Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, July 30, 2014

የመለሰ ዜናዊ አምላኪ፣ የህወሃት ባሪያ ..የሌባ አይነደረቅ . .

የሌባ አይነደረቅ . . .
ሰውየው ሙክክ ያለ የመለሰ ዜናዊ አምላኪ፣ የህወሃት ባሪያ ነው። በቃ መለስ ያስነጠሳትን ሁሉ በትምህርተ ጥቅስ አድርጎ የቤቱ ግድግዳ ላይ ሊሰቅል የሚዳዳው አይነት። ለምሁሩ፣ ባለ እራዕዮ፣ የአፍሪካ ተከራካሪ፣የማሌሊት . . .መለስ ዜናዊ ያለውን ግላዊ ፍቅር እና ታማኝነት ያየ ማንም ሰው ይሄ ወገን እስከ ከመቃብር ወዲያም ቢሆን ከታማኑነቱ ፈቀቅ ይላል ብሎ አይጠረጥርም።
መቼም ሰው የሚፈተነው በግዜ ነው እና ከጥቂት ግዜያት ወዲህ “ሙት አይሰማም” ብሎ ነው መሰል ይሄ ግልገል ባለ እራዕይ የአውራው ባለ እራዕይ መሪውን ስራወች እና እምነቶች በጎንዮሽም ቢሆን መነካካት ሲጀምር ሳየው “አወይ ጴጥሮስ ! ” ለማለት እየተገደድኩ ነው። ዛሬ ነገርን ነገር አመጣው እና የዛች ባድመ የምትባል የደም መሬት ጉዳይ ተነሳ። እናም ይሄ ወገን ባድመን በማስመልከት የተናገረው ነገር ከእውነት አስደነገጠኝ። ለእኔ አይደለም ያስደነገጠኝ፣ ከመቃብር ስር ላለው የሱ አለቃ እንጂ። የሚገርመው ነገር የባድመን ጉዳይ ጎትቶ ወደ ጨዋታ ያመጣው እሱው እራሱ መሆኑ ነው። በባድመ ላይ ያለውን አመለካከት ስረዳው ይብሩኑ ግራ መጋባቱ አስገረምኝ።
መቼም “ባድመ የኔ መሬት ናት” ብሎ 60 ሺ ልጆቹን የገበረውን የኢትዩጵያ ህዝብን ባድመ የማናት ብሎ መጠየቅ ቂልነት ነው። የሃገሬ መሬት ናት ብሎ ስላመነ ነው ያ ሁሉ ኢትዩጵያዊ ወጣት ከኦሮምያ፣ከአማራ፣ከጉራጌ፣ወላይታ. . . መንደሮች እየከነፈ ሄዶ መሬቷ ላይ ደሙን ያፈሰሰው፣አጥንቱን የከሰከሰው። በደሙ ያስከበራትን ምድር ደሞ ለድርድር የሚያቀርብ ኢትዩጵያዊ የለም።በቃ የእኛ የነበረውን መሬት ጠላት ሊቀማ ሲል ተከላክለን አስመልሰናል፣ መሬታችንን አግኝተናል። ብሎ ነው የኢትዩጵያ ህዝብ የባድመን ታሪክ በጀግንነት የዘጋው። ለኢትዩጵያ ህዝብ ባድመ ሁሌም የኢትዩጵያ ግዛት ናት።
በሌላው በኩል ግን ኢትዩጵያን የሚመራው ህወሃት እና የህወሃት ልብ እና ጭንቅላቱ የነበረው መለስ ዜናዊ በባድመ የኢትዩጵያ ግዛትነት እንደ ሌላው የኢትዩጵያ ህዝብ እርግጠኛ አልነበረም። እናም ባድመ በኢትዩጵያውያን ወጣቶች ደም ከሻብያ ከተመለሰች በኋላ የባድመ ትክክለኛ ባለቤትት ማን እንደሆነ አጣርቶ እንዲወስን ለአስታራቂ ኮምሽን አሳልፎ ሃላፊነቱን ሰጠ። መቼም የእራሱ የሆነ ንብረቱ እንደተቀማ የሚያምን ግለሰብ እቃው ሲገኝ ሽማግሌ የእቃውን ባለቤት አጣርቶ ለፈለገው ቢሰጥ እቀበላለሁ አይልም። የእራሱን የንብረቱ ባለቤትነት የተጠራጠረ ብቻ ነው ሌላ አካል ንብረቱ የእኔ ወይም የሌላ እንደሆነ አጣርቶ “ለእኔ ቢሰጠኝ እቀበላለሁ። ያንተ አይደለም ብሎ ለሌላ ቢሰጠውም እስማማለሁ“ ብሎ የሚፈርመው። እናም መለስ ያንን ነበረ ያደረገው።
