስራ አስፈፃሚው፤ከእነዚህም በላይ በርካታ አባላት መጎዳታቸውን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ጉዳት እንደደረሰባቸው በእለቱ የተናገሩት አቶ እንግዳወርቅ፤ ድብደባው የደረሰብዎት በደህንነት አባላት መሆኑን በምን አወቁ? መታወቂያ አይተዋል ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ በድብደባው ራሳቸውን ስተው መውደቃቸውን ገልጸው፣ሆኖም ከዚያ በፊት ከሚደርስባቸው ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም በእለቱ ስለፓርቲያቸው ከቀረበላቸው ጥያቄ በመነሳት፣በደህንነት ኃይሎች መደብደባቸውን እንዳወቁ ተናግረዋል፡፡
“ኢህአዴግ በአዲስ አበባ ም/ቤት አባላት ላይ ጥቃቱን አጠናክሮ የቀጠለው በቅርቡ “የእሪታ ቀን” በሚል ከተዘጋጀው ሰላማዊ ሰልፍ ወዲህ ነው” ያሉት የስራ አስፈፃሚ አባሉ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፤ ኢህአዴግ መንግስታዊ ውንብድናውን ካላቆመ ፓርቲው አሁንም ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት የጥቃቱን መጠንና ጥልቀት ለኢትዮጵያና ለአለም ህዝብ ማጋለጡን እንደሚቀጥል አሳስበዋል፡፡ የተደበደቡ አባላትን ጉዳይ ለፍርድ ለማቅረብ መዘጋጀቱንም ስራ አስፈፃሚው ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቶች ነፃ አይደሉም ትላላችሁ፤ ሆኖም ግን ክስ ትመሰርታላችሁ፤ ይህን የምታደርጉት ለምንድን ነው በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ ሲመልሱ “ላለፉት 23 ዓመታት ከታየው ልምድ በመነሳት ፍትህ በአገሪቱ ላይ አለመኖሩን ብናውቅም እኛ ግን ፍትህ ከመጠየቅ አንቦዝንም” ያሉት ስራ አስፈፃሚዎቹ፤ በዚህ አገር ፍትህ ላለመኖሩ የእነ አንዷለም አራጌ፣ የእነ እስክንድር ነጋና ሌሎችም የፓርቲው አባላት እንዲሁም የጋዜጠኞች እስርና እንግልት ማሳያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል – የስራ አስፈፃሚ አባላቱ፡፡
አንድነት ፓርቲ “ኢህአዴግ መንግስታዊ ውንብድና እየፈፀመብኝ ነው” ማለቱን በተመለከተ የጠየቅናቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፣ የፓርቲው መግለጫ እንዳልደረሳቸው ጠቁመው፣ ፓርቲው መግለጫውን እንዴትና በምን ሁኔታ እንደፃፈው ሳይመለከቱ፣ ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
አንድነት ፓርቲ “ኢህአዴግ መንግስታዊ ውንብድና እየፈፀመብኝ ነው” ማለቱን በተመለከተ የጠየቅናቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፣ የፓርቲው መግለጫ እንዳልደረሳቸው ጠቁመው፣ ፓርቲው መግለጫውን እንዴትና በምን ሁኔታ እንደፃፈው ሳይመለከቱ፣ ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment