የኢትዮጵያ ቴሌኮም ችግር ኔትወርክ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ ሲስተሙ ነው ተባለ
‹‹ከቴሌኮም ማስፋፊያ ሥራ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው›› ኢትዮ ቴሌኮም
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የቻይናው ህዋዌ ኩባንያ ለኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ሥራዎችን እየሠራ ቢሆንም፣ ቀደም ብሎ ይታወቅ ከነበረው የኔትወርክ ችግር በተጨማሪ ሌሎች ሲስተሞችም ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን ተጠቃሚዎች እየገለጹ ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ በትግበራ ላይ ካለው የቴሌኮም ማስፋፊያ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ችግሮች መኖራቸውን አምኖ፣ ቀደም ብሎ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ማስታወቁን በማስታወስ፣ የተጋነነ ችግር ባለመሆኑ በቅርብ ቀን ሁሉም ነገር እንደሚስተካከል ገልጿል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች እንደገለጹት፣ የ1.6 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ከአንድ አገር ለመጡት ሁለት የቻይና ኩባንያዎች ማለትም ዜድቲኢና ሁዋዌ ሲሰጥ ጥሩ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተስፋ ቢያደርጉም፣ አገልግሎቱ ከሳምንታት ያለፈ አልሆነም፡፡ ሁዋዌ የኔትወርክ ችግርን ለመቅረፍ ሥራውን እንደጀመረ በተለይ ‹‹ኖኪያ ኔትወርክ ኤርያ›› በሚባሉት አካባቢዎች ችግሩ ለጊዜው በመፈታቱ ደስታ ተሰምቷቸው እንደነበር የገለጹት ደንበኞች፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊዎች በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰኔ 2006 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የአዲስ አበባ ኔትወርክ ችግር መቶ በመቶ እንደሚቀረፍ ሲገለጽ፣ ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
የኃላፊዎቹን ገለጻ በትክክል መስማት አለመስማታቸውን እስከሚጠራጠሩ ድረስ፣ መቶ በመቶ የኔትወርክ ችግር ይቀርፋል በተባለበት ወር ሙሉ በሙሉ ባይሆንም፣ ከፍተኛ የሆነ የኔትወርክ ችግር ተባብሶ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡
‹‹ፈጣን የኔትወርክ አገልግሎት ለማግኘት 3Gን ተጠቀሙ›› የሚለውን የቴሌኮም ማስታወቂያ ተከትለውና በአገልግሎቱ ተማምነው የ‹‹3G›› አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚገልጹት ደንበኞች፣ የሞሉት ገንዘብ ተጠቅመውበት ሳይሆን ስልካቸው ሥራ ላይ ሳይውል ሒሳባቸው በነፃ መወሰዱ ችግራቸውን እንዳባባሰው ይናገራሉ፡፡
የችግሩን ሁኔታ ለማስረዳት በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችና ዋና መሥሪያ ቤት ቢሄዱም፣ እንኳን ችግራቸውን የሚያዳምጣቸው ቀርቶ በአግባቡ የሚያስተናግዳቸው በማጣታቸው አዝነው መመለሳቸውን ደንበኞች ገልጸዋል፡፡ ችግሩ በተለይ በሐምሌ ወር ቀጥሎ መባባሱንና የኔትወርክ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮ ቴሌኮም ለተጠቃሚዎች (ደንበኞች) የለቀቃቸው የገንዘብ መሙያ፣ ማስተላለፊያ፣ ቀሪ ሒሳብ ማወቂያ ሲስተሞችና በአጠቃላይ ደውሎ መገናኘት አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡
የቫውቸር ካርድ ገዝተው ለመሙላት ሲታገሉ አልገባ ያላቸው ደንበኞች፣ ባለሱቆች ችግሩን ያመጡት ይመስል ከእነሱ ጋር ግብግብ ላይ መክረማቸውንም አውስተዋል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው የመንግሥት አካል ችግሩን ተገንዝቦና አጣርቶ መፍትሔ የሚመጣበትን መንገድ ቢያመቻች የተሻለ መሆኑንና የኋሊት ከመሄድ እንዲያድናቸው የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ጠይቀዋል፡፡
ደንበኞቹ ያነሷቸው ችግሮች በከፊል መፈጠራቸውን ያመነው ኢትዮ ቴሌኮም ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ የሚታዩትን አንዳንድ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡
በትግበራ ላይ ካለው የቴሌኮም ማስፋፊያ ሥራ ጋር በተያያዘ፣ አዲሱን ሲስተም ከነባሩ ጋር በማጣጣም የትግበራ ሒደት በኢቪዲኦ፣ ዋን ኤክስ (1X) አገልግሎትና በካርድ መሙላት ዙሪያ የተወሰኑ ችግሮች እየተስተዋሉ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ችግሮቹ የኢቪዲኦና ዋን ኤክስ፣ የሲዲኤምኤ ዳታ አገልግሎት መቆራረጥ፣ ከሽያጭ በኋላ የሚስተናገድ ሲም መቀየር፣ የጠፋ ሲም ማዘጋት፣ የተጓዳኝ አገልግሎቶች ትዕዛዝ በሲስተም ቶሎ ያለማለቅና ሌሎችም ችግሮች መሆናቸውን የጠቀሰው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ያልተለዩትን ትዕዛዞች በመለየት በየ24 ሰዓት በደንበኛው አካውንት ላይ በየዕለቱ እየተሞሉ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡
ችግሮቹን ለመፍታት የቴክኒክ ቡድን አቋቁሞ በመሥራት ላይ መሆኑን የገለጸው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ደንበኞች ችግሮቹ መኖራቸውን ተገንዝበው የማስተካከያ ሥራው ሙሉ በሙሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በትዕግሥት እንዲጠባበቁ ጠይቋል፡፡
No comments:
Post a Comment