መለስ ዜናዊ ባድመ የኢትዩጵየ መሆኗን ስለሚጠራጠር አጣሪ ኮሚሽን አጣርቶ እንዲወስን ፈቀደ። አጣሪ ኮሚሽን ተብየውም አጣርቶ ባ ድ መ የ ኤ ር ት ራ ግ ዛ ት ና ት ብ ሎ ወ ሰ ነ ። መለስ ዜናዊም የ ባ ድ መ ን የ ኤ ር ት ራ ግ ዛ ት ነ ት ተ ቀ ብ ሎ በ ፊ ር ማ ው አ ረ ጋ ገ ጠ። እዚህ ጋርሌላ ታሪክ የለም በቃ ተከተተ።
ምንም እንኳን የኤርትራ ንብረት ብሎ በፊርማው አሳልፎ ቢሰጣትም መለስ ዜናዊ ባድመን በወቅቱ የኢትዩጵያን ሰራዊት ከስፍራ አስነስቶ ባድመን ለሻቢያ አሳልፎ ማስረከቡ ከኢትዩጵያ ህዝብ ጋር (በተለይ ደሞ መሰረቴ ነው ከሚለው የትግራይ ህዝብ በኩል) የሚያስነሳበትን ተቃውሞ ጠንቅቆ ያውቅ ነበረ። እናም ባድመን የህዝቡ ስሜት እንደናረ እና ጥያቄው ገና ከህዝብ ህሊና ሳይወጣ ለሻብያ አሳልፎ ከመስጠት በሰበብ አስባቡ ምክንያት እየፈጠሩ ለህዝብ ማደናገሪያ እንዲሆን ባድመን ከስምምነቱ ውጭ ይዞ ማቆየትን መረጠ።
እንደውም በሚያስቅ ሁኔታ ባድመ በኮምሺኑ ለሻብያ መሰጠትዋ እየታወቀ ከወር በላይ የመለስ ዜናዊ ህወሃት/ኢህአዴግ ሹመኞች ”ባድመ ለኢትዩጵያ ተሰጠች“ እያሉ ህዝብን ሊያሞኙ ሲሽከረከሩ ሰነበቱ። መጨረሻ ግን ግልጽ ጽሁፍ አንብቦ የሚረዳን ህዝብ በግግምና ማጃጃል ስለማይቻል ሃቁን በአደባባይ አመኑ። ማመን ብቻ አይደለም መለስ ዜናዊ፣ በረከት ሰምዖን፣ስዮም መስፍን እና ሌሎች የህወሃት ባለ ስልጣናት ኮሚሺኑ ”ባድመ የኤርትራ ናት“ ብሎ የወሰነውን ውሳኔ እንደሚቀበሉ በአደባባይ አፋቸውን ሞልተው ለህዝብ ተናግረዋል። ያውም ደግመው ደጋግመው።
እናም ዛሬ እኔን ያስገረመኝ ነገር ይሀው የመለስ ተከታይ “ባድመ ዛሬም የኢትዮጵያ ንብረት ናት።መለስ ዜናዊ እና ህወሃት/ኢህአዴግ ባድመን ለሻብያ አሳልፈው አልሰጧትም” ብሎ ሊከራከር ሲሞክር መስማቴ ነው። የባድመን ኢትዩጵያዊነት ቢቀበል ደስ ብሎኝ በጭብጨባ በተቀበልኩት። እሱ ግን መለስ ዜናዊ በፊርማው የባድመን የኤርትራ ግዛትነት መቀበል ሳይቃወም፣ በማንኛውም አለም አቀፍ ህግ መሰረት መለስ ዜናዊ በፊርማው አሳልፎ የሰጣት ባድመ የኤርትራ ግዛት ተደርጋ እንደምትታይ መናገር ሳይፈልግ ዛሬ ባድመ ላይ ያለው የኢትዩጵያ ሰራዊት ስለሆነ ብቻ ባድመ የኢትዩጵያ ህጋዊ ግዛት ናት አይነት ሸፋፋ ሙግት መሆኑ ነበረ ያስገረመኝ።
የኢትዩጵያ ሰራዊት ባድመን ከሻብያ ተከላክሎ በእጁ ማድገባቱ የባድመን ኢትዩጵያዊነት ለማረጋገጥ የመጀመሪያው እርምጃ እንጂ ብቸኛው እርምጃ አልነበረም። ሰራዊቱ በደሙ የተከላከለውን ምድር የሃገሪቱ መንግስት እና የፖለቲካ አካሉ በህግ የኢትዩጵያ ግዛትነቷን በማያወላደ መልኩ አምኖ ማረጋገጥ ሲችል ብቻ ነበረ ባድመ የኢትዩጵያ ልትሆን ትችል የነበረው። ወታደሩ በደሙ ያገኘውን ድል መንግስት ባደባባይ በስምነት ስም አሳልፎ ለሻብያ ከሰጠ በኋላ ግን “ባድመ ዛሬም የኢትዩጵያ ነች” እያሉ መቀለድ ማንንም አያሳምንም። ባድመ የኢትዩጵያ ነበረች ነገር ግን መለስ ዜናዊ እና ህወሃት በአለም ህዝብ ፊት በፈረሙት ፊርማ አሳልፈው ለሻብያ ሰጥተዋታል። በመለስ ዜናዊ እና ሻብያ ስምምነት መሰረት ባድመ የኤርትራ ናት።
ዛሬ ኢትዩጵያ ሰራዊቷን ከባድመ አላስነሳም ብላ መቀመጧ ባድመን የኢትዮጵያ ያደርጋታል የሚለው የህወሃቶች ማደናገሪያ ጆክ ምናልባት ቤቱን ለመሸጥ ተስማምቶ ከፈረመ እና ሂሳቡን ከተቀበለ በኋላ ከቤቱ አልወጣም ብሎ ክችች እንዳለ ጅል ነገር ነው የሚሆነው።ኮንትራት ፈርመሃል ቤትህን ሸጠሃል እና ቤቱ ያንተ ንብረት አይደለም። መጥኖ ነበር በፊቱን መደቆስ ዛሬ ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ ብለን በተረት እንዳናልፈው የሃገር ጉዳይ ነው እና ለዚህ ወገን እና ለመሰል ህዝብን በጠመዝማዛ ሰበብ አስባብ ሊሸውዱ ለሚሞክሩ ህወሃታውያን ምክር ቢጤ ጣል አድርገን እንዝጋ።
ልብ ገዝታችሁ ባድመን ብቻ ሳይሆን አሰብንም ጨምሮ መለስ ዜናዊ እና ህወሃት እየፈረሙ አስመራ ለተቀመጠው ጌታ ፈጣሪያቸው ለሻቢያ አሳልፈው የሰጧቸውን የሃገራችን ግዛቶች የኢትዩጵያ አካል ናቸው ብላችሁ እንደ ሰፊው የሃገራችሁ ለማመን ከተዘጋጃችሁ መልካም-ደስ ይለናል፡ እውነታውን ለማየት በመብቃታችሁ። ነገር ግን የኢትዩጵ ግዛት እየተቆረሰ (በምስራቅ የሃገራችን ግዛት ጭምር)ለጎረቤት ሃገሮች የተሰጠበትን ስምምነት ሳትቃወሙ፣ ግዛቶቹንም አሳልፈው የሰጡ ግለሰቦችን ድርጊት ሳታወግዙ ባድመ የእኛ ናት፣ አሰብ ግዛታችን ምናምን ስትሉ ምናልባት የአዕምሮ ጤነኝነታችሁ እንጠይቅ እንደሆነ እንጂ ለሃገር ተቆርቋሪ ናችሁ ብለን አንሸወድም። ምክንያቱም የሃገር ግዛት መሸጥን ለመቃወም የተሸጠበትን ስምምነት እና የሸጠውን አካል ድርጊት መቀወም የመጀመሪያው እርምና ነው እና።

No comments:

Post a Comment

wanted officials